ዜና፣ በቁጥጥር ሥር ውሎ በፍርድ ሂደት ላይ እያለ ከፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ፖሊስ እጅ ያመለጠው ኤርትራዊው ኪዳነ ዘካርያስ ሱዳን ውስጥ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አረጋገጠ

ኤርትራዊው ኪዳነ ዘካርያስ። ፎቶ፡ ፌደራል ፖሊስ

አዲስ አባባ፣ ታኅሣሥ 28 ቀን 2015 ዓ.ም፡- በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል በቁጥጥር ሥር ውሎ በፍርድ ሂደት ላይ እያለ የካቲት 11 ቀን 2013 ዓ.ም ከፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ፖሊስ እጅ አምልጦ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይፈለግ የነበረው ኤርትራዊው ኪዳነ ዘካርያስ ሱዳን ውስጥ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖለስ አረጋገጠ።

“በስደተኞች ላይ በሚፈጽመው የጭካኔ ተግባርና ግፍ የተሞላበት አያያዝ የሚታወቀው አደገኛ የሰዎች አዘዋዋሪ ኪዳነ ዘካርያስ ሀብተማርያም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በዓለም አቀፍ የፖሊስ ኅብረት ድርጅት (INTERPOL) በኩል በአሰራጨው መረጃ መሠረት በሱዳን በቁጥጥር ሥር ውሏል” በማለት የፌደራል ፖሊስ ጨምሮ ገልጿል ።

ተጠርጣሪው በምስራቅ አፍሪካ ስደተኞች ላይ ከሚደረገው አፈና፣ ዝርፊያ እና ግድያ ጀርባ ያለውን ትልቅ የወንጀለኛ ድርጅትን በመምራት በኢትዮጵያ እና በኔዘርላንድስ ስደተኞችን በህገ-ወጥ መንገድ በማዘዋወርና በሌሎች ተያያዥ ወንጀሎች እ.ኤ.አ ከ2019 ጀምሮ በሁለት የኢንተርፖል ቀይ ማስታወቂያዎች ይፈለግ እንደነበር ይታወቃል።

የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት፣ የዓለም አቀፍ የፖሊስ ኅብረት ድርጅት (INTERPOL)፣ የኢትዮጵያ፣ የሱዳን፣ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች፣ የኔዘርላንድስ ፖሊስ፣ ኢሮፖል እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች በጋራ በመተባበር በአቋቋሙት ግብረ-ሃይል መካከል በተደረገው የመረጃ ልውውጥ ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራ እየተጣራበት ይገኛል።

ከምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት እና ከኢንተርፖል አባል ሀገራት ጋር በመተባበር በተጠርጣሪው ዙሪያ እየተካሄዱ ያሉ ተጨማሪ ምርመራዎች የቀጠሉ ሲሆን በዚህም ሌሎች በዓለም አቀፍ ደረጀ የሚፈለጉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ሊውሉ እንደሚችሉ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ከኢትዮጵያ እስከ ደቡብ አፍሪካ የተዘረጋውን የህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መረብ ለመበጣጠስ ለጀመረው የተጠናከረ ኦፕሬሽን ኅብረተሰቡ ከፖሊስ ጎን ሆኖ የተለመደውን ቀና ትብብር እንዲያደርግ ጥሪውን ያቀርባል። ምንጭ፣ ፌደራል ፖሊስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.