አዲስ አበባ፡ሰኔ 28/2014፡- ጠቅላይ ሚንስቴር አብይ አህመድ በኦሮሚያ ክልል፣ ቄለም ወለጋ ዞን ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ላይ ጭፍጨፋ እንደተፈፀመባቸው በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው አስታወቁ። ጠ/ሚንስትሩ የጸጥታ አካላት የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (ሸኔ) ላይ ከሚያደርሱበት ዱላ በመሸሽ በምዕራብ ወለጋ በዜጎች ላይ አደጋ እያደረሰ እየሸሸ መሆኑን አስፍረዋል። አክለውም “በዜጎቻችን ላይ በደረሰው መከራ እያዘንን ቡድኑን እስከመጨረሻው ተከታትለን ከህዝባችን ጋር እናስወግደዋለን ” ብለዋል።
ጠ/ሚንስትሩ ይህን ከማለት ውጪ ጉዳት ስለደረሰባቸው አካላት ምንም መረጃ አልሰጡም፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን በሀዋ ገላን ወረዳ መንደር 20 እና መንደር 21 ላይ ቁጥራቸው ያልተረጋገጠ ንፁሀን ዜጎች ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ መፈጸሙን ሪፖርት እንደደረሰው አስታወቋል።
ጥቃቱ የደረሰው ትናንት ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም ሲሆን ኮሚሽኑ ጥቃቱ ያደረሱት የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (ሸኔ) አባላት መሆናቸውንና ግድያውም ከጥዋት አንስቶ መጀመሩን ከአካባቢው ተርፈው የሸሹ ሰዎች አመልክተዋል ብሏል።
“በአካባቢው የቀጠለው የጸጥታ ችግር እና በነዋሪዎች ላይ እየደረሰ ያለው ብሔር ተኮር ግድያ በአስቸኳይ መቆም አለበት ”
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)
የመንደር 20 እና መንደር 21 ነዋሪዎች በዋናነት የአማራ ብሄር ተወላጆች መሆናቸውን መረዳቱንም የገለፀው ኢሰመኮ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ወደ አካባቢው መድረሳቸው ቢናገርም ነዋሪዎቹ ግን ወደ ሌላ ቦታ ሄደው መጠለላቸውን ቀጥለዋል በማለት አስረድቷል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) “በአካባቢው የቀጠለው የጸጥታ ችግር እና በነዋሪዎች ላይ እየደረሰ ያለው ብሔር ተኮር ግድያ በአስቸኳይ መቆም አለበት ” ሲሉ አሳስበዋል። በተጨማሪም የንፁሃንን ሞት ለመከላከል መንግስት የፀጥታ ኃይሉን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።
በታጣቂዎች በተፈፀመ ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የዐይን እማኞች ለቢቢሲ አማርኛ የተናገሩ ሲሆን ሕጻናትን ጨምሮ ከ150 በላይ ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀረ አክለው ተናግረዋል። ጥቃቱ በአካባቢው የሚኖሩ በርካታ የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።
የመንግሥት ኮሙኑኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ሰኔ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ በቄለም ወለጋ፣ በምዕራብ ወለጋ እና በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞኖች የሚገኙ ወረዳዎች በተቀናጀ የፀጥታ ኃይል እርምጃ በመንግሥት ቁጥጥር ስር ሙሉ በሙሉ መግባታቸውን አስታውቀዋል።
“በአካባቢዎቹ በተለያዩ ጫካዎች የተደበቁ፤ አሳቻ ቦታዎች የመሸጉ ቡድኖችን ለማፅዳት የፀጥታ አካላትና ህዝቡ አሰሳ እያደረጉ ይገኛሉ” ሲል በመግለጫው አክሎ የገለፀ ቢሆንም ታጣቂዎቹ በትናትናው እለትም ከሰኔ 11 ቀኑ ተመሳሳይ ጥቃት በድጋሜ ተፈፅሟል፡፡
ጥቃቱን ፈፅሟል የተባለው የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት የአለም አቀፍ ቃል አቀባይ የሆኑት ኦዳ ተርቢ ቡድኑ ጥቃቱን አልፈፀመም ሲሉ በትዊተር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል፡፡
ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም. በምዕራብ ወለጋ ዞን ኦሮሚያ ክልል ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ከ 200 በላይ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የተለያዩ ዘገባዎች ዋቢ አድርጎ አዲስ ስታንዳርደ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም. በምዕራብ ወለጋ ዞን ግምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ስለነበረው ጥቃት ባወጣው መግለጫ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (መንግስት “ሸኔ” ብሎ የሚጠራው) መካከል “ከነበረው ውጊያ ጋር በተያያዘ በታጣቂው ቡድን በአካባቢው በሚኖሩ ሲቪል ሰዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት በሰው ሕይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል” በማለት ተናግሯል። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ መንግሥት በሲቪል ሰዎች ላይ ተጨማሪ ጥቃት እንዳይፈጸም አስፈላጊ የሆኑ የመከላከል እርምጃዎችን እንዲወስድ፣ በማንኛውም ሁኔታ ሲቪል ሰዎች የጥቃት ዒላማ እንዳይደረጉ ተገቢ የሆነ ጥንቃቄና ጥበቃ እንዲያደርግ፣ እንዲሁም ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያፈላልግ አሳስበዋል።አስ