ዜና፣ በኮምቦልቻ ከተማ ከልኡል መኮነን ሆቴል እስከ ኢንዱስትሪ ፓርክ ያለው መንገድ “ማሪቱ ለገሰ ጎዳና” በሚል ተሰየመ

ፎቶ፥ኮምቦልቻ ኮምዩኒኬሽን

አዲስ አባባ፣ጥር 01 ቀን 2015 ዓ.ም፡- በኮምቦልቻ ከተማ ከልዑል መኮነን ሆቴል ወደ አየር መንገድ በሚወሰደው ጎዳና፣ እስከ ኢንዱስትሪ ፓርክ ያለው መንገድ በአምባሰሏ ንግስት አርቲስት ማሪቱ ለገሰ ስም እንዲሰየም መወሰኑን የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳዳደር በትላንትናው እለት አስታወቀ።

እንደ የኮምቦልቻ ኮምዩኒኬሽን መረጃ፣ የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መሀመድ አሚን የሱፍ ወሎ የ4ቱም ቅኝት መፈለቂያ የበርካታ ድምጻውያን እና ደራሲያን መገኛ አካባቢ ነው ብለዋል። ወሎ በበርካታ አርቲስቶች የተዜመለትና ህዝቡ በፍቅር በአብሮነት በአንድነት ተወዶ ተከባብሮ የሚኖር ማህበረሰብ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ አሚኮ ዘገባ ደግሞ “ወሎ ሲነሳ ማሪቱ ትነሳለች ማሪቱ ስትነሳ ወሎ ትነሳለች” ያሉት ከንቲባው፣ ማሪቱ ማለት በየትም ቦታ “የወሎ አምባሳደር ናት ” ለዚህም ላደረገችው እስተዋጾ በስሟ ጎዳና መሰየሙ ላበረከተችው አስተዋጾ ማስታወሻ ነው ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የከተማ አስተዳደሩ ባቋቋመው ጊዜያዊ ኮሚቴ የባህል አልባሳት እና ልዩ ልዩ የጌጣጌጦች ሶጦታ አበርክቶላታል።

የአምባሰሏ ንግስት አርቲስት ማሪቱ ለገሰ ከ23 አመታት ቆይታ በኋላ ባለፈው ሳምንት ሰኞ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቷ የሚታወስ ነው።

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.