አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 13/ 2015 ዓ.ም፡- በአማራ ክልል ስላለው ወቅታዊ ውጥረት ዘገባ በመስራታቸው የታሰሩ 11 ጋዜጠኞችን መንግስት እንዲፈታ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን የተሰኘው የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ጠየቀ፡፡
ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ትላንት ባወጣው መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የክልል ልዩ ሀይልን መልሶ የማደራጀት ውሳኔ ማስተላለፋቸውን ተከትሎ በአማራ ክልል ውጥረት መንገሱን አስታውሶ ሐምሌ 28 በክልሉ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ከታወጀ ሶስት ቀን በኋላ የ “አልፋ ሚዲያ” መስራች በቃሉ አላምረው ለእስር መዳረጉን ገልጧል፡፡ በቃሉ ፍርድ ቤት አለመቅረቡን እና በምን ምክንያት እንደታሰረ እንዳልተነገረው ቡድኑ አስታውቀቋል፡፡
በተጨማሪም አማራ ሚዲያ ማዕከል የተሰኘ የዩቱዩብ ቻናል ዳይሬክተር የሆነው አባይ ዘውድ ከሐምሌ 3 ቀን ጀምሮ በእስር ላይ ይገኛል ያለው የቡድኑ መግለጫ በተመሳሳይ መልኩ አፍሪ ነጋሪ የተሰኘ ሚዲያ መስራች የሆነው ይድነቃቸው ከበደ በዚሁ ሳምንት ሀሙስ ነሃሴ 11 ቀን ከመኖሪያ ቤቱ ተይዞ ለእስር መዳረጉን ገልጧል፡፡ ይድነቃቸው በቁጥጥር ስር የዋለው በቅርቡ በአማራ ክልል የተከሰተውን ሁነት በመዘገቡ መሆኑን እና በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ 4ኛ ፖሊስ ጣቢያ እንደሚገኝ ገልጧል፡፡
“እነዚህ እስራት የመንግስትን ተቺዎች ዝም ለማሰኘት ባለስልጣናቱ የጀመሩት ሰፊ እንቅስቃሴ አካል ሲሆን ከዚህ አመት መጀመሪያ ጀምሮ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ብሔርተኝነት አቀንቃኞችን በእስር ላይ ይገኛሉ” ሲል ገልጧል።
“ከሚያዚያ ወር ጀምሮ በክልሉ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚፈፀመው የጋዜጠኞች እስር የኢትዮጵያ መንግስት ስላለው ውጥረት ሚዲያዎች ገለልተኛ ሽፋን እንዳይሰጡ የማድረግ ስትራቴጂው ነው፤ ጋዜጠኞች የዘፈቀደ እስራት ስጋት ሳይኖርባቸው ትችት መሰንዘር ወይም የተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ሀሳብ መስጠት አይችሉም። የድንበር የለሽ ጋዜጠኞች ቡድን ጋዜጠኞቹ በአስቸኳይ እንዲፈቱ አጥብቆ ይጠይቃል” ሲሉ የድንበር የለሽ ጋዜጠኞች ቡድን ከሰሃራ በታች ዳይሬክተር ሳዲቦ ማሮንግ ገልፀዋል፡፡ አስ