ዜና፡ በጋምቤላ ከተማ የመንግስት ሃይሎች ከጋምቤላ እና ከኦሮሞ ታጣቂ ቡድኖች ጋር ወጊያ አደረጉ፣ በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ ሁለት ከተሞች የተኩስ ልውውጥ ድምጽ ተሰማ

ኦነሰ ሀይሎቼ በደምቢዶሎ እና ጊምቢ ከተሞች  ከመንግስት ታጣቂዎች ጋር እየተዋጉ ነበር ብሏል

በአዲስ ስታንዳርድ ሪፖርተሮች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7/2014- የጋምቤላ ክልል መንግስት ዛሬ ማለዳ  በጋምቤላ ከተማ ከጠዋቱ 12፡30 ጀምሮ በ”ጠላት ጦር” እና በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መካከል የተኩስ ልውውጥ እየተደረገ መሆኑን እስታወቀል።  ባወጣው መግለጫ የጋምቤላ ነፃነት ግንባር (ጋነግ) እና መንግሥት  ሸኔ ብሎ የሚጠራው የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (ኦነሰ) ጋር በመቀናጀት በጋምቤላና በአካባቢው ተኩስ መክፈታቸውን  አስታወቋል፡፡

የጋምቤላ ነፃነት ግንባር (ጋነግ) እና የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (ኦነሰ) ቃል አቀባይ በበኩላቸው የጋምቤላ  ዋና ከተማን ለመቆጣጠር በቅንጅት ዘመቻ መጀመራቸውን ገልፀዋል፡፡በግምቢና ደምቢ ዶሎ ከተሞች የኦነግ ሃይሎች ከመንግስት ሃይሎች ጋር እየተዋጉ መሆኑንም  አስታወቋል፡፡

ዛሬ ጠዋት የክክሉ መንግስት ባወጣው አጭር መግለጫ በጋምቤላ ከተማ ያለውን አንፃራዊ ሰላም ለማደፍረስ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት የፀረ ሰላም ሀይሎችን ለመመከት የከተማው ማህበረሰብ ሳይረበሽ ከፀጥታ ሀይሉ ጎን እንዲሆን ሲል ጥሪ አቅርቧል።

የከተማው ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት ከተማዋ በጋምቤላ ነጻ አውጪ ግንባር እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) ቁጥጥር ስር ውሏል። “አብዛኞቹን መንደሮች ተቆጣጥረውታል። አሁን ይህን በምናገርበት ሰዓት የተኩስ ድምጽ ይሰማኛል ከጠዋት ጀምሮ ተኩስ ይሰማል” ሲልም  አክሎ ገልጿል፡፡

የክልሉ ምክር ቤት ዋና መስሪያ ቤትም በታጣቂ ሃይሎች ቁጥጥር ስር መዋሉንም  ነዋሪው ተናግሯል። እሱንም ጨምሮ ሌሎች በርካታ ነዋሪዎች ለሕይወታቸው በመስጋታቸው  ወደ ጫካ መሰደዳቸውንም አስረድቷል። እንደ ነዋሪው ገለጻ ጥቃቱን ለመከላከል እየሞከሩ ያሉት የፌደራል ፖሊስ አባላት እና የክልሉ ልዩ ሃይል አባላት ብቻ ናቸው። “ከባድ መሳሪያ የታጠቁ ታጣቂዎች ባደረሱት ድንገተኛ ጥቃት ተዳክመዋል። ጥይት ጨርሰው ወደ ፖሊስ ጣቢያ አፈግፍገዋል”  ሲል አስረድቷል።

የክልሉ መንግስትም “የመንግስት ሃይሎች ከፍተኛ ውጊያ ካደረጉ በኋላ የከተማዋን  በከፊል ነፃ ማውጣት ተችሏል” ሲል ተጨማሪ መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫው የደረሰው ጉዳት በውል እንደማይታወቅ የገለፀ ሲሆን  በሁለቱም ወገን ላይ ጉዳት መድረሱን ግን  አስታውቋል። መግለጫው በጋምቤላ ከተማ ከጠዋቱ 12:30 ጀምሮ ሲካሄድ የነበረው የተኩስ ልውውጥ ያለማቋረጥ እስከ ረፋዱ 4 ሰዓት ሲካሄድ ቆይቶ በአሁኑ ሰዓት በከተማው መጠነኛ መረጋጋት መፈጠሩን ገልጿል። መግለጫው  እስከ አሁን ሠዓት ድረስ የተኩስ ልውውጥ መኖሩን ጠቅሶ የከተማዋ ነዋሪዎች በቤታቸው እንዲቆዩ አሳስቧል።

ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የክልሉ ባለስልጣን በበኩላቸው በጥቃቱ ቢያንስ ሁለት የጸጥታ ሃይሎች ሲገደሉ  ከታጣቂዎች መሃል ሶስት  መገደላቸውን ለቢቢሲ አማርኛ ተናግረዋል። በስፍራው ያሉ የመንግስት ሃይሎች በቁጥር መብለጡንና የክልሉ መንግስት ለፌዴራል መንግስት ማሳወቁን አክለዋል። “በአቅራቢያ ካሉ ከተሞች ተጨማሪ ሃይል ለማሰማራት እየሞከሩ እንደሆነ ነግረውናል” ሲሉም አስረድተዋል።

