ዜና ትንታኔ፦በምዕራብ ወለጋ በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት የሟቾች ቁጥር መጨመሩ ተገለፀ፣ የአማራ ማህበረሰብ የጥቃቱ ዋና ኢላማዎች ናቸው

በብሩክ አለሙ

ሰኔ 14ቀን፣ 2014 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፦በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ፣ ቶሌ ቀበሌ ቅዳሜ ሰኔ 11፣ 2014 ዓ.ም  በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ260  እስከ 320  እንደሚሆን የተለያዩ የዜና ምንጮች የአካባቢውን ነዋሪዎች እንደ ዋቢ በመጥቀስ እየዘገቡ ነው

ቅዳሜ ሰኔ 11 2014 ዓ.ም በተፈፀመው ጥቃት አብዛኛው ሰለባዎች በክልሉ የሚኖሩ የአማራ ብሄር ተወላጆች መሆናቸውም የተገለፀ ሲሆን ፣ ትናንት ሮይተርስ ያነጋገራቸው አንድ የዓይን ምስክር 260 ሰዎች ተገድለዋል ሲሉ ሲሆን ሌላ ነዋሪ ደግሞ የሟቾቹ ቁጥር 320 ይደርሳል ብለዋል። በመንደሮቹ የተገደሉ ነዋሪዎችን አስከሬን በመሰብሰብ በትናንትናው ዕለት በጅምላ መቀበራቸውን ከጥቃቱ የተረፉ ነዋሪዎች  ደግሞ ለቢቢሲ አማርኛ ገልፀዋል።

ለሚዲያው የናገረው አንዱ ነዋሪ ከጥቃቱ በጉድጓድ ውስጥ ተደብቆ የተረፈ ሲሆን  አራት ወንድሞችና እህቶች እንዲሁም ሦስት የአጎት ልጆች ተገድለውበታል። “እስካሁን አስከሬናቸውን ሰብስበን የቀበርናቸው 260 ሰዎች ናቸው። በእርሻ ቦታ ላይ ነው የቀበርናቸው። በአንድ መቃብር ላይ ከ50 እስከ 60 የሚሆኑ ሰዎችን ደራርበን ነው የቀበርነው” ብሏል።

ሌላኛው ነዋሪ ጥቃቱን የፈጸሙት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት መሆናቸውን ጠቅሷል። “በአማራዎች ላይ የተፈጸመ ጭፍጨፋ ነው” ያለው ግለሰቡ፣ ጫካ ውስጥ ተደብቆ መትረፍ መቻሉንም ሮይተርስ በዘገባው አስነብቧል ።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጥቃቱን በማስመልከት ሰኞ ከሰዓት በኋላ ባወጣው መግለጫ፣ ታጣቂዎቹ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት እንደማይፈጽሙና የጊምቢው ጥቃትም መንግሥት አደራጅቶታል ባለው ኢ-መደበኛ ኃይል የተፈጸመ ነው ብሏል። አክሎም ይህ ክስተት በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ጠይቋል።

ከጥቃቱ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ  “በንጹሃን ዜጎች ላይ በሕገ ወጥ እና በኢ-መደበኛ ኃይሎች የሚደርስ ጥቃት እና መተዳደሪያን ማውደም ተቀባይነት የለውም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቤኒሻንጉል እና ኦሮሚያ ክልሎች፣ ዋና ዓላማቸው ኅብረተሰቡን ማሸበር በሆነ አካላት የተፈጸመው የሰው ልጆችን ሕይወት የሚቀጥፍ ዘግናኝ ድርጊት የምንታገሰው አይደለም፡፡ ጥቃት በደረሰባቸው አካባቢዎች ሰላም እና ደህንነትን መመለስ አሁንም ቅድሚያ የምንሰጠው ተግባራችን ነው” በማለት በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት በትናንትናው ዕለት ሰኔ 13፣ 2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የተፈፀመውን ጥቃት “የሽብር ጥቃት” ሲል የፈረጀው ሲሆን ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖችና ለደረሰው ጉዳት የተሰማውን ሃዘን ገልጿል። መግለጫው አክሎም  መንግሥት ይህንን ጥቃት የፈጸመው ‘ሸኔ’ ብሎ የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መሆኑን ገልፀው “የሕግ የበላይነትን የማስከበር ተልዕኮ ያነጣጠረበት የሸኔ የሽብር ቡድን እየደረሰበት የሚገኘውን ከፍተኛ ሽንፈት ለመሸፈን የጥፋት በትሩን ወደ ንጹሃን አዙሯል” ብሏል።

የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በጥቃቱ  በመስጂዶች የተጠለሉትም ጭምር  ሰለባ ሆነዋል ብሏል

