ዜና፡ የጉራጌ ዞን የክልል አደረጃጀት ጥያቄን የደገፉ አመራሮች ታሰሩ



የታሰሩ የጉራጌ ዞን አመራሮች ምስል- ማህበራዊ ድረገፅ



ነሐሴ 17፣ 2014 ዓ. ም፣ አዲስ አበባ፡-  ከጉራጌ ዞን የክልል አደረጃጀት ጋር በተያያዘ የዞኑ አመራሮች እና  የመምሪያ ኃላፊዎች መታሰራቸውን ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የመንግስት ሰራተኛ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናገሩ።

የዞኑ ፋይናንስ መምሪያ ኃላፊ አቶ ምነወር  ሀያቱ፣ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወ/ ማሪያም፣ አቶ አበበ አመርጋ የዞኑ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ ኃላፊ እና አቶ አጅመል  የወልቂጤ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ም/ዲን መታሰራቸውን እኝሁ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት ግለሰብ  ለዘጋቢያችን ተናግረዋል።

በተጨማሪም አቶ አለማየሁ ገ/መስቀል የጉራጌ ዞን የብልፅግና ፓርቲ የገጠር ዘርፍ ሀላፊ፣ አቶ መስፍን ተካ የጉራጌ ዞን የፀጥታ መምሪያ ሀላፊ፣ አቶ ሸምሱ አማን የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ሀላፊ አቶ ታምራት ውድማ የጉራጌ ዞን ግንባታ እንዲሁም የመሠረተ ልማት መምሪያ ሀላፊ እና ሌሎች ወጣቶችም መታሰራቸው ታውቋል፡፡

አዲስ ስታንዳርድ ጉዳዩን አስመልክታ ጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚንኬሽን ቢሮ ስልክ የመታች ሲሆን በቢሮው የሚሰሩ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ባለሙያ “ጉዳዩ በኮማንድ ፖስት የሚመራና በህግ የተያዘ ስለሆነ እኛ ምንም መረጀ መስጠት አንችልም” ብለዋል። አዲስ ስታንዳርድ በተያያዘ ወልቂጤ ከተማ ነዋሪነታቸውን ያደረጉ የመንግስት ሰራተኛ  ያናግረች ሲሆን ስማቸው እንዳይጠቀስ ጠይቀው ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የታሰሩ ሰዎች እንዳሉ ተናግረው በዝርዝር እንነማን እንደሆኑ ግን እንዳማያቁ ተናግረዋል። 

ይህ በንዲህ እንዳለ አዲስ ስታንዳርድ በኮማንድ ፖስቱ አመራር ስር የሚሰሩትን ኮማንደር ጠጄ [የአባት ስም ሳይጠቀስ ስልኩ የተቋረጠ] አነጋግራ “ይህ የተባለው እስር ስለመኖሩ አለውቅም። የተጣራ መረጃ ሲኖር ወደፊት እናሳውቃለን” የሚል ምላሽ አግኝታለች።

በተያያዘ መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው ዓለም አቀፍ የጉራጌ ማህበር  (ዓጉማ) የጉራጌ ክልል እንሁን ጥያቄ ጋር በተያያዘ  በዞኑ ባሉ የጉራጌ ማሕበረሰብ ላይ የሚፈፀም እስር ውክቢያ እና እንግልት እንዲቆም አሳስስቧል

ማህበሩ ባወጣው መግለጫ የሕዝብ እንደራሴዎች ያጸደቁት የጉራጌ ክልል እንሁን ጥያቄ ለመቀልበስ በተከታታይ እየሰራ ያለው “የብልጽግና ፓርቲ እና እሱ የሚመራው የመንግሰት መዋቅር”  የሕዝብን ጥያቄ ለመቀልበስና ለማፈን ተከታታይ እና የተጠና ግፊት  እያደረገ ነው ያለ ሲሆን  ነሐሴ 05 ቀን 2014 ዓ/ም በተካሄደው ዳግም የዞኑ  የምክር ቤት ስብሰባ ውድቅ ሆኗል ብሏል፡፡

