አዲስ አበባ፡ ሰኔ 17 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ፡- የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊትን (መንግስተ ሸኔ ብሎ የሚጠራውን) የታጠቀ ቡድንን ጨምሮ በሌሎች ህገ-ወጥ ኃይሎች ላይ የሚወሰደው ህግ የማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኦሮሚያና አማራ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳደሮች አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና ዶክተር ይልቃል ከፋለ ተናገሩ፡፡
ይህ በእዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ትናንት ባወጣው መግለጫ በኦሮሚያ ፣ በጋምቤላ ፣በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በደቡብ እንዲሁም በሌሎች ክልሎች ኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈፀመ ያለው ማንነትን መሠረት ያደረገ ግድያ መፈናቀል እና ስቃይ ባስቸኳይ ካልቆመ ኢትዮጵያ ወደለየት የእርስ በርስ መጠፋፋት እንዳያደርሰን ምክር ቤቱን በእጅጉ አሳስቦታል ፣ መፍትሄ መፈለግ አለበት ብሏል።
የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባውን ሰኔ 15 ቀን 2014 ዓ.ም አካሄዷል፡፡ ኮሚቴው በስብሰባው በወቅታዊ አገራዊ የጸጥታ ጉዳይ እና እየተወሰደ ባለው “የሕግ ማስከበር እርምጃ” ላይ የተወያየ ሲሆን ህግ የማስከበሩ እርምጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ ማስቀመጡን ይፋ አድርጓል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ዶክተር ይልቃል ከፋለ፥ የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ የሰጡ ህግ የማስከበር እርምጃ መወሰዳቸውን ገልጸው በተወሰደው እርምጃም የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊትን ጨምሮ “የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ ጥለው በነበሩ በርካታ ህገ-ወጥ ኃይሎች ላይ ህግ የማስከበር እርምጃ ተወስዷል” ብለዋል፡፡ አክለውም የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት “ሸኔ” ከሰሞኑ የጸጥታ ኃይሎች በሌሉባቸው አካባቢዎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ አሰቃቂ ጥቃት መፈጸሙን ጠቅሰዋል።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው፥ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ቡድኑ ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል በሚኖሩ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ያደረሰውን ጥቃት አውግዘው በቡድኑ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ መቀመጡን የገለፁ ሲሆን “አሁን ላይ የጸጥታ ኃይሉ ከህዝብ ጋር በመቀናጀት ቡድኑ ላይ እየወሰደ ባለው እርምጃ እጅግ አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ነው” ብለዋል።
ርዕሳነ መስተዳድሮቹ በየትኛውም ክልል በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈጸም ጥቃት የሁሉም ኢትዮጵያውያን ጉዳይ መሆኑን ያብራሩት ሲሆን ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን ጠብቀው የአገር ጠላት የሆኑ ኃይሎችን በጋራ ሊታገሉ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በቀጣይም የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የተጀመረው ህግ የማስከበር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለፅ ህብረተሰቡ መንግስት እየወሰደ ላለው እርምጃ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
በተያያዘ ዜና ሰሞኑን በዜጎች ላይ የተፈጸሙ ግድያዎችን አስመልክቶ ኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) በሰጠው መግለጫ ምዕራብ ወለጋ ዞን በቶሌ የንጹሃን ጭፍጨፋ ተሳታፊ የሆኑ ኃይሎች በሙሉ በገለልተኛ አካል ተጣርቶ ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግና አጥፊዎችም ሕግ ፊት እንዲቀርቡ ጥሪ አቅርቧል፡፡ ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም በኦሮምያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ አካባቢ በተፈጸመ ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹኃን ዜጎች መገደላቸውንና አብዛኞቹ ሴቶችና ህፃናት እንደሆኑ መረጃዎች ማመላከታቸውን ኦፌኮ የገለፀ ሲሆን ከጥቃቱ የተረፉትን ለማረጋጋትና በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድም እሳስቧል፡፡
