እለታዊ ዜና፡ የአማራ ክልል የገጠመው ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ለዘመናት የተሰበከው የልዩነት ሃሳብ ውጤት መሆኑን አቶ ደሳለኝ ጣሰው ገለፁ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26/2015 ዓ.ም፡- የአማራ ክልል የገጠመው ወቅታዊ የጸጥታ ችግር በድንገት የተከሰተ ሳይሆን ለዘመናት የተሰበከው የልዩነት ሃሳብ ውጤት በመሆኑ ችግሮችን ገምግሞ እና አርሞ መውጫ በሮችን ማዘጋጀት ተገቢ ነው ሲሉ የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኅላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ገለፁ፡፡

የአማራ ክልል ሠላም እና ጸጥታ ቢሮ ኅላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በአማራ ክልል ወቅታዊ የሠላም እና ደህንነት ላይ መሠረት ያደረገ የግምገማ ውይይት በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ባለው መድረክ “የእርስ በእርስ ልዩነቶች አሸናፊም ተሸናፊም የላቸውም፤ ለችግሮቻችን የበሰለ መፍትሄ መፈለግ ያስፈልጋል” ብለዋል።

“የሠላም እና ደህንነት ጉዳይ የአማራ ሕዝብ ወቅታዊ ቁልፍ አጀንዳ ነው” ያሉት አቶ ደሳለኝ  የክልሉን ሠላም እና ማሕበረሰባዊ ረፍት አደጋ ላይ የሚጥሉ በርካታ የጸጥታ ችግሮች ተፈጥረው እንደነበር ገልፀው ችግሮችን በቅድሚያ በሠላማዊ መንገድ በሽምግልና እና በውይይት ለመፍታት ጥረት መደረጉን ገልፀዋል ሲል አሚኮ ዘግቧል

ኃላፊው ለክልሉ አሁንም ድረስ አጀንዳዎችን በመወርወር አካባቢውን ሠላም የራቀው ቀጣና ለማድረግ የሚሰሩ መኖራቸውን ጠቅሰው የተለያየ ፍላጎት ያላቸው እና በውስጥም በውጭም ያሉ ኃይሎች የክልሉን ሠላም ለማወክ ቀን ከሌሊት እየሰሩ ነው ብለዋል።

ችግሩ በተፈጠረበት መጠን ልክ ከቁጥጥር ውጭ ያልወጣው ከችግሮቹ በላይ የመሆን ሥነ-ልቦናዊ እና ታሪካዊ ልምድ ያለው ሕዝብ በመሆኑ ነው ያሉት አቶ ደሳለኝ ክልሉ በሀገሪቱ የተከሰቱ የሕልውና ስጋቶችን እስከ መስዋዕትነት የደረሰ ዋጋ በመክፈል የቀለበሰ ታላቅ ሕዝብ ነው ብለዋል፡፡

የክልሉን ሠላም እና ጸጥታ ማስከበር ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም ያሉት አቶ ደሳለኝ የጸጥታ ኃይሉ እና የፖለቲካ አመራሩ በቅንጅት መሥራት እንደሚኖርባቸው ጠቅሰው የክልሉ ሕዝብ፣ ወጣቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና መላው ሕዝብ ለክልሉ ሠላም መከበር እና ለሕግ የበላይነት መስፈን በጋራ እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.