ዜና ትንታኔ፡የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ተፅዕኖ እያሳደረብን ነው ሲሉ የትራንሰፖርት ተጠቃሚዎችና የታክሲ አሽከርካሪዎች ተናገሩ

ፎቶ ምንጭ: ኢዜአ

በብሩክ አለሙ

ሰኔ 20፣ 2014 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፦የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ተፅዕኖ እያሳደረባቸው መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የትራንሰፖርት ተጠቃሚዎችና የታክሲ አሽከርካሪዎች  ለአዲስ ስታንዳርድ ገለፁ፡፡

የተለያዩ አለም አቀፍ ዝገባዎች እና የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች እንደተናገሩት በሩሲያ እና በዩክሬን ጦርነት ምክንያት የነዳጅ ዋጋ  በእጅጉ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በዚህም የተነሳ የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ እስከ 140 ዶላር መሸጥ ደርሶ ነበር፡፡ ይህም ከፈረንጆቹ 2008 አጋማሽ ጀምሮ ከፍተኛ ጭማሪ እንደሆነም  ይታወቃል፡፡ ታድያ ይህ የአለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ጭማሬ በጦርነት፣ በድርቅና በመሳሳሉት ምክንያቶች አቅሟ የተዳከመው ኢትዮጵያ ከባድ አጣብቂኝ ውስጥ ከቷቷል፡፡

በአለም አቀፍ ደረጃ በተደረገው የነዳጅ ዋጋ ጭማሬ ምክንያት የኢትዮጽያ መንግስት ከወር በፊት የነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሬ አድርጓል፡፡ በተደረገው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ የተነሳ በታክሲዎች ላይ  ከ50 ሳንቲም እስከ 3 ብር ከ50 ሳንቲም ጭማሪ ስለመደረጉ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ገልጿል። መንግስት የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያውን ተከትሎ በእቃዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ በመግለፅ ቢያስጠነቅቅም ለአዲስ ስታንደርድ ሃሳባቸውን ያካፈሉ የከተማዋ ነዋሪዎች  ግን  የዋጋው ጭማሬ መኖሩንና የኑሮ ውድነቱ ጭራሹኑ ማየሉን ገልፀዋል፡፡ አክለውም በትራንፖርት ላይም ለከፋ እንግልት መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

መንግስት በነዳጅ ላይ የዋጋ ጭማሪ ባደረገበት ማግስት ነጋዴውና የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭዎች በህበተሰቡ ላይ የራሳቸውን ጭማሬ ሲያደረጉ መቆየታቸውን አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገረቻቸው የተለያዩ የመዲናይቱ የማህበረሰብ ክፍሎች ተናግረዋል፡፡ ይህም ድርጊት ቀድሞውኑ ለህዝቡ ከባድ የነበረውን የኑሮ ውድነት ይባስ እንዲያሻቅብ ማድረጉንም አክለው ገልፀዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ በአገር አቀፍ ደረጃ እየጨመረ የመጣውን የነዳጅ ጭማሪ ምክንያት በማድረግ ቢሮው በጥናት ላይ ተመርኩዞ ከሰኔ 01 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ የሚዲ-ባስና ሚኒ-ባስ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎችን የታሪፍ ማሻሻያ አድርጓል፡፡

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ከታሪፍ ማስተካከያ በላይ ክፍያ የሚጠይቁ አገልግሎት ሰጭዎች  ህግን ተላለፈው በሚገኙ አሽከርካሪዎች ላይ ጥብቅ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ቢገልጽም የነዳጅ ዋጋ መጨመርን ተከትሎ የትራንፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎች ያልተገባ የታሪፍ ጭማሪ እንደሚያደርጉና ህጉ እየተተገበረ አለመሆኑን አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገራቸው የትራንስፖርት ተጠቃሚዎች ያስረዳሉ፡፡ መንግሰት ያደረገው ማሻሻያያም  ትልቅ ተፅእኖ አያደረሰብን ነው ሲሉ በመዲናዋ አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገረቻቸው  የትራንፖርት ተጠቃሚዎች አክለው ገልፀዋል፡፡

 የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ምን ይላሉ?