ኦፌኮ የንጹሃንን ደም በማፍሰስ ሊገኝ የሚችል ምንም አይነት የፖለቲካ ትርፍም ሆነ ድል ሊኖር እንደማይችል የገለፀ ሲሆን “በኦሮምያ የሚኖሩ የሌላ ብሄር ተወላጆች እንደማንኛውም የክልሉ ነዋሪ ጥበቃና ለሕይወትና ንብረታቸው ሙሉ ዋስትና ማግኘት ይገባቸዋል የሚል ፅኑ እምነት አለን” ብሏል፡፡
በተለያዩ ጊዜያት በሚፈጸሙ ጥቃቶችና የንጹኃን ግድያዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሃገሪቱ እየተካሄደ ያለው ጦርነት ዋና ምክንያት እንደሆነ እንረዳለን ያለው ፓርቲው በፖለቲካ ልዩነት ወደ ጦርነት የገቡ ኃይሎች ልዩነታቸውን በማጥበብ በሰላማዊ መንገድ ችግሮቻቸውን ለመፍታት ሁሉን አቀፍ ድርድር በማድረግ ጦርነት እንዲያቆሙም አሳስቧል፡፡
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በምዕራብ ወለጋ ዞን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለተገደሉበት ጥቃት የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ፈጣን፣ ገለልተኛ እና ጥልቅ ምርመራ እንዲያደርጉ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሼል ባቸሌት ትናንትና አሳሰበዋል
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በበኩሉ በወለጋ በተፈፀመው ግድያ ያመለጡ የአማራ ተወላጆች በየጫካው ሕይወታቸውን ለማትረፍ ተሸሽገው እንደሚገኙ ገልፆ በንጹሃን ዜጎች ላይ በተቀናጀ መልኩ እየተከናወነ ያለ ግድያና ጭፍጨፋ መንግሥት እንዲያስቆም አሳስቧል።
ፓርቲው መላው ሀገር ወዳድ የኦሮሞ ህዝብ በስሙ የሚነግዱ የፖለቲካ ነጋዴዎችን እና ገዳዮችን እንዲያወግዘ፣ የንጹሃን ወንድሞቹ የአማሮች ደም መፍሰስ እንዲቆም፣ የኦሮሞ ምሁራንና፣ በህብረተሰቡ ዘንድ ተሰሚነት ያላቸው ወገኞች ሁሉ ፣ ይህንን በአማራ ወንድሞች ፣ሴቶች እና ህጻናት ወገኖቹ ላይ እየደረሰ ያለውን ኢሰብኣዊ ፍጅት፣ ሌላ የማያባራ የእርስ በርስ ጥላቻና ጦርነት መዘዝ ከመቀስቀሱ በፊት ያውግዙ ሲል በመግለጫው ጥሪ እቅርቧል፡፡
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በምዕራብ ወለጋ ዞን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለተገደሉበት ጥቃት የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ፈጣን፣ ገለልተኛ እና ጥልቅ ምርመራ እንዲያደርጉ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሼል ባቸሌት ትናንትና የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ጽ/ቤት ባወጣው መግለጫ አሳሰበዋል።
ጽ/ቤቱ እማኞችን አነጋግሮ እንደዘገበው ሰኔ 11ቀን 2014 ዓ.ም ከጠዋቱ 3 ሰአት ላይ የታጠቁ ግለሰቦች በብዛት የአማራ ተወላጆች በሚኖሩበት ወደቶሌ መንደር በመዘለቅ እና በዘፈቀደ መተኮስ እንደጀመሩ እና በመቶዎች ከሚቆጠሩ ሰዎች በጥቃቱ መገደላቸውን ጠቅሶ አብዛኞቹ ሴቶች እና ህፃናት መሆናቸውን ዘገባው አመልክቷል። አያይዞም ቢያንስ 2,000 ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች ቤታቸውን ጥለው እንዲሰደዱ መገደዳቸውን አመልክቷል።
“በቶሌ መንደር ላይ በተፈጸመው ጥቃት ትርጉም የለሽ ግድያ እና የአከባቢው ህዝብ በግዳጅ መፈናቀሉ በጣም አሳዝኖኛል” ሲሉ ባችሌት ተናግረዋል። አክለውም “የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በጥቃቱ ላይ በፍጥነት ምርመራ መጀመሩን እንዲያረጋግጡ እና ተጎጂዎች እና ቤተሰቦቻቸው የእውነት፣ የፍትህ እና የካሳ ክፍያ የማግኘት መብት እንዲኖራቸው፣ ጥፋተኞችን ተጠያቂ በማድረግም ጭምር እንዲያረጋግጡ ጥሪዬን አቀርባለሁ” ብለዋል።
በጥቃቱ ወቅት ቁጥራቸው በውል ያልተገለጸ ሰዎች ታፍነው መወሰዳቸው የተዘገበ ሲሆን እስካሁን ያሉበት አይታወቅም። ከፍተኛ ኮሚሽነሩ “የተጠለፉት ነፃነታቸውን መልሰው እንዲያገኙ ባለሥልጣናቱ አስፈላጊውን እና ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስዱ እጠይቃለሁ” ብለዋል ።
በኦሮምያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቅዳሜ ለት በተፈጸመው ጥቃት የሟቾች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ሲሆን ከጥቃቱ የተረፉ የአካባቢው ነዋሪዎች አሁንም ለህይወታችን እንሰጋለን ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል
ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች የተቀሰቀሰው ውጥረትና ብጥብጥ እየጨመረ ባለበት በአሁኑ ወቅት መንግስት በህይወት የመኖር መብትን እንዲያረጋግጥና እንዲጠብቅ ኮሚሽነሯ አሳስበዋል።
ከጥቃቱ ያመለጡ ምን ይላሉ?
በኦሮምያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቅዳሜ ለት በተፈጸመው ጥቃት የሟቾች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ሲሆን ከጥቃቱ የተረፉ የአካባቢው ነዋሪዎች አሁንም ለህይወታችን እንሰጋለን ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።
አዲስ ስታንዳርድ በስልክ ያነጋገራቸው አቶ መንሱር ሱልጣን አሁን ላይ በአካባቢው ስላለው ሁኔታ ሲናገሩ “ህብረተሰቡ አልተረጋጋም ሁላችንም ከፍተኛ ሀዘን እና ስጋት ውስጥ ነን” ብለዋል። በየቀኑ አስክሬን እናገኛለን ያሉት አቶ መንሱር ” ብዙ ሰዎች ጠፍተዋል የት እንደሉ አላወቅንም። ሞተው ይሁን ሸሽተው ግራ ገብቶናል። የሟቾች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል።አላህ ፍርድ ይስጥ ” ሰሉ ተናግረዋል። አክለውም አሁንም ስላለመገደላቸው ምንም ዋስትና እንደሌላቸው በምሬት ተናግረዋ።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት አስተያየት የቅዳሜውን የጊምቢ ወረዳ ጥቃት ጨምሮ ሰሞኑን የተፈጸሙ ጥቃቶች መንግሥት “ሸኔ” በሚለው እና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ በሚጠራው ቡድን መፈጸማቸውን ገልጸው፣ ጥቃቱ በተፈጸመበት ሥፍራ በቡድኑ ላይ ጠንካራ እርምጃ እየተወሰደ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
“ህፃን፣ ሴት፣ አዛውንት ሳይሉ ነው የጨረሱን። ገና 13 አመት የሆነውን የአህቴን ልጅ በጥይት 4 ቦታ መተው ገደሉት” ያሉት የ63 አመት አዛውንት የሆኑት ወ/ሮ ወርቅነሽ ተጫነ አክለውም “በህይወት ዘመኔ አንዲህ ያለ ጭካኔ ኤይቼ አላውቅም። መንግስት ባለበት አገር እንዲህ መሰቃየት በጣም ያሰፍራል። አሁንም መንግስት ካለ ከዚህ ያውጣን። በፍርሀት ነው ያለነው። ነገ ተመልሰው መምጣታቸው ማይቀር ነው ” ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል። አሁን የመንግስት ፀጥታ አካላት በቦታው መኖራቸውን የገለፁት ወይዘሮዋ መቼ ተነስተው እንደሚሄዱ ስለማናውቅ በፍርሃት ውስጥ ነን ሲሉ ተደምጠዋል።
አዲስ ስታንዳርድ ጥቃቱን አስመልክታ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ፣ ቶሌ ቀበሌ ቅዳሜ ሰኔ 11፣ 2014 ዓ.ም በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ260 እስከ 320 እንደሚሆን የተለያዩ የዜና ምንጮች የአካባቢውን ነዋሪዎች እንደ ዋቢ በመጥቀስ መዘገቧ ይታወሳል። አስ