ዜና: በባሕርዳር ከተማ ውስጥ አራት ቦምቦችን በማፈንዳት የሽብር ጥቃት ለመፈፀም የተንቀሳቀሱ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ ፓሊስ ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2014 በባሕርዳር ከተማ ውስጥ አራት ቦምቦችን በማፈንዳት የሽብር ጥቃት ለመፈፀም የተንቀሳቀሱ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአማራ ክልል ፓሊስ ኮሚሽን ገለፀ ።

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያና ኮምዩኒኬሽን መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር መሰረት ደባልቄ በሰጡት መግለጫ ሰኔ 20/2014 ዓ.ም ምሽት ኅብረተሰቡን ለማሸበር ያለመ ወንጀል መፈፀም የፈለጉ ኀይሎች በባሕርዳር ከተማ በአራት ቦታዎች ላይ ቦንብ እንዳፈነዱ ገልጸዋል በማለት አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ኮማንደር መሰረትን እንደ ምንጭ በመጥቀስ ዘግቧል። ፓሊስ ከሕዝብ ጋር በመቀናጀት ባደረገው ክትትልም ወዲያውኑ ስድስት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር አውሏል።

በተጨማሪም ከተጠርጣሪዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው 14 ተባባሪ አካላት በቁጥጥር ስር ውለው የክልልና የፌዴራል የፀጥታ አካላት ምርመራ እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።

“በሀገሪቱና በክልሉ ሕግ ለማስከበር እየተንቀሳቀስን እንገኛለንበተለይም በአማራ ክልል የተደራጁ ሕገወጦችን ወደ ሕግ ለማቅረብ ሲሠራ ቆይቷል የኀብረተሰቡን የሰላም ጥያቄ በማዳመጥ በተወሰደው ሕግ የማስከበር ርምጃም አብዛኞች ጥፋተኞች ወደ ሕግ ቀርበው እፎይታ ተገኝቷል ብለዋል” በማለት የክልሉ መገናኛ ብዙሀን በተጨማሪ ዘግቧል።

የተጠርጣሪዎች ቤት በሚፈተሽበት ወቅትም 2 ቦንብ፣ 3 ብሬን መሳሪያ እና 3ሺህ 700 ጥይት፣ አንድ ስናይፐርና አምስት መቶ ጥይት እንዲኹም በቀጣይም ተመሳሳይ የሽብር ወንጀል ለመፈፀም የያዙትን እቅድና መመሪያ ፓሊስ መያዙን ኮማንደር መሰረት ጠቁመዋል። ፓሊስ የሚደርስበትን የምርመራ ውጤት ወደፊት ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደረግም ጨምረው ገልፀዋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.