ዜና፦የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በአፋር ክልል ወደ 9000 የሚጠጉ በህገ ወጥ መንገድ ታስረው የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ጠየቀ


ሰኔ 23፣ 2014 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፦ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ)  ባለፈው ሳምንት  ባወጣው መግለጫ በግንቦት ወር አደረኩት ባለው ክትትል እና ቁጥጥር በታህሳስ ወር 2014 ዓ.ም  “በህገ-ወጥ እና ኢ-መንግስታዊ” በሆነ መንገድ ወደ ዘጠኝ ሽህ የሚጠጉ የትግራይ ተወላጆች በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ በሚገኙ ሰመራ እና አጋቲና የማሰሪያ ጣቢያዎች ተይዘው እንደቆዩ አስታውቋል። ኮሚሽኑ በመግለጫው አክሎም ይህ የእስር ድርጊት በአስቸካኡይ እንዲቆምም ጠይቋል። 

ኮሚሽኑ ባሳለፍነው ረቡዕ ሰኔ 22 ቀን 2014 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት ከትግራይ ክልል አዋሳኝ ከሆኑ 3 የአፋር ክልል ወረዳዎች፣ ማለትም ከአባላ፣ ከኮነባ እና ከበረሃሌ ከነበረው ጦርነት ጋር መያዛቸውን ያወሳ ሲሆን የአካባቢው ባለስልጣናት “ለደኅንነታቸው ጥበቃ እና በወንጀል ጥርጣሬ የሚፈለጉ ሰዎችን ለመለየት” በሚል ምክንያት እንደያዟቸው ገልጿል።

ኢሰመኮ በሪፖርቱ በሰመራ ካምፕ ውስጥ በጣም አሳሳቢ ሁኔታዎች እንዳሉም ሳይሸሽግ ጠቅሷል።  ባለፉት 5 ወራት ውስጥ በሰመራ ካምፕ ብቻ በበሽታ ሕይወታቸው ያለፉ የትግራይ ተወላጆች እንዳሉ፣ እንዲሁም ካምፑ ውስጥ በወሊድ ወቅት የሞተች እናት መኖሯን፣ቤተሰቦቿ የአእምሮ መረበሽ ደርሶባታል በሚል በሰንሰለት አስረው ያስቀመጧት ወጣት ሴት መመልከቱን፣ እስከ 10 የሚደርሱ ከባድ ቁስል ያለባቸው ሰዎች እንደተመለከተ፣ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው 5 ሕፃናት እንዲሁም የቆዳ በሽታ ወረርሽኝ ነው በተባለ በሽታ የተጠቁ ከ4-5 ዓመት ዕድሜ መካከል የሚገኙ ሕፃናት በእነዚሁ ካምፖች ውስጥ እንደሚገኙ ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አካቷል። ኮሚሽኑ አያይዞም  ተገቢ ሕክምና ባለማግኘታቸው የቆዳ ወረርሽኝ የተባለው በሽታ ወደ ሌሎች የታሰሩ  ሰዎች መዛመቱን ጠቅሷል። 

እንደኮሚሽኑ ገለፃ የአፋር ክልል የፀጥታ ሃይሎች ከዞኑ እና ከወረዳው በለስልጣናት ጋር በመተባበር በተለያዩ ቀናት ወደተባሉት የእስር ካምፖች እንደወሰዷቸው ጠቅሶ ከተያዙበት ጊዜም ጨምሮ እንዳልተፈቱ አክሎ ተናግሯል። 

ኮሚሽኑ  ያነጋገራቸው በካምፖቹ ውስጥ የሚገኙት ሰዎች ከመኖሪያቸው አካባቢ እንዲወጡና በነዚህ ቦታዎችም እስካሁንም ድረስ እንዲቆዩ የተደረጉት ከፍቃዳቸው ውጪ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሁለቱ ካምፖች በኢሰመኮ የክትትል ጉብኝት ወቅት 8,560 ሰዎች የነበሩ ሲሆን፣ ወንዶች እና ሴቶች ተለያይተው የተያዙ በመሆናቸው የአንድ ቤተሰብ አባላት ተለያይተው ለመኖር ተገድደዋል። ኮሚሽኑ  “በካምፖቹ ውስጥ የሰብአዊ እርዳታና የሕክምና አገልግሎት አቅርቦት እጅግ ውስን በመሆኑና በካምፑ በተከሰተ ወረርሽኝ መሰል በሽታ ለሕይወት መጥፋት ጭምር ምክንያት ሆኗል” ያለ ሲሆን አክሎም “ በወሊድ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር በአካባቢው ወደሚገኝ የጤና ተቋም ሄዶ ለመታከም ባለመፈቀዱ ችግሩን አባብሶታል” በማለት ታሳሪዎቹ ያሉበትን አሳሳቢ ሁኔታ አስምሮበታል፡፡ኢሰመኮ ያነጋገራቸው ጉዳዩ የሚመለከታቸው የክልሉ መንግሥት አካላት “የእንቅስቃሴ ገደብ የተጣለው ለሰዎቹ [ለታሳሪዎቹ] ደኅንነት ጥበቃ እና ከፀጥታ ስጋት ጋር በወንጀል ጥርጣሬ የሚፈለጉ ሰዎችን የመለየት ስራ መስራት በማስፈለጉ” መሆኑን ይናገራሉ። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ሰመራና አጋቲና ካምፕ ውስጥ ተይዘው የሚገኙት ሰዎች ሁኔታ በመጠለያ ጣቢያ ስም የተፈጸመ፣ በብሔር ማንነት ላይ የተመሰረተ ሕገ ወጥ እና የዘፈቀደ እስር በመሆኑ በአፋጣኝ ሊለቀቁ ይገባል፤ ወደ መኖሪያ አካባቢያቸውም እስኪመለሱ ድረስ በካምፑ ውስጥ ለመቆየት የሚፈልጉ ሰዎች ቢኖሩ በሙሉ ፈቃደኝነትና ያለ ማናቸውም ዓይነት የእንቅስቃሴ ገደብ ሊሆን ይገባል” ብለዋል፡፡ ዶ/ር ዳንኤል አክለውም “በፈቃዳቸው ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው ለመመለስ ወይም አሁን ባሉበት ቦታ ለመቆየት ወይም ወደ ሌላ ቦታ ለመሄድ ለሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ አስፈላጊው ድጋፍና እርዳታ ሊሰጣቸውም ይገባል፤ እንዲሁም በምክንያታዊ ሁኔታ በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች ካሉ በመደበኛው የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት ከሚታይ እና በፍርድ ቤት ትእዛዝ ብቻ ከሚፈጸም በስተቀር፤ የአሁኑ አያያዝ የሕግ መሰረት የሌለው ከመሆኑም በተጨማሪ በካምፑ የሚገኙትን ሰዎች ለተደራረበ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እያጋለጠ በመሆኑ በአፋጣኝና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሊያበቃ ይገባል” በማለት አሳስበዋል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.