በዚህም በቅርቡ በጋምቤላ በደምቢዶሎና በጊምቢ ከተሞች ላይ ጥቃቶች መሰንዘሩንና ይህም ጥቃት በመክሸፉ በጊምቢ ወረዳ ላይ የበቀል ጥቃት መፈጸሙን ገልጿል። የመንግሥት ኮሚዪኒኬሽን መግለጫ የሞቱ ሰዎችን ቁጥር ባይጠቅስም የበርካታ ንጹሃን ሕይወት በግፍ ተቀጥፏል እንዲሁም ንብረትም ወድሟል ሲል የገለፀ ሲሆን አክሎም “የጥፋት ኃይሉ ሙሉ በሙሉ እንዲደመሰስ በመላው የክልልና የፌደራል የጸጥታ ኃይሎች የተጀመረው የተቀናጀ ተልዕኮ ተጠናክሮ ይቀጥላል” ብሏል።

የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በቶሌ አጎራባች ቀበሌ ብሔርንና ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ የጅምላ ግድያ መድረሱን የገለፀ ሲሆን  በጥቃቱም  በመስጂዶች የተጠለሉትም ጭምር  ሰለባ ሆነዋል ብሏል። በአሁኑ ወቅት ለሕይወታቸው ፈርተው የሚገኙ ዜጎችም መንግሥት በአስቸኳይ ከለላ እንዲያደርግላቸው እንዲሁም መንግሥት በተደጋጋሚ የሚደርሰውን ጥቃት እንዲያስቆምና ወንጀሉን የፈጸሙ አካላት ወደ ፍርድ እንዲቀርቡ መደረግ አለበት በማለት አሳስቧል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በበኩሉ በተለያየ ጊዜ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ጭፍጨፋ እንደ ተፈጥሯዊ እና መደበኛ ክስተት እየተወሰደ ሲል መግለጫ የወጣ ሲሆን  በባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት መዋቅራዊ እና ሥርዓታዊ በሆነ መንገድ በአማራ ሕዝብ ላይ ግድያ፣ መፈናቀል፣ ሃብት እና ንብረቱን ማውደም እና መንጠቅ ሲፈጸም ቆይቷል ብሏል።

በአሁኑም ወቅት በተለይ በኦሮሚያ እና በቤንሻንጉል ክልሎች በተከታታይ መጠነ ሰፊ ጭፍጨፋ ደርሷል ያለው አብን እነዚህንም ጥቃቶች “የዘር ማፅዳት ወንጀል ናቸው” ሲል ፈርጇቸዋል።

“መንግሥት ተደጋጋሚ ጥቃት በሚፈጸምባቸው አካባቢዎች ዜጎችን ከጥቃት ለመከላከል የሚያስችል አቅም የሌለው ከሆነ ደግሞ ፣ ችግሩን አምኖ ሊቀበል እና ለጥቃት ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎችን በማደራጀት ፣ በማስታጠቅ እና አመራር በመስጠት ራሳቸውን እንዲከላከሉ የሚያስችል አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር ይጠበቅበታል።” ብሏል በመግለጫው።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)ም በተለያዩ አካባቢዎች በዜጎች ላይ እየደረሱ ያሉ ጭፍጨፋዎችን በማውገዝ በትናንትናው ዕለት መግለጫ አውጥቷል። በመግለጫውም የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ መሆኑን ገልፆ በዚህ ወቅት መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ሥራውን በጥንቃቄ እንዲሰራ ጠይቋል። በተጨማሪም በዜጎች ሕይወት ላይ እንዲህ አይነት ጥቃት የሚፈጽሙ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ መንግሥት ሊወስድ ይገባል ሲልም አሳስቧል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በብሔር ላይ ያተኮረ ግድያ በቅርብ አመታት ውስጥ ባይጀመርም ባለፉት አራት አመታት በሰላማዊ ዜጎች ላይ የደረሰውን ያህል ግፍ እንዳልታየ በመጥቀስ ደግሞ መግለጫ ያወጣው እናት ፓርቲ ነው። በባለፉት ጥቂት ቀናት በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የደረሱ ጭፍጨፋዎች አገሪቱ ያንዣበባት ትልቅ አደጋ ማሳያ ነው ያለው እናት ፓርቲ ብሔራዊ የሃዘን ቀን ሊታወጅ ይገባል ብሏል። 

የጥቃቱ ሰለባዎች የድረሱልን ጥሪ በክልል አስተዳደሮች ችላ ተብሏል ያለው ፓርቲው፣ እነዚህ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ አካላት ከሥልጣናቸው እንዲነሱና ተጠያቂም እንዲደረጉ የጠየቀ ሲሆን አክሎም “መንግሥት እንዲህ ያሉ ዘር ተኮር ፍጅቶች በአገራችን እየተፈጸሙ መሆናቸውን አምኖ መከላከል ካልቻለ እገዛ ለሚያደርጉ ዓለም አቀፍ አካላት ጥሪ ያድርግ” ሲል አሳስቧል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.