ዜና ትንታኔ፡ በኮንደሚኒየም ቤቶች ላይ የወጣው አዲስ የግብር ተመን የህዝቡን አቅም ያላገናዘበ፣ የህግ ክፍተት ያለበት እና ማህበራዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል የህግ ሙሁራንና የቤት ባለንብረቶች ገለጹ 

በሞላ ምትኩ @MollaAyenew

አዲስ አበባ፣ ሰኔ፣ 26/2015 ዓ.ም፡- በአዲሰ አበባ ከተማ  አስተዳደር ገቢዎቸ ቢሮ የተላለፈውና  በትግበራ ላይ ያልው የቤት ጣራና ግድግዳ  ግብር  አዲስ የክፊያ ተመን በአሁኑ  ወቅት  ያለውን ነባራዊ ሁኔታን  ያላገናዘበ እና አሁን  ያለውን  የኑሮ ውድነት በህዝቡ ላይ የፈጠረውን  አሉታዊ ጫና በከፋ ደረጃ የሚያባብስ ከመሆኑም በላይ የህግ ክፍተት እንዳለበት በጋራ መኖሪያ ህንጻዎች የቤቶች  ባለንብረቶች  እና የህግ ሙሁራን ተናገሩ። 

በአቃቂ ቃሊቲ ከፍለ ከተማ በቂሊንጦ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ባለንብረቶች ለአዲስ ስታንዳርድ አንደገለጹት የከተማ አስተዳደሩ ህዝቡ በአስጭናቂ የኑሮ ሁኔታ ላይ እንዳለ እያወቀ አንዳንድ ማስተካከያዎች ቀድመን አንዳናደርግ አስቀድሞ ሳያሳውቀን  ድንገተኛ  የግብር ክፍያ  አስገዳጅ ማምጣቱ  አግባብነት የለውም ይላሉ።

በቂሊንጦ ሳይት ዳርፉር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የባለ አንድ ምኝታ ኮንደሚንየም ባለንብረት የሆነች ስሟ እንዳይገለጥ የጠየቀች  እናት በወሩ ከሚታገኘው የተጣራ 4000 ብር ወርሃዊ ክፊያ  2000  ብሩን  በየወሩ ለባንክ እዳዋን  ትከፍላለች። የቀራትን  ገንዘብ ደግሞ ከዘመድ አልፎ አልፎ የሚደረግላትን ችሮታ ጋር በማድረግ  ልጆቿን  ጾም እንዳያድሩ ትጠቀማለች።

“ባለቤቴ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ አራት ዓመታት ሆኗል። ያለአጋዥ ሁለት  ልጆቼን እያስተዳደርኩ ያለሁት በዚችው የወር ደሞዝ ነው። አሁን ድንገተኛ ክፍያ ሲመጣብኝ በጣም ነው የተጨነቅኩት” ያለችው ባለንብረቷ ” አሁን የመጣው የቤት ግብር መክፈል አልቻልኩም  እንደዚህ አይነት አስገዳጅ ነገር ይመጣል ብየ ባላሰብኩበት ሰዓት በመምጣቱ ለከፋ ሁኔታ ዳርጎኛል”  ትላለች።

ነዋሪዋ አያይዛም ከእኔ በእጅጉ ያነሱ የባሰ  ኑሮ የሚኖሩ በርካታ ሰዎች እየተጠየቀ ያውን ግብር መክፈል ይቅርና ጭራስ የእለት ጉርስ የማያገኙ አንድ ቀን በልተው ሁለት ቀን ምንም ሳይቀምሱ የሚኖሩ በርካቶች ናቸው ስትል ገልፃለች።

“መጀመሪያውኑ 10/90 እና 20/80 ኮንደሚኒየም ስንመዘገብ አላማው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በረጅም ግዜ በሚከፈል ብድር የቤት ባለቤት ማድረግ ነበር። በእቅዱ መሰረትም እጣ የወጣልን ቤት አግኝተን እየኖርንበት ነው። አሁን  የባንክ እዳችንን ከፍለን ሳንጨርስ እንደዚህ አይነት አስገዳጅ ነገር መምጣቱ አሳዛኝ ነው” የሚለው ደግሞ ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ ሌላ የቤት ባለንብረት ነው።

ግለሰቡ አያይዞም “ግብር መክፈል ተገቢ ቢሆንም አሁን ወቅቱ አይደለም በባንክ እዳ ተይዞ ያለን ቤት ግብር ክፈሉ ብሎ ማስገደድ ትክክል አይደለም፤  ለህዝብ አስባለሁ ከሚል መንግስት እንደዚህ አይነት ህዝብን የሚያስጨንቅ እርምጃ  አይጠበቅም” ይላል።

ነዋሪው አያይዞም “እኔ የሚኖረው አቃቂ ውስጥ ሌላ ቤት ተከራይቸ ነው። ይህ ያደረግኩት የባንኩን እዳ መክፈል ባለመቻሌ ነው። ቤቴን በ8000 ብር አከራይቸ እኔ ደግሞ አፈር ቤት በ6000 ብር ተከራይቼ ነው ለባንክ እየከፈልኩ ያለሁት። ይህ የማደርገው የሚተዳደረው በጥበቃ ስራ ስለሆነ የማገኘው ወርሃዊ ደሞዝ ስለማይበቃኝ ነው” ይላል።