ሰማ መንግስቱ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ሲሆን የነዳጅ ጭማሬው ያስከተለውን ተፅዕኖ አስመልክቶ “የነዳጅ ዋጋ ጭማሬን ተከትሎ የኑሮ ውድነት ስለጨመረ ታክሲ ይጠቀም የነበረ ሰው ሳይወድ በግዱ  ሸገርና አንበሳ የከተማ አዉቶቢስ ለመጠቀም ተገዷል፡፡ ቀድሞውኑ የነበሩ አውቶብሶች በቂ ያልነበሩ ሲሆን አሁን ደግሞ ታክሲዎች የታሪፍ ጭምሬ በማድረጋቸው የትራንስፖርት ተጠቃሚው ክፍያው ወደሚቀንሰው የከተማ አውቶብስ መጠቀም በመጀመሩ ረጃጃም ሰልፎች እየታዩ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የአውቶብስ እጥረት በማስከተሉ ህብረተሰቡ ጊዜውን በአግባቡ ተጠቅሞ በስራው ላይ ውጤታማ እንዳይሆን እያደረገ ይገኛል፣” ያለ ሲሆን አክሎም “ታክሲዎችም የተደረገውን የታሪፍ ማሻሻያ ምክንያት በማድረግ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሬ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ ከመገናኛ ቦሌ አራብሳ መሸት ሲል ጠብቀው የ15 ብር ታሪፍን  እስከ 30 ብር እያስከፈሉ ነው” በማለት ያለውን ሁኔታ ካስረዳ በኋላ የነዳጅ ጭማሬው በነዋሪው ላይ ትልቅ ተፅእኖ መፍጠሩን ካለው የሸቀጦች ሽመታ ጋር አያይዞ ሰማ  “እቃ ለመግዛት ስትሄድ ሻጩ ነዳጅ ስለጨመረ እቃ የሚያመጡልን ተሸከርካሪዎች ጭማሬ በማድረጋቸው እኛም ጨምረናል ይሉሃል፡፡ ነዋሪው በሚጠቀመው ትራንሰፖርትና በሸቀጦች ላይ ተገቢ ያልሆነ ክፍያን ለመክፈል እየተገደደ ነው “ ሲል ያስረዳል፡፡

“የትርንስፖርት ስራ አዋጫ ሆኖ ሳይሆን አማራጭ ስላጣን ብቻ የምንሰራው ስራ ሆኗል፡፡ ሰርተን የምናገኘው ለመኪናው  እንጂ ለእኛ ምንም የሚተርፈን የለም፡፡ በዚህም የተነሳ የኑሮ ውድነቱን መቋቋም አቅቶናል፡፡ የቤት ኪራይ መክፈልና ቤተሰባችንን ማስተዳደር አልቻልንም”

ሄኖክ ሞገስ ሌላኛው የመዲናዋ ነዋሪ ሲሆኑ “የነዳጅ ጭማሬው በትራንስፖርት ከክፍለ ሀገር የሚመጡ እቃዎች ላይ የዋጋ ጭማሪን አስከትሏል፡፡ ይህ ደግሞ ህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ የኑሮ ውድነትን አምጥቷል፡፡ ከክፍለሃገር የሚመጡ የምግብ እቃዎች ላይ አሽከርካሪዎች ነዳጅ  ጨምሯል በሚል ምክንያት ዋጋ በመጨመራቸው ነጋዴዎችም ህብረተሰቡ ላይ የዋጋ ጭማሪ አደርገዋል“ በማለት ያስከተለውን ተፅእኖ ለዘጋቢያችን ገልጿል፡፡

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ቁምነገር እሸቱ ለአዲስ ስታንዳርድ በተደረገው ነዳጅ ዋጋ ጭማሪ የተነሳ የዋጋ ላይ ግሽበት እንዳይከሰት ከሶስት ወር በፊት የሚቆጣጠር ግብረ-ሀይል ተቋቁሞ ቁጥጥር ለማድረግ ወደ ስራ እንዲገባ መደረጉን ገልፀዋል፡፡   

የነዳጅ ጭማሬ የታክሲ አሽከርካሪዎች ላይ ምን አስከተለ?

