ዜና፡ በጋምቤላ ክልል በደረሰ በጎርፍ አደጋ ከ74 ሺ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸው ተገለጸ

ምስል-የጋምቤላ ክልላዊ መንግስት ኮሙኒኬሽን

በብሩክ አለሙ @Birukalemu21  

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19/2014 ዓ.ም፡- በጋምቤላ ክልል በ8 ወረዳዎች በተከሰተ የጎርፍ አደጋ የተነሳ ከ74 ሺህ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር አገልግሎት አስታወቀ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉም ጆር ወረዳ ኡንጎጊ ከተማ በመገኘት የደረሰውን ጉዳት የተመለከቱ ሲሆን በጉብኝታቸውም ወቅት “ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ለማድረግ የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል” ብለዋል።

በክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳደር አቶ ተንኳይ ጆክ የተመራ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ቡድን በኢታንግ እና በላሬ ወረዳዎች ተገኝተው በክልሉ የተከሰተው የጎርፍ አደጋ በርካታ ነዋሪዎችን ከቤት ንብረታቸው እንዳፈናቀለ እና በሰብልና እና በንብረት ላይም ከባድ ጉዳት መድረሱን መመልከታቸውን ተናግረዋል። በጎርፉ አደጋ ለተፈናቀሉ ወገኖች መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ነሀሴ 16 ቀን 2014 ዓ.ም በጋምቤላ ክልል በአራት ወረዳዎች በደረሰ የጎርፍ አደጋ ከ40ሺ በላይ የሚሆኑ አባዎራና እማዎራ ከመኖሪያ ቀያቸዉ መፈናቀላቸዉን አዲስ ስታንዳርድ መዘገቡ የሚታወስ ሲሆን በጎርፉ በኢታንግ ልዩ ወረዳ፣ በዋንቱዋ፣ በመኮይ፣ በባዜል ቀበሌ፣ በፒሏል፣ በቢልጃኮክ እንዲሁም በላሬ አካባቢዎች በሺዎች የሚቆሩ አባወራና እማወራ ከቤት ንብረታቸዉ እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል፡፡

የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር አገልግሎት ኃላፊ አቶ ጋትቤል ሙን እንዳሉት በሃገሪቱ ደጋማዉ አካባቢ በጣለዉ ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት በላሬ፣ በመኮይ በዋንቱዋና በኢታንግ ልዩ ወረዳ በሚገኙ ቀበሌዎች ላይ የጎርፍ መጥለቅለቅ ማስከተሉን ተናግረዋል።አቶ ጋትቤል አያይዘዉም የጎርፍ አደጋዉ በቤት ዉስጥ ያሉ ቁሳቁሶች እንዲሁም በቁም እንስሳት ላይ ጉዳት ማድረሱን ገልፀዋል። በጎርፍ አደጋዉ ከቤት ንብረታቸዉ ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸዉ ጠቅሰዉ ይህንንም ከክልሉ መንግስትና ከሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት በመነጋገር አፋጣኝ ድጋፍ የሚደርስበት ሁኔታ ይመቻቻል ብለዋል።

በጎርፍ አደጋዉ ከመኖሪያ ቀዬአቸዉ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች  የጎርፍ አደጋዉ ድንገት የተከሰተ በመሆኑ ንብረቶቻቸውን ለማሸሽ እንኳን ጊዜ እንዳልነበራቸዉ እና  አደጋዉ ሲከሰት ልጆቻቸዉን ብቻ ይዘዉ ደረቃማ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ማረፋቸን ጠቅሰዉ መንግስት አስቸኳይ ድጋፍ እንዲያደርግላቸዉም ጠይቀዋል።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ርዳታ ማስተባበሪያ ትናንት ባወጣው መግለጫ በመጪዎቹ ሳምንታት ውስጥ አንዳንድ የኢትዮጵያ ክፍሎች የጎርፍ አደጋ ሊያጋጥም  እንደሚችል ጠቁሟል፡፡ እክሎም በጎርፍ አደጋ የተነሳ ከ 1.7 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሊጠቁ እንደሚችሉና ከ 400,000 በላይ ሰዎችን የመፈናቀል ስጋት ውስጥ እንደሆኑ ገልጿል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.