አስተያየታቸው ለአዲስ ስታንዳርድ  የሰጡ የቤት ባለንብረቶች የሚስማሙበት አንኳር ነገር  የከተማ አስተዳደሩ የቦታ ኪራይና  የቤት ግብር ክፊያ እንዲሁም ለኮንደሚኒየም ቤቶች  ያወጣው ተመን  የተጋነነ ነው ይላሉ።

ባለንብረቶቹ አያይዘውም  አስተዳደሩ  ኮንደሚኒየም ቤት ያላቸው ነዋሪዎች ምን አይነት ገቢ እንዳላቸው በቂ ጥናት ሳያደረግ ከአቅም በላይ ክፊያ እንዲንከፍል እያስገደደን ነው ይላሉ።   

ስማቸው ለደህንነት ሲባል አንዳይገለጥ የጠየቁ ሌላ ነዋሪ “በልተን ማደር ካልቻልን ስለ መንገድ ልማት እንዴት ማሰብ ይቻላል?” ሲሉ ይጠይቃሉ።

አያይዘውም ይህ “ጋሪውን ከፈረሱ ማስቀደም ነው”  በጋራ መኖሪያ ቤት እጣ ደርሷቸው የቤት ባለቤት የሆኑ በርካታ   ጡረተኞች፣ ጧሪ የሌላቸው አረጋዊያንና ሌሎች መክፈል የማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ስላሉ መንግስት በአጽንኦት ሊያስብበት ይገባል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ባዘጋጀው መድረክ ተገኝተው በአዲሱ የቦታ ኪራይና ግብር አተማመን ፍትሃዊነት ማብራሪያ የሰጡት  የአዲስ አበባ አስተዳደር  የገቢዎች ቢሮ ሃላፊ አቶ አደም ኑር  በበኩላቸው በአገራችን እንደዚህ ዓይነቱን ግብር  መሰብሰብ የተጀመረው አሁን ሳይሆን  ከ1937 ዓ.ም.  ጀምሮ   በቦታ ኪራይ እና ቤት ግብር አዋጅ ቁጥር 80/1968 መሰረት እያንዳንዱ ቤት በሚኖረው ዓመታዊ የቤት ኪራይ ግምት መሰረት   እየተከፈለ እንደነበር ገልጸው አሁን አዲስ የተጨመረው የኮንደምኒየም ቤቶች መሆኑን ገልጸዋል።

ሃላፊው አያይዘውም አሁን የሚሰበሰበው  ዓመታዊ የቦታ ኪራና የቤት ግብር  ሌላ መሰረተ ልማትን ለመገንባት ይቅርና ግብሩን ለመሰብሰብ  የሚወጣውን  ወጪ የማይሸፍን እጅግ ዝቅተኛ፣ ሳይሻሻልም ለረጅም ዓመታት የቆየ፣ ከግዜው ጋር መዘመን የማይታይበት መሆኑን በመገንዘብ የዓመታዊ ኪራይ ዋጋ ተመን ወቅታዊ መደረጉ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋ።

 ከዚህ  ጋር በተያያዘ አንዳንድ አከራዮች በተከራዮች ላይ የዋጋ ጭማሪ እያደረጉ መሆኑን  በተደረገ  ክትትል ደርሰንበታል  ለዚህም የከተማ አስተዳደሩ የካቲት 30 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው ውይይት ማንኛውም አከራይ  እስከ ሰኔ 30  ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ  የቤት ኪራይ እንዳይጨምር  ውሳኔ ማስተላለፉን ተናግረዋ::

መንግስት የግብር ከፋዩን ጫና ለመቀነስ በማሰብም ግለሰቦች መክፈል ከነበረባቸው 50 በመቶ ብቻ እንዲከፍሉ  ድርጅቶች ደግሞ 75 በመቶ መደረጉ ህዝብ ላይ ያለውን የኑሮ ጫና በመገንዘብ   መሆኑን  ሃላፊው  ጠቁመዋል፡፡  

በአዲስ ቻምበር የግልግል ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት አቶ  ዮሃንስ ወልደገብርኤል  ግን በዚህ ሃሳብ አይስማሙም። የቦታ ኪራይ እና ቤት ግብር አዋጅ ቁጥር 80/1968 መሰረት ያደረገ ተመን መደረጉ  ከፍተኛ   ክፍተት ያመጣል ይላሉ።

“አዋጁ በወጣበት ወቅት በአገሪቱ የነበረው ነባራዊ ሁኔታ አሁን ካለው  አውድ ጋር  ፈጽሞ የተለየ  በመሆኑ የከተማ  አስተዳደሩ የህግ ስህተት እየፈጸመ ነው” ሲሉ  ይሞግታሉ።