በከተማዋ አንዳንድ አካባቢዎች የታጠቁ ሃይሎች መታየታቸውን ቢቢሲ አማርኛ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል። ነዋሪዎቹ አክለውም አንዳንድ የከተማዋ አካባቢዎች በታጣቂ ሃይሎች ቁጥጥር ስር መሆናቸውን ገልጸው፣ የክልሉ ፕሬዝዳንት መቀመጫ ላይ ጥቃት ሊደርስ እንደሚችል ግምታቸውን ገልፀዋል። በተጨማሪም በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ቅጥር ግቢ አካባቢ ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ መሰማቱን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። በርካቶች መቁሰላቸውንና የፕሬዚዳንቱ መኖርያ ቤት እና የነዳጅ ማከማቻ በታጣቂ ሃይሎች ኢላማ መደረጉንም ተናግረዋል። ፕረዚደንት ኡሞድ ኡጁሉ ግን ስለተኩስ ልውውጡ እና ስለከተማዋ ወቅታዊ ሁኔታ ምንም አይነት መረጃ እንደሌላቸው ለቢቢሲ አማረኛ ተናግረዋል።

የጋምቤላ ነፃነት ግንባር (ጋነግ) ከኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (ኦነሰ) ጋር በመሆን በ ጋምቤላ ዋና ከተማ ውስጥ ዛሬ ማለዳ ላይ ዘመቻ እያካሄደ መሆኑን አስታውቋል፡፡ የጋምቤላ ነፃነት ግንባር (ጋነግ) በፌስቡከ ገፁ ዘመቻው የብልጽግና መንግሥት ሰራዊት ተቋማት፣ የብልጽግና መንግስት አመራሮች እና ሰራዊት ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ገልፆ ማንኛውም ስቭል ማይበረሰብ የበራር ጥይቶች ሰለባ እንዳይሆን ከቤቱ እንዳይወጣ አሳስቧል፡፡ በተመሳሳይ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (ኦነሰ)  አለምአቀፍ ቃል አቀባይ ኦዳአ ታርቢ “የጋምቤላ ነፃነት ግንባር እና የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት የተቀናጀ ዘመቻ በአሁኑ ወቅት በጋምቤላ ዋና ከተማ እየተካሄደ ነው” ብለዋል።

በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ እና በቀለመ ወለጋ ዞኖች በሚገኙ ሁለት ከተሞች  ወታደራዊ ሃይላቸው ከመንግስት ሃይሎች ጋር እየሰተዋጉ እንደሆነ  የኦነሰ ቃል አቀባይ ተናግረዋል። በቄለም ወለጋ ዞን ዋና ከተማ ደምቢዶሎ እና በምዕራብ ወለጋ ዞን አጎራባች በምትገኝ ጊምቢ ከተማ ከመንግስት ሃይሎች ጋር እየተዋጉ መሆኑን ኦነሰ ገልጿል። የኦነሰ ቃል አቀባይ በትዊተር ገፁ ላይ እንዳስታወቀው በዳምቢዶሎ ታስረው የነበሩ የፖለቲካ እስረኞችን ማስፈታቱን አስታውቋል።

የጊምቢ ከተማ ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገረው ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት ጀምሮ በከተማው  አካባቢ ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ እንደተሰማ ገልጿል። አክሎም የከተማው ነዋሪዎች ከቤታቸው አለመውጣታቸውን ገልፆ በከተማዋ ከመንግስት ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች በስተቀር ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንደሌለ ገልጿል። በተመሳሳይ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የደምቢዶሎ ከተማ ነዋሪ፣  “ከባድ የተኩስ ድምፅ ነው ከእንቀልፋችን ቀሰቀሰን። ከቤት መውጣት አልቻልንም። የተኩስ ልውውጥ እንሰማለን ግን ምን እየተካሄደ እንዳለ አናውቅም”  ስል አስረድቷል።

የፌዴራል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት  ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።

የጋምቤላ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ከጥቂት ሰዓታት በፊት ባወጣው መግለጫ በከተማው ከጠዋቱ 12:30 ጀምሮ ያለማቋረጥ ለረጅም ሰዓት የተኩስ ልውውጥ ሲደረግ እንደነበር አስታውሶ በአሁኑ ሰዓት ተቆርጠው የቀሩ የታጣቂ ቡድኑ አካላትን ‘የማጥራት ስራ’ እየተከናወነ መሆኑን አስረድቷል።

ታጣቂ ቡድኑን ሙሉ በሙሉ ለመደምሰስ በመንግስት ፀጥታ አካላት እየተወሰደ ያለዉ የማያዳግም እርምጃም ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገልጿል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.