አዲስ ስታንዳርድ አዲስ አበባ ከተማ መገናኛ አከባቢ ተገኝታ  የታክሲ ሹፌሮችን ያነጋገረች ሲሆን መንግስት በነዳጅ ላይ የዋጋ ጭማሬ ማድረጉን እንጂ ባለ ታክሲዎች ላይ የሚመጣውን ተፅዕኖ ከግንዛቤ ውስጥ አላስገባም ሲሉ ይናገራሉ፡፡ “የነዳጅ ጭማሬውን ምክንያት በማድረግ የመኪና መለዋወጫ እቃዎች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሬ ተደርጎብናል፡፡ ጉዳዩ የሚመለከተው አካል መፍትሄ ሊሰጠን ይገባል” ሲሉ በምሬት አክለው ገጸውልናል፡፡

አቶ ታደለ ወ/ሚካኤል የታክሲ ባለቤትና አሽከርካሪ ሲሆኑ ከመገናኛ አያት ባለው መስመር  ላይ የታክሲ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ ቀርበን ባነጋገርናቸው ወቅትም “የነዳጅ ዋጋ ጭማሬ ባለ ታክሲዎች ላይ ተፅዕኖ አድርጎብናል” ሲሉ ገልፀውልናል፡፡ አቶ ታደለ አክለው ስለ ጉዳዩ ሲያስረዱም “የመለዋወጫ እቃዎችን መግዛት አቅቶናል፡፡ ነዳጅ ስለጨመረና ታሪፍ ማሻሻያ ስለተደረገ የመለዋወጫ እቃ ሻጮች ዋጋ እየጨመሩብን ይገኛሉ፡፡ ቀድሞ ከነበረው  የተደረገው ማሻሻያ ከ 50 ሳንቲም እስከ 2 ብር ብቻ ነው፡፡ ይቺ ተጨመረች ብለው እንደ ሞተር ዘይት፣ ፊልትሮ፣ ጎማ፣ ቺንጋና የመሳሰሉት እቃዎች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሬ እድርገውብናል” ብለዋል፡፡

በምሳሌ ሲያስረዱም “የሞተር ዘይት ከዚህ ቀደም 800 ብር ይሸጥ የነበረ ሲሆን አሁን ግን 1800 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ ለ15 ቀን ብቻ የሚያገለግለን ፊልትሮ እንኳ 150 ብር ነበር የምንገዘው አሁን ግን 250 ብር ገብቷል፡፡ አንዱ የታክሲ ጎማ 3000 ብር የነበረ ሲሆን  አሁን ግን 8000 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ የታክሲ ስራ አማራጭ ስታጣ የምተሰራው ስራ ሆኗል፡፡ ምንም ውጤጥ አይገኝበትም፡፡ የታክሲ ትራንስፖርት ላይ ያለውን ችግር ያወቀለት የለም፡፡ መንግስት እኛ ያለንበትን አጣብቂኝ አልተረዳልንም፡፡ የታክሲ ተጠቃሚዎችም አንድና ሁለት  ብር መጨመሩን ነው የሚያዩት እንጂ እኛ ጋር ያለውን ችግር አልተረዱልንም” በማለት ስለ ችግሩ አብራርተውልናል፡፡

ሌላኛው አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገረቻቸው ተስፋዬ ታምራት የተባለ የታክሲ ሹፌር  የተጨመረው የነዳጅ ወጋና የታሪፍ ማሻሻያው ከታክሲዎች ገቢ ጋር  ተመጣጣኝ አለመሆኑን ያስረዳል፡፡ “የተጨመረው የነዳጅ ዋጋ በመለዋወጫ እቃዎች (spare parts) ላይ ከፍተኛ ዋጋ እንዲጨምር አድርጓል” በማለት የሌሎች የታክሲ አገልግሎት ሰጪ ሹፌሮች ያነሱትን ሃሳብ አረጋግጦልናል፡፡ በምሳሌ ሲያስረዳም  ፍሬን ሸራ  400 ብር የነበር ሲሆን አሁን ግን 830 ብር እየተሸጠ መሆንን ጠቅሷል፡፡ “ካቅማችን በላይ ሆኗል” በማለት ሃሳቡን የገለጸው ይህ ሹፌር ቁጥጥር ሊደረግበት ያልቻለና መንግስት ሃይ ሊለው የሚገባው ቦታ የመለዋወጫ እቃዎች ሻጮች አንዱ ነው ሲልም አክሏል፡፡ በዚህም የተነሳ እንዳንድ ባለ ታክሲዎች ከተቆጣጣሪዎች ጋር በመስማማት መንግስት ባስቀመጠው ታሪፍ ላይ ጭማሬ በማድረግ እየሰሩ የገኛሉ፡፡ ይህን የሚያደርጉት ደግሞ የመለዋወጫ እቃ መግዛጥ ስላልቻሉ መሆኑን ያስረዳል፡፡