አያይዘውም አዋጁ የወጣው በደርግ አስተዳደር ዘመን ሲሆን በወቅቱ የነበረው ብቸኛ የቤቶ አከራይ ራሱ መንግስት ስለነበር  እና ግለሰቦች ከሚኖሩበት ቤት ውጭ የሚያከራዩት     ቤት ስለማይፈቀድ በተከራዩ  ህብረተሰብ  ላይ የተፈጠረ ምንም ዓይነት  ማህበራዊ ቀውስ አልነበረም ያሉት የህግ ሙሁሩ  በአሁኑ  ወቅት ግን አከራዮች  ግለሰቦች በመሆናቸው እንዲከፍሉ የተተመነባቸውን ገንዘብ ወደ ተከራይ ስለሚያወርዱት የሚፈጠረው ማህበራዊ ቀውስ ቀላል አይሆንም ይላሉ።   

“የከተማ አስተዳደሩ ህጉ ሳይሻሽል እንደዚህ ዓይነት ተመን መተመኑና በአስገዳጅና በአጣዳፊ  እንዲከፈል ማዘዙ ከህግ አንጻር አግባብነት የለውም”  ብለዋል

የኮርፖሬት ኮንሳልታት የህግ  ሙሁሩ አቶ የሁላሸት ታምሩም  በበኩላቸው ለአዲስ ስታንዳርድ በአከራይና ተከራይ መካከል ጣልቃ በመግባት በቤት ኪራይ መናር ምክንያት በማህበረሰቡ ሊፈጠር የሚችለውን ቀውስ ማቃለል አይቻልም ይላሉ።

“በነጻ የገበያ ስርዓት የቤት ባለቤቶችን ራይ እንዳትጨምር ተከራይ እንዳታስወጣ ማለትም ሌላ በመንግስት ሊፈጸም የማይገባው   ስህተት ነው፤ እንደዚህ ዓይነቱ ጉዳይ በአከራይና በተከራይ መካከል የሚፈጸም ውል እንጂ መንግስት ወርዶ  ጣልቃ እየገባ የሚወስነው አይደለም” ይላሉ።

አቶ ያሬድ ሀይለመስቀል የዋይ ኤች ኤም ኢንቬስትመንት ኮንሰልቲንግ ኋላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መስራችና ስራ አስኪያጅ  ናቸው።  በዚሁ መድረክ ተገኝተው “የከተማ አስተዳደሩ እየተከተለ ያለው መንገድ አግባብነት  የሌለው፣ ግራ የሚያጋባ  እና ማህበራዊ ቀውስን የሚያመጣ ነው”  ሲሉ ይሞግታሉ።

አሁን ያለው ጉዳይ ከገንዘብ እጥረት ጋር የተያያዘ ሆኖ  ከፖሊሲ ችግር የሚመነጭ  ነው የሚሉት አቶ ያሬድ ከዓለም ባንክ ጋር መንግስ የገባው  ስምምነት  አገሪቱን ወዳልተፈለገ ችግር እየከተታት ነው ብለዋል ያምናሉ።

ከፍተኛ የቤት እጥረት ባለበት ሁኔታ እንደዚህ ዓይነት ህግን መሰረት ያላደረገ የክፊያ ተመን አውጥቶ ህዝብን ማስጨነቅ አግባብነት የለውም ያሉት አቶ ያሬድ በተለይ በኮንደሚኒየም ቤቶች ጡረታ የወጡ መምህራን፣ ወታደሮች፣ እና ሌሎች የመንግስት ሰራተኞች እንደዚሁም በቂ መተዳደሪያ የሌላቸው ዜጎች ይገኙበታል  በመሆኑም አሁን የተላለፈው የግብር ተመን የህዝቡን አቅም ያገናዘበ አይደለም ብለዋል።

አቶ ያሬድ አያይዘውም “አንድ ሰው ከደሞዝ 35 በመቶ ታክስ ይከፍላል፣ በንግድ ቤት ታክስ ይከፍላል፣ የአከራይ ታክስ ይከፍላል፣ እንደዚሁም የቤት ታክስ ይከፍላል  ይህ ሁኔታ ሰላምን የሚነሳ አሰልቺ ነገር ነው” ይላሉ። 

ይህ የቤት ግብር በመርህ ደረጃ ምንም አይነት ችግር ላይኖረው ይችላል በተጨባጭ ሲታይ ግን በአገራችን ቤት ሰዎች በህይወት ዘመናቸው ሰርተው የሚያገኙት ንብረት ነው ግብር መክፈል ባለመቻላቸው  ሌላ ችግር  የሚናስከትልባቸው  የሚፈጠረው ማህበራዊ ቀውስ ከፍተኛ እንደሆነ ያስረዳሉ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም የመሬት ኪራይና የቤት ግብር  ጨምሮ ከተለያዩ የገቢ ርዕሶች ገቢ እንዲሰበስብ ስልጣን የተሰጠው ቢሆንም አሁን በኮንደሚኒየም የጋራ ቤቶች ባለንብረቶች ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ ተገቢ ሆኖ ሳይሆን ከዓለም ባንክ ጋር የተገባው  ስምምነት ለመፈጸም ለሚያደርገው ጥረት ከፍተኛ የገንብ እጥረት ስለገጠመው መሆኑን አቶ ያሬድ ያስረዳሉ።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.