መግለጫው አክሎም “ሐሳቡ ውድቅ የሆነበት የብልጽግና ፓርቲ እና እሱ የሚመራው መንግሰት የሕዝብን ጥያቄ መመለስ ትቶ ጉራጌ ዞን ላይ ባሰፈረው  የደህንነትና ጸጥታ መዋቅር እና የኮማንድ ፖስት አማካይነት ሕዝቡን በጅምላ እያሰረ ይገኛል” ሲልም ትችት አቅርቧል።

በተያያዘ ማህበሩ የደቡብ ክልል ከፍተኛ አመራሮችን የተቸ ሲሆን “የጉራጌ ጥያቄ መመለስ አለበት ብለው ከሕዝብ ጎን የቆሙ የጉራጌ አመራሮች እና ትግሉን የሚመሩ ወጣቶችን በማሰር ላይ ይገኛል” ሲል በመግለጫው አትቷል፡፡ 

ማህበሩ በመግለጫው“ሕዝብን በማፈንና በማሰር የሚገኝ ጥቅም የለም፡፡ የሕዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ የሚደረገው እንቅስቃሴም ይበልጥ ግለቱ ይጨምር እንጂ በፍጹም የሚቀንስ አይደለም” ያለ ሲሆን፣ የብልጽግና ፓርቲ እና እሱ የሚመራው መንግሰት በዘመቻ የጀመረው እስር እና አፈና ባስቸኳይ እንዲያቆም፣ አሁን ያሰራቸው የጉራጌ ልጆች ባስቸኳይ እንዲፈታ፣ የክልልነት እንሁን ጥያቄው እየተጠየቀ ያለው ያለምንም አመጽ በሰላማዊ መንገድ በመሆኑ ሕዝቡ የጠየቀው የክልልነት ጥያቄ ባስቸኳይ ሪፍረንደም እንዲደረግ እንዲያደርግ፤ እንጠይቃለን ብሏል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚ/ር አብይ አህመድ፣ ፓርቲያቸው እና መንግስታቸው በጉራጌ ሕዝብ ላይ እየፈጸመ ያለው እስር እንግልት እና አፈና እንዲያቆም እና ለሕዝቡ ሕጋዊ ጥያቄ ሕጋዊ ምላሽ እንዲሰጥ አበክሮ የጠየቀው ማህበሩ፣  የመንግስት አካል የሆኑት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እና የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምም ይህንን የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብት ረገጣ ከወዲሁ በአንክሮ እንዲከታተሉና ለማዕከላዊ መንግስትም  ምክረ ሃሰብ እንዲሰጡ አሳስቧል፡፡ 

ነሐሴ 12/2014 ዓ.ም. የደቡብ ክልል ኮማንድ ፖስት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ላልተወሰነ ጊዜ በጉራጌ ዞን ወረዳዎችና ከተማዎች ማንኛቸውም መንግስታዊ ይሁን መንግስታዊ ያልሆኑ ስብሰባዎች እና ዉይይት ማድረግ መከልከሉን አዲስ ስታንዳርድ መዘገቧ ይታወሳል

የክልሉ ኮማንድ ፖስት ከነሐሴ 12 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ማንኛውም ሰልፍና መሰል እንቅስቃሴዎችን ማካሄድ እና የንግድ ሱቆችና ተቋማትን ያለምንም ምክንያት መዝጋት የከለከለ ሲሆን የባጃጅ እንቅስቃሴ እስከ ምሽት 2 ሰአት ድረስ እንዲሁም የሞተር ሳይክል እንቅክቃሴ እስከ ምሽት 1ሰአት ብቻ እንዲሆን መገደቡ ይታወቅል።

ኮማንድ ፖሰቱ በመንግሥት የስራ ሰአት የቢሮ ሀላፊም ይሁን ባለሙያ በቢሮ አለመገኘት እንደማይቻል ገልፆ ይህን ትእዛዝ በሚተላለፉ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስድም አስታውቋል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.