“የትርንስፖርት ስራ አዋጫ ሆኖ ሳይሆን አማራጭ ስላጣን ብቻ የምንሰራው ስራ ሆኗል፡፡ ሰርተን የምናገኘው ለመኪናው  እንጂ ለእኛ ምንም የሚተርፈን የለም፡፡ በዚህም የተነሳ የኑሮ ውድነቱን መቋቋም አቅቶናል፡፡ የቤት ኪራይ መክፈልና ቤተሰባችንን ማስተዳደር አልቻልንም” ሲል ይህ የታክሲ አሽከርካሪ አክሎ ገልጿል፡፡

አሽከርካሪ መሳይ ዘመዱ በበኩሉ የተጨመረው የነዳጅ ዋጋና ታሪፉ ተመጣጣኝ  አለመሆኑን ገልጾ ተግባራዊ ይደረጋል የተባለው የነዳጀ ድጎማው ቀርቶ የመለዋወጫ እቃዎች ዋጋ ላይ መንግስት ማስተካከያ ቢያደረግ መልካም ነው ሲል ሃሳቡን አካፍሎናል፡፡

የሸገር ባስ ድጋፍ ሰጪ አውቶብሶች መመናመንና ያስከተለው ተፅዕኖ

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ  ሀገር አቋራጭ አውቶብሶችን ከግል አገልግሎት ሰጪ ማህበራት ጋር ስምምነት በማድረግ  “ሸገር ድጋፍ ሰጪ” በሚል ሰይሞ  ከ 400 በላይ አውቶብሶችን የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ አድርጓል፡፡ እነዚህም አውቶብሶች ወደ ስራ ከገቡ በኋላ በትራንሰፖርቱ ላይ የሚታየውን ችግር ማቃለል ችለዋል፡፡ ይሁንና አሁን ላይ እነዚህ አውቶብሶች ቁጥራቸው ተመናምኖ የትራንስፖርት ተጠቃሚው ለእንግልት እየተዳረገ ይገኛል፡፡ ሸገር ድጋፍ ሰጪ አውቶብሶች ስራቸውን እያቋረጡ ባሉበት ወቅት በታክሲዎች ላይ በተደረገው የታሪፍ ጭማሬ የተነሳ  የታክሲ ተጠቃሚዎች የህዝብ ትራንስፖርት መጠቀም በመጀመራቸው የትራነስፖርት እጥረት እንዲፈጠርና ተጠቃሚው ላላስፈላጊ እንግልት እንዲዳረግ አድርጎታል፡፡

በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች የኢዜአ ጋዜጠኛ ያነጋገራቸው የትራንስፖርት ተገልጋዮች የትራንስፖርት ችግር ተንቀሳቅሶ ሰርቶ ለመብላት፤ ወጥቶ ለመግባት ፈታኝ ሆኖብናል ብለዋል። በታክሲ አገልግሎት ሰጭዎች ህገ ወጥ ተግባር ለእንግልትና ያልተገባ ክፍያ እየተዳረጉ መሆኑን ተናግረው በተለይም በስራ መግቢያና መውጫ ሰዓት የትራንስፖርት አገልግሎት ማግኘት ፈታኝ እየሆነ መምጠቱንም ገልጸዋል። ለዚህም እንደኛው ምክንያት ሸገር ድጋፍ ሰጪ አውቶብሶች ስራቸውን እያቋረጡ መሆናቸውን እንስተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር እፀገነት አበበ በከተማዋ የትራንስፖርት አቅርቦትና ፍላጎትን ለማጣጣም የሸገር ድጋፍ ሰጪዎችን በኪራይ ውል አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረጉን  ገልጸው  ሆኖም ከአገልግሎት መስጫ ታሪፍና ከክፍያ ጋር የተያያዘ ጥያቄ በማቅረባቸው ከግንቦት 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ የተወሰኑት አገልግሎት መስጠት ማቋረጣቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል። በመሆኑም ያቀረቧቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ቢሮው በጥናት ላይ የተመሰረተ መፍትሄ ለመስጠት በመስራት ላይ  መሆኑን አክለው ገልፀዋል።

የነዳጅ አቅራቦዎች፣ የንግድ ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ትራንስፖረት ቢሮ፣ ከተማ መስተዳድር የህዝብ ግኑኝነት ሃላፊን በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.