ዜና፡- ጃኬን አሳታሚ ኃ/የተ/የግ/ማህበር በሚታወቅበት አዲስ ስታንዳርድ ድረ ገጽ አማካኝነት የሶስት ቋንቋ አገልግሎት ጀመረ

አዲሱ የአዲስ ስታንዳርድ በይነ መረብ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 7፣ 2014 ዓም፡- የአዲስ ስታንዳርድ የተሰኘው ታዋቂው የበይነ መረብ እና የህትመት ሚዲያ አሳታሚ የሆነው ጃኬን አሳታሚ ኃ/የተ/የግ/ማህበር ከዛሬ ጀምሮ የመጀመሪያውን የሶስት ቋንቋ ድረ-ገጽ በመክፈት የቋንቋ ብዝሃነቱን በማስፋፋት አገልግሎቱን ጀመረ።

የባለሶስት ቋንቋ ድረ-ገጽ አገልግሎቶችን ከመጀመሪያው አዲስ ስታንዳርዳርድ እንግሊዘኛ ቋንቋ በማስፋፋት በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት ከሚነገሩት ሁለት ተጨማሪ የሃገር ውስጥ ቋንቋዎች በአማርኛ እና በአፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች በመጨመር አገልግሎቱን መጀመሩን አሳታሚው አስታውቋል።

ጃኬን አሳታሚ ኃ/የተ/የግ/ማህበር በተለያዩ ቋንቋዎች አገልግሎት የማስፋፋት ዋና ዓላማ በፍጥነት እያደገ የመጣውን ከተለያዩ ተከታታዮቹ የሚመጡትን ጥያቄዎችን መሠረተ በማድረግ እና ፍላጎቶችን ለማሟላት እንዲሁም ጃኬን ከሚተገብራቸው አጠቃላይ መልሶ የማዋቀር ስራ ውስጥ የአጭር ጊዜ ዕቅዶቹ አንዱ አካል በመሆኑም ጭምር መሆኑንም አሳታሚው ገልጿል።

አዲስ በተሻሻለው ድረ-ገጽ www.addisstandard.com ጃኬን የሚዲያ ውጤቶቹን በአማርኛ እና በአፋን ኦሮሞ ቋንቋዎችን ከነባሩ በበይነ መረብ እና የህትመት መጽሔት ከሚቀርበው የእንግሊዝኛ ቋንቋ አገልግሎት በተጓኝነት አቅርቧል።

በዚህም መሰረት ጃኬን በተጨማሪ የቋንቋ አገልግሎቶት ማስፋፊያው የተለያዩ እለታዊ የዜና ዘገባዎችን፣ የዜና ትንታኔዎችን፣ ጥልቅ ዘገባዎችን እና ዳሰሳዎችን ጨምሮ በሶስቱም ቋንቋዎች አዲስ ስታንዳርድ ስያሜ ለታዳሚዎቹ እንደሚያቅርብም ታውቋል።

የሶስት ቋንቋዎች ድረ ገጽ መከፈትን አስመልክቶ ዋና አዘጋጅ ሲያኔ መኮንን እንደተናገሩት “አዲስ ስታንዳርድ እንደ ገለልተኛ ሚዲያ እንደመሆኑ መጠን ለሀገር ውስጥ ታዳሚያን አዲስ አማራጭ ይሆናል።” ያሉ ሲሆን ጨምረውም “በገለልተኛ ሚዲያ ምህዳር ውስጥ ብዝሃነትን መመልከት አስደሳች ነው። በተለይ በአፋን ኦሮሞ ዘገባ መጀመርን አስመልክቶ በታዳሚዎች በርካታ አበረታች ምላሽ አግኝተናል። ስለዚህ ታዳሚዎች  የሚጠብቁትን ያክል ሆኖ ለመገኘት ጠንክረን እንሰራለን።” ብለዋል።

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ነፃ ሚዲያ ውስብስብ ተግዳሮቶች እንደሚገጥሙት ዋና አዘጋጁዋ አስምረውበት ሆኖም ግን አዲስ ስታንዳርድ የሚገጥሙት ተግዳሮቶች እየጨመሩ ቢሄዱም ታማኙነቱን፣ ሙያዊ የሥነ ምግባር ደንቡን እና በሁሉም ምርቶቹ ላይ ተጨባጭነቱን እንደሚጠብቅ ቃል ገብተዋል።

