ዜና፡-የኢ.ፌ.ድ.ሪ ፕሬዝዳንት ሣህለ-ወርቅ ዘውዴ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አኪንዉሚ አደሲና ጋር ኢትዮጵያ ትኩረት ስለምትሰጣቸው የልማት እቅዶች መከሩ

የኢ.ፌ.ድ.ሪ ፕሬዝዳንት ሣህለ-ወርቅ ዘውዴ እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አኪንዉሚ አደሲና
ፎቶ: አፍሪካ ልማት ባንክ

ዲስ አበባ፣ 12/2014፡- ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አይቮሪኮስት የሚገኙት የኢ.ፌ.ድ.ሪ ፕሬዝዳንት ሣህለ-ወርቅ ዘውዴ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አኪንዉሚ አደሲና ጋር የተገናኙ ሲሆን፣ በወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታና ቀጣይ የሐገሪቱ የልማት የትኩረት አቅጣጫ ላይ ተወያይተዋል፡፡ አቢጃን በሚገኘው የባንኩ ዋና መስሪያ ቤት የተገኙት ፕሬዝዳንቷ በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታና ከድህረ – ኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ አገሪቱ ቅድሚያ ስለምትሰጠው የልማት ስራዎች  ከባንኩ ፕሬዝዳንት ጋር ተወያይተዋል፡፡

የአፍሪካ ልማት ባንክ የኢትዮጵያ ተመራጭ የልማት አጋር ነው ያሉት ፕሬዝዳንቷ፣ ባንኩ በኢትዮጵያ የመሰረት ልማት ግንባታ ዘርፍ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ድጋፍ ሲያደርግ በመቆየቱ አመስግነዋል፡፡ “በግብርና፤ ትራንስፖርት፣ ኃይል ማመንጫና የውሃ መሰረተ-ልማት ስራዎች ላይ ባንኩ ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን ያደረገ ሲሆን፣ በዘርፎቹ ለተከናወኑ ፕሮጀክቶችም ከአንድ ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ብድር በማቅረብ ከፍተኛ አስተዋፆ አበርክቷል፡፡” ሲሉ ፕሬዝዳንቷ አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

ምንም እንኳን ባለፉት ሁለት አመታት ኢትዮጵያውያን ከባድ የሚባል ጊዜን እያሳለፉ ቢሆንም መጪው ጊዜ ለኢትዮጵያ ብሩህ እንደሆነ የሚጠቁሙ ተስፋዎች እንዳሉ አብራርተዋል፡፡ “በተለይ ሐገሪቱ እያስፋፋች የምትገኘው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ለወጣቱ ህብረተሰብ በተለይም ለሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የተሻሉ እድሎችን ይዞ መጥቷል፡፡” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሴቶች ለሐገራቸው ልማት ስለሚያበረክቱት አስተዋፆ በአድናቆት ያብራሩት ፕሬዝዳንት ሣህለ-ወርቅ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ የወጣቶችን የሥራ እድል የሚያስፋፉ ውጥኖችንና የሴቶችን ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ የልማት ጅምሮችን የሚያበረታታበትን መንገድ እንደሚያደንቁ የገለፁ ሲሆን፤ በተለይ የባንኩ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አደሲና ለወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚነት የሚሰጡትን ከልብ የመነጨ ትኩረት እሳቸውም እንደሚጋሩ ገልፀዋል፡፡

በኢትዮጵያ መንግስትና የአፍሪካ ልማት ባንክ መካከል ያለው አጋርነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለፁት የባንኩ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አደሲና፣ በኢትዮጵያ በባንኩ የገንዘብ አቅርቦት የተሰሩ የልማት ፕሮጀክቶች ባንኩ ትኩረት በሚሰጣቸው አምስት የስኬት መለኪያዎች ሲመዘኑ ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበባቸው ናቸው ሲል ገልፀዋል፡፡“ከአዲስ አበባ ተነስቶ በሞያሌ አልፎ የናይሮቢና ሞምባሳ ከተሞችን የሚያገናኘው አውራ ጎዳና ግንባታን ባንኩ በገንዘብ መደገፉን የገለፁት ፕሬዝዳንት አደሲና ለዚህም ከአንድ ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ብድር እንደፈቀዱ ገልፀዋል፡፡የፕሮጀክቱ በስኬት መጠናቀቅ በኢትዮጵያና ኬንያ መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ እስከ 400$ ድረስ እንደሚያሳድገው ገልፀዋል፡፡”

