ትንታኔ፡- ከምስራቅ ወለጋ የተፈናቀሉ የአማራ ብሄር ተወላጆች በአዲስ አበባ ተጠልለው ይገኛሉ

አስኮ የሚገኘው የወጣቶች ማእከል

 ጌታሁን ፀጋዬ 

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 12፣ 2014፤ ህዳር አጋማሽ ከኦሮሚያ ክልል ከምስራቅ ወለጋ የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች  በአዲስ አበባ መጠጊያ ፍለጋ ላይ እንደነበሩ ለአዲስ ስታንዳርድ ጥቆማዎች ደርሰው ነበር፡፡ ተፈናቃዮቹ በአብያተ ክርስቲያናት እና በወጣትማእከላት በተዘጋጁ ጊዜያዊ ካምፖች ተጠልለው እንደሚገኙ ከተነገረላቸው ቦታዎች መካከል በኮልፌ ቀራንዮ አስኮ እና ዘነበ ወርቅ ይገኙበታል።

የአዲስ ስታንዳርድ ዘጋቢ ወደ አምቦ በሚወስደው መንገድ የሚገኘውን አስኮ ሰፈር የጎበኘ ሲሆን በአካባቢው የሚገኝ በወጣቶች ማእከል ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮችን ጋር ስላሉበት ሁኔታ በአካል ተገኝቶ ተመልክቷል። በወጣት ማእከል ውስጥም አዛውንቶች ፤ሴቶች፤ሕፃናት እና ወንዶች የሚገኙ ሲሆን ተፈናቃዮች አንዱ የሆኑት አቶ አውራሪስ (ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው ተቀየረ) እንደተናገሩት  በመጀመሪያ የወጣት ማዕከሉ ለ72 ተፈናቃዮች  በበጎ ፈቃደኝነት ለ አንድ ሳምንት በመጠለያና ነት ሲያገለግል እንዳቆያቸው ተናግረዋል።

“የአካባቢው ህብረተሰብ ምግብ፣ ፍራሽ፣ ብርድ ልብስ፣  አንሶላ እና መሰል ነገሮችን ሲሰጡን ነበር፡፡” ያለው አዉራሪስ “ከ72 ተፈናቃዩች ውስጥ ግማሽ ያህሉ ወደ አዲስ አበባ የሚገኙ ዘመዶቻቸው ጋር ሲሄዱ ሌሎቻችን ግን  ከመጠለያ ውጪ ላይ እንገኛለን አሁን ያለብን  ትልቁ ችግር መጠለያ ነው።” ሲልም አክሏል፡፡ ከአውራሪስ በስተቀር አብዛኞቹ ተፈናቃዮች ስለ መፈናቀላቸው ሁኔታ ሲጠየቁ ከመፈናቀላቸው በፊት ይኖሩ የነበረው ምስራቅ ወለጋ መሆኑን ከመናገር በስተቀር የተፈናቀሉበትን ሁኔታ ለመግለፅ ሆነ ለመወያየት  እንዲሁም ለመናገር ፍቃደኛ አይደሉም፡፡ “ጥቃት እንዳይደርስብን እንፈራለን” እንዲሁም “ወደ መጣንበት እንዳንመለስ እንፈራለን” በማለት ዝምታ የመረጡበትን ምክንያት ያስረዳሉ።

የአስኮ ወጣቶች ማእከል ስራ አስኪያጅ አቶ መልካሙ እንኮሳ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት “ተፈናቃዮች በአስኮ ወጣቶች ማእከል ለአንድ ሳምንት ያህል በመጠለያነት ሲገለገሉ እንደነበር ነበር ነገር ግን ማእከሉን ለንግድ ስራ የተከራዩ ሰዎች ስራ  ለመስራት ስለተቸገሩ ተፈናቃዮቹ ሌላ አማራጭ እንዲፈልጉ ነግረናቸው  ተቋሙን ለቀው ወጥተዋል።” በማለት አብራርተዋል፡፡ አቶ መልካሙ አያይዘውም በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 ለስራ አስፈፃሚ ኮሚቴውና ሰላምና ፀጥታ ዘርፍ ተፈናቃዮቹ በተጠቀሰው ቦታ መኖራቸውን አሳውቀን እርዳታ እንዲያገኙ እና ጉዳዩን ከሚመለከታቸው አካላት ምላሽ እንዲሰጡን እየጠበቅን ነው” ብለዋል። አዲስ ስታንዳርድ በመቀጠል ስለሁኔታው የአዲስ አበባ ከተማ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጽ/ቤትን ጠይቃ ምላሽ ለማግኘት አቶ ዮናስ ዘውዴ “ሁኔታውን አጣርተን እናሳውቆታለን” ቢሉም  ከሳምንታት በውኀላ በድጋሚ በስልክ  ቢጠየቁም መረጃ የለንም ብለው መልሰዋል። 

