ዜና፡ የአፋር ህዝብ ፓርቲ ኢዜማ ያወጣው መግለጫ ላይ ማስተካከያ እንዲያደርግ አሳሰበ


አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18/ 2014 ዓ.ም፡- የአፋር ህዝብ ፓርቲ ኢዜማ በሶማሌ እና አፋር አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰተውን ግጭት በተመለከተ ትናንት ነሐሴ 17 ቀን  ያወጣውን መግለጫ የአፋርን ክልላዊ ሉዓላዊነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባና በህዝባችን ውስጥ ቁጣን በመቀስቀሱ ማስተካከያ እንዲያደረግ ሲል አሳሰበ

የአፋር ህዝብ ፓርቲ ባወጣው መግለጫ የኢዜማ መግለጫ ፍሬ ነገር የአፋርን ህዝብ የራሱን ክልል በራሱ የማስተዳደርና ክልላዊ ሉዓላዊነቱን ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ሆኖ አግኝተኗል ብሏል፡፡ ይህም በህዝባችን ውስጥ ቁጣን የቀሰቀሰ  በመሆኑ ኢዜማ በመግለጫው ላይ ማስተካከያ እንዲያደረግ እንጠይቃለን ሲል አክሏል።  

ፓርቲው ግጭቱ የተነሳው በአፋር ክልል እምብርት መሆኑና በአፋርና ሶማሌ ክልልሎች መካከል ግጭት አለመኖሩ እየታወቀ እና አፋሮች በቤታቸው ውስጥ ለጥቃት ከመዳረጋቸውም በላይ ከሠመራ አዋሽ አዲስ አበበ የሚወስደው መንገድ ለሁለት አመት ገደማ ለአፋሮች እርም ተደርጎ የነበረ መሆኑ እየታወቀ፤ እዜማ  “….በሰላማዊ መንገድ ሊፈታ የሚገባው የአስተዳደር ወሰን ጉዳይ..” ማለቱ ወይ ከግንዛቤ እጥረት አልያም ሆን ተብሎ ወገንተኝነትን ለማሳየት የተደረገ ሙከራ ነው ብለን የምናምን በመሆኑ ማስተካከያ እንዲደረግባቸው እናሳስባለን ብሏል። 

በፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የሚመራው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ትናንት መግለጫ ያወጣ ሲሆን በመግለጫውም የአፋር እና የሱማሌ ክልል አመራሮች ከህወሓትና አልሻባብ በኩል የተሞከረባቸውን ጥቃት ለመመከት ባሳዩት ትዕግስት እና ቁርጠኝነት ልክ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች ላይ በተደጋጋሚ ለሚፈጠሩ ችግሮች ልዩ ትኩረት ሰጥተው ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት እንዲሰሩ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

ኢዜማ አክሎም በሰላማዊ መንገድ ሊፈታ የሚገባው የአስተዳደር ወሰን ጉዳይ ዜጎችን ለተጨማሪ የሰላም እጦትና የደኅንነት ችግር እንዲዳርግ መፍቀድ የሚያሳድረው ጉዳት ከክልሎቹ አልፎ ለአጠቃላይ ሀገሪቱ ስጋት ከመሆን በተጨማሪ ለውጭ ሀይሎች መግቢያ ቀዳዳ እንደሚከፍት መረዳት ያስፈልጋል ብሏል፡፡ ፓርቲው የክልሎቹ አመራሮችም የማሕበረሰቡን ጥቅም እና የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ቅድሚያ በመስጠት ዘላቂ መፍትሔ እንዲመጣ ከግማሽ መንገድ በላይ ተጉዘው ለጋራ ሰላምና ተጠቃሚነት መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲል አክሏል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.