ዜና፡ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕዝበ ውሣኔ እንዲያደራጅ ባቀረበለት ጥያቄ ላይ ውሣኔ አሳለፈ

ምስል- የፌዴሬሽን ምክር ቤት


በብሩክ አለሙ @Birukalemu21


አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18/ 2014 ዓ.ም፡- የፌደሬሽ ምክር ቤቱ ነሐሴ 12 ቀን 2014 ዓ.ም በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት የሚገኙ 6 ዞኖች  ማለትም የወላይታ፣ የጋሞ፣ የጎፋ፣ የደቡብ ኦሞ፣ የጌዴኦ፣ የኮንሶ ዞኖች፣ እንዲሁም 5 ልዩ ወረዳዎች ማለትም  የደራሼ፣ የአማሮ፣ የቡርጂ፣ የአሌ እና የባስኬቶ ልዩ ወረዳ በጋራ ”የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” የመመስረት ጥያቄ  በማቅረባቸው ውሳኔ ለመስጠት እንዲያስችል በብሔራዊ የምርጫ ቦርድ አማካኝነት በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ እንዲደራጅና የሕዝብ ውሳኔው ውጤት ሪፖርት ለምክር ቤት እንዲቀርብ ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ ቦርዱ የማደራጀት ጥያቄው ላይ ውሣኔ አሳለፈ፡፡

በብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ሕዝበ ውሳኔውን ለማደራጀት እንደ ግብዓት ሆኖ ለቦርዱ ያገለግል ዘንድ ከላይ የተገለጹት ከስድስቱ ዞኖች እና የአምስቱ ልዩ ወረዳዎች በየራሳቸው ምክር ቤቶች ሕዝበ ውሳኔውን በጉዳዩ ላይ የሰጧቸውን ውሳኔዎች፣ ውሳኔያቸውን ለማስፈጸም ለፌዴሬሽን ም/ቤት ያቀረቧቸውን ጥያቄዎች፣ እንዲሁም አያይዘው ለምክር ቤቱ የላኳቸው ሌሎች ሰነዶች እንዲላኩለት ጠይቋል።

ነሐሴ 12 ቀን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከላይ በተጠቀሱት 6 ዞኖች እና 5 ወረዳዎች የሚደረገው የህዝብ ውሳኔ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ እንዲደራጅ ለብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የቆረጠውን ቀን በተመለከተ ቦርዱ ጉዳዩን አግባብነት ካላቸው የህግ ማእቀፎች አንፃር በጥልቅ መመርመሩን ጠቅሷል፡፡

ይህን በተመለከተም አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ተከናውኖ ምርጫዎች ወይም የህዝበ ውሳኔዎች ደረጃቸውን በጠበቀ ሁኔታ ለማካሔድ  የሚወስደውን ጊዜ ምን ያህል እንደሆነ የመወሰን ፣ የመርሀ ግብር ሰሌዳ የማዘጋጀት የማፅደቅ እንደ አስፈላጊነቱም የማሻሻልና የማስፈጸም  ሥልጣን የተቋሙ ብቻ መሆኑን ምርጫ ቦርድ አስገንዝቧል።

ቦርዱ ለዚህ ጉዳይ አፈፃፀም የሎጂስቲክስ ዝግጅት ለማድረግ፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ እና ምደባ ለመተግበር፣ የምርጫ ፀጥታ ጉዳይን ለመገምገም፣ የመራጮች ትምህርት ለመስጠት፣ የምርጫ ጣቢያዎች ለማደራጀት፣ ለታዛቢ ሲቪል ማህበራት ፈቃድ ለመስጠት እና በጉዳዩ ላይ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት ለማወያየት የሚያስፈልገውን ጊዜ ታሳቢ ያደረገ የጊዜ ሰሌዳ አውጥቶ ለምክር ቤቱ እንደሚገልፅም ነው ያስታወቀው። 

ነሐሴ 12 ቀን 2014 ዓ.ም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባደረገው ስብሰባ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የሚገኙ የ6 ዞኖች (የጋሞ፣ ወላይታ፣ ጎፋ፣ ጌዴኦ፣ ኮንሶ እና የደቡብ ኦሞ ዞኖች) እና የ5 ልዩ ወረዳዎች(የቡርጂ፣ የአማሮ፣ የደራሼ፣ የባስኬቶ እና የአሌ ) በአንድ ክልል የእንደራጅ አቤቱታን ተቀብሎ ከመረመረ በኃላ ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ውሳኔ ማስተላለፉን አዲስ ስታንዳርስድ መዘገቧ ይታወሳል፡፡

ምክር ቤቱ የጋራ ክልል የመመስረት ጥያቄው ከሕገ መንግሥቱ አንፃር ውሳኔ ለመስጠት እንዲያስችል የሕዝብን ይሁንታ ማረጋገጥ ስለሚያስፈልግ ከማንኛውም ተጽእኖ ነጻ በሆነ መልኩ ገለልተኛ በሆነው ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ አማካኝነት በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ እንዲደራጅና የሕዝብ ውሳኔው ውጤት ሪፖርት ለምክር ቤት እንዲቀርብ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

በተጨማሪም የሀድያ፣ ሀላባ፣ ከምባታና ጠምባሮ፣ ስልጤ፣ ጉራጌ ዞኖችና የም ልዩ ወረዳ በነባሩ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አንድ ላይ የሚቀጥሉ ይሆናል የተባለ ሲሆን የሕዝብ ውሳኔው ሂደት ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና የሕዝብን ሰፊ ተሳትፎ ባረጋገጠ መልኩ እንዲጠናቀቅ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና የጸጥታ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ምክር ቤቱ በአብላጫ ድምጽ መወሰኑ የሚታወስ ነው፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.