ሰኔ24፣2014 ዓ.ም፣አዲስአበባ፦ የ”ህግ ማስከበር ዘመቻው ከጠላት የሚለቀቅን ገንዘብ በመጠቀም የክልሉን ሕዝብ በመከፋፈልና እርስበርስ በማጋጨት ጠላት ወደፊት ሊያካሂደው ላሰበው ጥቃት፤ የተዳከመና የተከፋፈለ አማራን የመውረር እቅዱን ለማሳካት ተልእኮ ፈጻሚ በመሆን ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ቡድኖችም ተልእኳቸውን መፈጸም የማይችሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር ተደርጓል” ሲሉ የአማራ ክልል መንሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ገለፁ፡፡
ኃላፊው ይህን ያሉት የህግ ማስከበር ዘመቻውንና ተያያዥ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት ሲሆን፣ የክልሉ መንግሥት የህግና ሥርዓት ማስከበር ዘመቻውን ሲጀምር የራሱን መዋቅር ከመመርመር የጀመረ መሆኑን ጠቅሰው በፀጥታ መዋቅሩ ውስጥ የከዳ፣ የጦር መሣሪያ ንግድ ላይ የተሠማራ፣ በወንጀል የተጠረጠረን በሕግ ቁጥጥር ሥር ማዋል ተችሏል ብለዋል፡፡
የህግ ማስከበር ዘመቻው ከጅምሩም የሕዝቡን የሰላም ጥያቄዎች መነሻ አድርጎ እየተከናወነ ያለ መሆኑና የህግና ሥርዓት ማስከበር ዘመቻው ከተጀመረ ወዲህ “ሕዝባችን እረፍት አግኝቷል፤ ሰላምና መረጋጋትም ተፈጥሯል እንዲሁም ወደ ሥርዓት አልበኝነት ሊወስድ የሚችለው በር ተዘግቷል” ሲሉ ኃላፊው አቶ ግዛቸው አክለው ገልፀዋል፡፡
በ”አሸባሪዎች” ጥቃት የሚደርስባቸውን ዜጎች ምክንያት በማድረግ ሀዘንን መግለጽ ከሁላችንም የሚጠበቅ ቢሆንም የጠላትን ዓላማ ሊያሳካ በሚችል መንገድ በሰልፍና ግርግር በመፍጠር የሚደረጉ ሀዘንን መግለጫዎች በጥንቃቄ የሚታዩ መሆናቸውን በመግለፅ ህግና ሥርዓትን የማስከበር ሥራ ወቅታዊ ጉዳይ ሳይሆን የሁልጊዜ ሥራችን በመሆኑ በሚዲያና ተግባቦት፣ በፖለቲካ እና ከሕዝባችን ጋር በሚኖሩ የገጽ ለገጽ ምክክሮች ታጅቦ በተቀናጀ ሁኔታ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
“አሁንም ጠላት ለወረራ እየተዘጋጀ ለመሆኑ በቂ መረጃዎች ያሉ በመሆናቸው የፀጥታ መዋቅራችንን የማደራጀት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት ይቀጥላል” ያሉት አቶ ግዛቸው “ከህግ ማስከበሩና ጠላቶቻችንን ለመመከት ከምናደርገው ዝግጅት ጎን ለጎን ለልማት ሥራዎቻችን ትኩረት መስጠት ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“ጠላት ከሚያደርገው ዝግጅት አኳያም ሕዝባችን ክብሩንና ነጻነቱን ለማስጠበቅና የፀጥታ መዋቅራችን ጽኑ ደጀን ለመሆን ራሱን ዝግጁ ሊያደርግ ይገባል” ሲሉም አሳስበዋል፡፡
ይህ በእንዲ እያለ በባሕር ዳር ከተማ የባጃጅ ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ እስከ ምሽቱ 2:00 ብቻ እንዲኾን ተገድቧል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ፀጥታ ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው “አሁን ካለንበት ሀገራዊ እና ክልላዊ ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ለከተማው ሰላምና ደኅንነት ሲባል ከዛሬ ምሽት ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ማንኛውም የባጃጅ ወይም የባለሦስት እግር ተሽከርካሪ እስከ ምሽቱ 2:00 ብቻ አገልግሎት የሚሰጡ ይሆናል” ብሏል። ከምሽቱ ሁለት ሰዓት በኋላ ሲንቀሳቀስ የተገኘ ማንኛውም የባጃጅ ተሽከርካሪ ላይ ለሚወሰድበት ማንኛውም ቅጣትና እርምጃ ኀላፊነቱን ባለቤቱ ወይም አሽከርካሪው እንደሚወስድም ተገልጿል።
“በፀጥታ ኀይላችን ብርቱ ትግል፣ በሕዝባችን የማይቋረጥ ደጀንነት የአፍራሽ ኀይሎች ምኞት አይሳካም ” ያለው ምክር ቤቱ ማንኛውንም ወንጀል መከላከል የሚቻለው የኅብረተሰብ ተሳትፎ የላቀ መሆኑን ገልፆ የከተማው ነዋሪ እንደተለመደው ጥቆማዎችን በመስጠትና ከሕግ አስከባሪዎች ጎን በመቆም ለሰላም ዘብ እንዲቆም ጥሪ አቅርቧል፡፡
ሰኔ 21 ቀን 2014 ዓ.ም በባሕርዳር ከተማ ውስጥ አራት ቦምቦችን በማፈንዳት የሽብር ጥቃት ለመፈፀም የተንቀሳቀሱ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአማራ ክልል ፓሊስ ኮሚሽን መግለፁ ይታወሳል ።
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያና ኮምዩኒኬሽን መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር መሰረት ደባልቄ በሰጡት መግለጫ ሰኔ 20/2014 ዓ.ም ምሽት ኅብረተሰቡን ለማሸበር ያለመ ወንጀል መፈፀም የፈለጉ ኀይሎች በባሕርዳር ከተማ በአራት ቦታዎች ላይ ቦንብ እንዳፈነዱ ገልጸዋልበማለት አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ኮማንደር መሰረትን እንደ ምንጭ በመጥቀስ ዘግቧል። ፓሊስ ከሕዝብ ጋር በመቀናጀት ባደረገው ክትትልም ወዲያውኑ ስድስት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር አውሏል። በተጨማሪም ከተጠርጣሪዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው 14 ተባባሪ አካላት በቁጥጥር ስር ውለው የክልልና የፌዴራል የፀጥታ አካላት ምርመራ እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።አስ