በንኩ በቀጣይም 402 ሚሊዮን ዶላር የተመደበለትን በአዲስ አበባ የቀበና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክትን ለማስጀመር የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግ ፕሬዝዳንቱ ገልፀዋል፡፡ ፕሮጀክቱ የግሉን ዘርፍ በሐገሪቱ ልማት የማሳተፍ ተቋማዊ አሰራርን እንደሚያጎለብትም ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን የፖለቲካ አለመረጋጋቶች ለመቅረፍ የምታደርገውን ጥረት እንደሚያደንቁና የአፍሪካ ቀንድ ባጠቃላይ የተረጋጋ እንዲሆን ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ዶ/ር አደሲና ገልፀዋል፡፡ “ኢትዮጵያን ለመርዳት የሚቻለውን ሁሉ እናደርጋለን፣ ከገጠማችሁ ፈተና ለመላቀቅ በምታደርጉት ጥረት የአፍሪካ ልማት ባንክ ከጎናችሁ ይቆማል፤ የገጠማችሁ ፈተናዎች በፍጥነት የሚቋጩበት ሁኔታ እንዲፈጠር እንፀልያለን፡፡ ” ሲሉ ዶ/ር አደሲና ለፕሬዝዳንት ሣህለ-ወርቅ ገልፀውላቸዋል፡፡

በሐገሪቱ የተከሰተው አውዳሚ ጦርነት ከተቋጨ በኋላ የመንግስት ቀዳሚ ትኩረት ሐገሪቱን መልሶ መገንባት እንደሆነ ፕሬዝዳንት ሣህለ-ወርቅ ገልፀዋል፡፡ የአፍሪካ ልማት ባንክ የኢትዮጵያን ቀጣይ የልማት ጉዞ እንደሚደግፍም የባንኩ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አደሲና ስላረጋገጡላቸው ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በመገባደድ ላይ ባለው የፈረንጆቹ አመት የአፍሪካ ልማት ባንክ ቦርድ ለኢትዮጵያ ካፀደቃቸው ድጋፎች መካከል ከ5 አመት በታች የሚገኙ ህፃናት በአልሚ ንጥረ-ነገር የበለፀገ ምግብ እንዲያገኙ ድጋፍ ለማድረግ፣ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግና የተሻሻለ የጤና አጠባበቅ እውቀትና አሰራሮች እንዲስፋፋ ለማገዝ ከ27 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ባንኩ በልዩ ትኩረት ከደገፋቸው ፕሮጀክቶች መካከል የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ የሆኑ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በተገነቡባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች በግብርና የሥራ ፈጠራ ዘርፍ እንዲሰማሩ ለማገዝ 47 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ያደረገው ተጠቃሽ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የከቪድ ወረርሽኝን ለመቋቋም ለምታደርገው ሥራ እንዲውል ባንኩ 165 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር እርዳታ ሐምሌ 2012 ላይ የለገሰ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ ምጣኔ ኃብት ኮቪድ ከመከሰቱ በፊት በነበረው ዓመት የ8.3 በመቶ እድገት ያሳየ ሲሆን፣በመገባደድ ላይ ባለው የፈረንጆች አመት የሐገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት 6.3 በመቶ ይሆናል ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የአፍሪካ ልማት ባንክ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የሚያደርገው ትብብር አዲስ አበባ የሚገኘውን የአፍሪካ ህብረት ዋና ጽ/ቤት አቅም ለማጠናከር ጭምር ይረዳል፡፡

ኢትዮጵያ በአመት ከአጠቃላይ የመንግስት በጀቷ 58 በመቶ ያህሉን ድህነትን በቀጥታ ለመቀነስ ለሚረዱ ፕሮጀክቶችና የዜጎቿ እድሜ እንዲጨምር በሚያስችሉ የልማት ስራዎች ላይ ታውላለች፡፡ የአፍሪካ ልማት ባንክ በኢትዮጵያ አጠቃላይ ወጪያቸው ከ1.6 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሆኑ 20 የልማት የፕሮጀክቶችን በትራንስፖርት፣ የኃይል አቅርቦት፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና የንፅህና አጠባበቅ ዘርፍ ላይ ያተኮሩ የመሰረተ-ልማት ፕሮጀክቶችን በመደገፍ ላይ ይገኛል፡፡አስ  

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.