“በድረ-ገፃችን የቋንቋ ብዝኀነት ለሀገራችን ታዳሚያን ጠቃሚ እና አስፈላጊ የሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የበለጠ ሽፋን ለመስጠት እንጥራለን። የታዳሚዎችን ተሳትፎ በመጨመር በዘገባዎቻችንን ላይ የእውነታዎቻቸው መንፀባረቅ የበለጠ እንደሚጎለብት ተስፋ እናደርጋለን።” በማለት አስተያየታቸውን ሰጠተዋል።

የሶስትዮሽ ቋንቋ ድረ-ገጹን ከመጀመር ጋር ተያይዞ የጃኬን አሳታሚ ድርጅታዊ እሴቶቹን እና ራዕዩን በመልካም ሁኔታ የተመሰረቱ የስነ-ምግባር ደረጃዎቹን ለመጠበቅ እና ለማጠናከር እንዲሁም በሁሉም ስራዎቹ ላይ የጠራ አሰራር እንዲኖር በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የጃኬን ኤዲቶሪያል ፖሊሲ እና መመሪያዎች፣ የጋዜጠኞች መመሪያ እና ዘዬን የሚያካትት በከፍተኛ ጥራት የተዘጋጁ የኤዲቶሪያል ሰነዶች ጥቅልን አዘጋጅቷል።

በተጨማሪም ጃኬን የኤዲቶሪያል ፍልስፍናውን በማህበራዊ ፍትህ ላይ የተመሰረተ ተራማጅ ሚዲያ ማሳየት በቅርቡ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን የኤዲቶሪያል ፍልስፍናውን የሚገልጽ ሰነድ በማዘጋጀት ይፋ ለማድረግ ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል።

የጃኬንን ወቅታዊ መልሶ ማዋቀር እና የሶስት ቋንቋ ድረ-ገጽ መጀመሩን አስመልክቶ አስተያየት የሰጡት የጃኬን ዋና ስራ አስፈፃሚ እና የአዲስ ስታንዳርድ የቀድሞ ዋና አዘጋጅ ፀዳለ ለማ የዜና ክፍል ቡድኑን እንኳን ደስ አላችሁ ያሉ ሲሆን ጨምረውም “የዛሬው የአዲስ ስታንዳርድ ባለሶስት ቋንቋ ድረ ገጽ ስራ በኢትዮጵያ እጅግ ፈታኝ በሆነው የሚዲያ ገጽታ ውስጥ የአንድ አመት ተኩል የረዥም ልፋት ፍሬ ነው። በስራው ላይ ስላሳያችሁት ቁርጠኝነት ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ፤ የስራችውን ውጤት ለማየት በጉጉት እጠባበቃለሁ።” ብለዋል።

ዋና ስራ አስፈፃሚዋ አያይዘውም የጃኬን ታዋቂ ብራንድ አዲስ ስታንዳርድ ህትመት መፅሄት በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት ወደ ታዳሚው ለመመለስ እየተሰራ ነው ብለዋል። አዲስ ስታንዳርድ መፅሄት ህትመት በጥቅምት 2009 ስራ አቁሞ እንደነበር ይታወሳል።

ሌሎች በመሰራት ላይ ከሚገኙት ስራዎች መካከል አዲስ ስታንዳርድ ዩቲዩብ ቻናል ማስተዋወቅን እንደሚጨምርም ጠለቅ ያለ ማብራሪያ ሳይጨምሩ ፀዳለ ፍንጭ ሰተዋል። “በኢትዮጵያ  የሚዲያዉ ዘርፍ ፈታኝ ቢሆንም፣ ጃኬን አሳታሚ በሁሉም ቋንቋዎች ውስጥ ሥነ ምግባራዊ ጋዜጠኝነትን ለማንፀባረቅ ቁርጠኛ ሆኖ ይቀጥላል።” ብለዋል።

አዲስ ስታንዳርድ በኢትዮጵያ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ በእናት ኩባንያው ጃኬን አሳታሚ ኃ.የተ.የግ.ማ ውጤት ሲሆን መቀመጫቸውን ሀገር ውስጥ ካደረጉ ጥቂት ነጻ ሚዲያዎች መካከልም አንዱ ነው።

ጃኬን በየካቲት 2003 ዓም የተመሰረተ ሲሆን በቆራጥነት፣ በተጨባጭ እና በገለልተኛ ጋዜጠኝነት የሚታወቀውን አዲስ ስታንዳርድ ህትመትን ያሰራጫል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.