ዜና፡ እርቅ ይውረድ፣ የሰው ደም መፍሰስ ይብቃ ሰላም ይታወጅ ሲሉ ቅዱስነታቸው አቡነ ማትያስ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 12/2015 ዓ.ም፡- በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች መሳሪያ አንግበር የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጡ እና መንግስት በሩን ክፍት አድርጎ ሁሉንም እንዲያወያይ ቅዱስነታቸው አቡነ ማትያስ ጥሪ አቀረቡ። አቡነ ማትያስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት ነሃሴ 12 ቀን 2015 ዓ.ም በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ተንተርሰው ባቀረቡት ይፋዊ አባታዊ የሰላም ጥሪ እርቅ ይውረድ፣ የሰው ደም መፍሰስ ይብቃ ሰላም ይታወጅ፣ ምድሪቱንም እናሳርፋት ብለዋል።

ዘመነ ፓትርያርክነታችን ጆሮ ጭው የሚያደርግ ለማየት የሚያሰቅቅ መከራ የበዛበት በመሆኑ ልባችን ቢሰበርም ከመከራችን ባሻገር የእናንተ የልጆቻችን መከራ የከፋ ሁኖ ስለሚሰማን የመከራው ዳርቻ ይናፍቀናል ያሉት ብጹእነታቸው አሁን ያለው ችግር ወደ ሚቀጥለው ዘመን እንዳይሻገር ገትተነው ቀጣዩን አዲስ አመት በሰላም ለመቀበል እንድንችል ዘንድ ከጉልበት ሳይሆን ከልብ ሽብረክ በማለት እርቅ ይውረድ ብለዋል።

ከአካላዊ ጦርነት እስከ ቃላት ውርወራ ብዙ ጥላሸት የመቀባባት ሰለባ ሆነው የወደቁት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ልጆቻችን ትምህርት ሆነውን ልባችን ዘንበል ባለማለቱ ለወደፊት ሊመጣ የሚችለው ሲታሰብ እጅግ ያስፈራልና በዐራቱም ማዕዘን ነፍጥ አንሥታችሁ ያላችሁ በሙሉ ያነገባችሁትን ገዳይ መሣርያ አውርዳችሁ ለሰላምና ለዕርቅ ቅድሚያ በመስጠት ለአንዲት አገራችሁ ሕልውና ተገዢዎች እንድትሆኑ፤ መንግሥትም ልበ ሰፊ ሁኖ ሁሉንም ለውይይት እንዲሰበስብ በጽኑ እንለምናለን ብለዋል ብጹእነታቸው በደብዳቤያቸው።

በኢትዮጵያ ምድር ላይ ያላችሁ ሽማግሌዎች ሽምግልናችሁ ለዚህ ቀን ካልሆነ ለመቼም አይሆንምና በአገሩም ሽማግሌ የለም ወይ? መባሉ በሰማይ በምድር ያስወቅሳልና ልጆቻችሁን እንድትመክሩና እንድታስታርቁ ከዛሬ ጀምሮም ለሰላም ጠበቆች ሁናችሁ እንድትቆሙ አበክረን እንጠይቃለን ሲሉ አሳስበዋል።

በተለያዩ የውጭ ሀገራት ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ባስተላለፉት ጥሪ እናንተ በሰላም አገር እየኖራችሁ ዘመዶቻችሁ በእሳት ሲጠበሱ ዝም ብሎ ማየት ስለማይገባ እስከአሁን ስታደርጉት እንደቆያችሁት ሁሉ አሁንም ለሰላሙ ብርቱ ጥረት እንድታደርጉ በጥብቅ እናሳስባለን ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ግጭት ባለባቸው አከባቢዎች ሰላም እንዲሰፍን የበኩላቸውን ጥረትና እገዛ እንዲያደርጉ፣ ቤተ ክርስቲያንን የምንመራ ውሉደ ክህነትም መፍትሔ መሆን ሲገባን የችግሩ አካል ሆነዋል እየተባልን ነውና ውስጣችንን አጥርተን ለወገኖቻችን በአስታራቂነት ለመድረስ ጊዜው አሁን ስለሆነ ዛሬ እንድንነሣ መንፈሳዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን ብለዋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.