ዜና፡ የሶዶ ከተማ አቃቤ ህግ ታዋቂው ምሁርና የተቃዋሚ ፓርቲ አባል አሰፋ ወዳጆ ላይ ክስ መሰረተ




በብሩክ አለሙ @Birukalemu21

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13/ 2014 ዓ.ም፡- የሶዶ ከተማ አቃቤ ህግ የወላይታን በክልል የመደራጀት ጥያቄ ደጋፊ እና የወላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ ፓርቲ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ አሰፋ ወዳጆ የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ጥሰዋል ሲል ክስ መሰረተ፡፡

የክሱ ዝርዝር ደብዳቤ እንደሚገልፀው ተከሳሹ በራሰቸው ማህበራዊ ሚድያዎች እና በስብሰባዎችና ላይ በአገር ሰላምና ደህንነት ላይ ችግር ለመፍጠር እና በሀገር ውስጥ ግጭትና ሁከት ለመፍጠር አስቦ በርካታ ተከታይ ባሉት Asefa Oyato Wodajo  በሚለው የፌስቡክ  ገጽ ላይ የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃን በተንቀሳቃሽ ምስል አሰራጭቷል ሲል ያስረዳል፡፡

አቃቤ ህጉ በዚህም መሰረት ተከሳሹ የኢፌድሪ መንግስት የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1185/2012 ዓ/ም አንቀጽ 4፤5 እና 7(4) መተላለፋቸው የሚያሳይ በተከሳሹ ዩቱዩብ የተናገሩበትን ቨድዮ በሲዲ በማቅረብ ክስ መስርቼባቸዋለው ብሏል፡፡

አቶ አሰፋ ዛሬ ነሐሴ 13 ቀን ችሎት ቀረቡ ሲሆን “ቤተሰቤ እየተጉላላ ስለሆነ የዋስትና መብት ተከብሮልን ከውጭ ሆኜ ልከራከር” ብለው ጠይቀው  ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎበታል ሲሉ ባለቤቱ ምንተዋብ ገብረስላሴ ለአዲስ ስታንዳርደ ገልፀዋል፡፡ አክለውም  አቃቤ ህግ 14 ተጨማሪ ቀን ይሰጠኝ ብሎ መጠየቁን ጠቅሰው ፍርድ ቤቱ በአምስት ቀን ውስጥ ምርመራውን ጨርሶ ለነሐሴ 18 ቀን እንዲቀርብ ሲል ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል ብለዋል፡፡

የወላይታን በክልል የመደራጀት ጥያቄ ደጋፊ እና የወላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ ፓርቲ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና የቀድሞ የዲላ ዩኒቨርሲቲ መምህር የነበሩት አቶ አሰፋ እሁድ ነሐሴ 1 ቀን 2014 ዓ.ም በሶዶ ከተማ የጸጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አዲስ ስታንዳርድ መዘገቧ ይታወሳል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.