አዲስ ስታንዳርድ የተፈናቃዮቹን ሁኔታ የበለጠ ለማጣራት  የአስኮ ወጣቶች ማዕከልን በድጋሚ ተገኝታ ጎብኝታለች።  ተፈናቃዮቹ አሁን በአካባቢው ባሉ ነጋዴ በተከራዩላቸው የመኖሪያ ቤት ውስጥ ተጠልለዋል የሚገኙ ሲሆን  የአካባቢው ማህበረሰብ ምግብና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን እየተረዱ እንደሚገኙ ተመልክታለች ። ነገር ግን  አሁንም ተፈናቃዮቹ ለደህንነታቸው በመፍራት ስለተፈናቀሉበት ምክንያት ለመነጋገር ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል ። “ወደ መጣንበት እንዳንመለስ እንፈራለን። “ ይላል አዉራሪስ ።

አቡነ አረጋዊ ቤተክርስቲያን

ከምስራቅ ወለጋ የተፈናቀሉ አማራ ብሄር ተወላጆች ተጠልለው የነበሩበት ቦታ ኮልፌ ቀራንዮ ዘነበወርቅ ሰፈር አቡነ አረጋዊ ቤተክርስቲያን ነበር።አዲስ ስታንዳርድ የቤተ ክርስቲያኗን ኃላፊ ቄስ መልአከ ማርያም መንግሥቱን አነጋግራለች። እንደ ደብሩ ሃላፊው ገለፃ “ከምስራቅ ወለጋ የተፈናቀሉ ወደ 120 የሚጠጉ የአማራ ብሄር ተወላጆች በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ለ2 ሳምንታት ተጠልለው የነበረ ሲሆን በፌዴራል መንግሥት፣ በኦሮሚያ ክልል መንግሥትና በአማራ ክልል መንግሥት እገዛ ወደ ተሻለ ቦታ እንዲዛወሩ ተደርጓል ምስራቅ ወለጋ ዞን በሌላ በሌላ አካባቢዎች እንዲሰፍሩ ተደርገዋል” ብለዋል ።

በተጨማሪም አዲስ ስታንዳርድ በብሔራዊ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊን ያነጋገረ ሲሆን ኮሚሽኑ  አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቦ “የኦሮሚያ አደጋና ስጋት አስተዳደር ኮሚሽን ይህንን ጥያቄ ሊመልስ ይገባል” ብሏል። ነገር ግን የኦሮሚያ ክልል የአደጋና ስጋት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊን ለማነጋገር የተደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም።

ባሳለፍነው ዓመት መጨረሻ ላይ በጊዳ ኪራሙ ወረዳ በነዋሪዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ግድያ እና መፈናቀል ተከትሎ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ገልጿል። በነሃሴ 14፣ 2013 ዓም የ150 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈውን የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎችን ድርጊት እንደሆነ ነዋሪዎች መናገራቸውን ኢሰመኮ በሪፖርቱ  አመልክቷል። መግለጫው በዚህ መሰል ጥቃት ምክንያት ነዋሪዎች በተለይም ሴቶችና ህጻናት ወደ አጎራባች አካባቢዎች ወደ አማራ ክልል እና ወደ ኪራሙ ከተማ መሰደዳቸውን ዘርዝሯል። ኢሰመጉ አያይዞም በማግስቱ አንዳንድ የአማራ ተወላጆች አጸፋውን በመመለስ 60 ሰዎችን ገድለዋል ሲል አብራርቷል። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ከፌደራል መንግስት ጋር ተቀናጅተው የነዋሪዎችን ደህንነት እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል። “በተለይ በአካባቢው የጸጥታ ሃይሎች ተሰማርተው የወሰዱት እርምጃ በአግባቡ ሊጣራ ይገባል” ሲሉ የኦሮሚያ ክልል መንግስትና የፌደራል መንግስት ጉዳዩን እንዲያጣራ ጠይቀዋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.