እለታዊ ዜና፡ በአፋር እና ሱማሌ ክልል አዋሳኝ ግጭት የፌደራል መንግሥት ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጥ ኢዜማ አሳሰበ


በብሩክ አለሙ @Birukalemu21

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17/2014 ዓ.ም፡- በአፋር እና ሱማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ያለውን የእርስ በእርስ ግጭት የፌደራል መንግሥት ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጥ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አሳሰበ፡፡

በፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የሚመራው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በዛሬው እለት መግለጫ ያወጣ ሲሆን በመግለጫውም የአፋር እና የሱማሌ ክልል አመራሮች ከህወሓትና አልሻባብ በኩል የተሞከረባቸውን ጥቃት ለመመከት ባሳዩት ትዕግስት እና ቁርጠኝነት ልክ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች ላይ በተደጋጋሚ ለሚፈጠሩ ችግሮች ልዩ ትኩረት ሰጥተው ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ፓርቲው በመግለጫው በአካባቢው የተከሰቱት የጎርፍ አደጋዎች፣ ጦርነት ያስከተላቸው መፈናቀሎች፣ በድርቅ ሳቢያ የተፈጠሩ ችግሮች፣ ከፍተኛ የሆነ የኑሮ ውድነት እና የመሳሰሉት ጫናዎች በማሕበረሰቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ የፈጠሩት እንቅፋቶች ውስብስብ በሆነበት በዚህ ወቅት በሰላማዊ መንገድ ሊፈታ የሚገባው የአስተዳደር ወሰን ጉዳይ ዜጎችን ለተጨማሪ የሰላም እጦትና የደኅንነት ችግር እንዲዳርግ መፍቀድ የሚያሳድረው ጉዳት ከክልሎቹ አልፎ ለአጠቃላይ ሀገሪቱ ስጋት ከመሆን በተጨማሪ ለውጭ ሀይሎች መግቢያ ቀዳዳ እንደሚከፍት መረዳት ያስፈልጋል ብሏል፡፡

በማከልም የፌደራሉ መንግሥት የክልሎቹን ወቅታዊ ሁኔታ አስቸጋሪነት በመረዳት ለጉዳዩ ከፍተኛ አትኩሮት ሰጥቶ በአካባቢው ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ የጎሣ መሪዎች፣ የሐይማኖት አባቶች እና የሚመለከታቸው አካላትን ሁሉ በማስተባበር ዘላቂ ሰላም የሚሰፍንበትን መንገድ በአፋጣኝ ማፈላለግ ይኖርበታል ሲል አሳስቧል፡፡

ኢዜማ የክልሎቹ አመራሮችም የማሕበረሰቡን ጥቅም እና የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ቅድሚያ በመስጠት ዘላቂ መፍትሔ እንዲመጣ ከግማሽ መንገድ በላይ ተጉዘው ለጋራ ሰላምና ተጠቃሚነት መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲል አክሏል፡፡ 

ባሳለፍነው ሀሙስ ነሐሴ 12/2014 ዓ.ም የሶማሌ ክልል ኮሙኒኬሽን በሶማሌ እና አፋር ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በሚገኙ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የተፈናቀሉ ዜጎች በአስከፊ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ አስታውቋል።

ከመኖሪያ ቀዬአቸው የተፈናቀሉት ዜጎች በአሁኑ ወቅት በሲቲ ዞን ኤረር ወረዳ አስቡሊ እና በድዌይ በሚባል አካባቢ የተሰባሰቡ ቢሆንም በክረምቱ ከባድ ዝናብ ምክንያት መንገዶች በመቆራረጣቸውና ወደ አካባቢው ተሽከርካሪ ሊገባ ባለመቻሉ ምንም አይነት የእለት ደራሽ እርዳታ ለማቅረብ ያልተቻለ መሆኑን የክልሉ መንግስት ገልጿል።

በአሁኑ ወቅት ተፈናቃዮቹ በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ የጠቀሰው ኮሚኒኬሽኑ የክልሉ መንግስት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመቀናጀት አፋጣኝ እርዳታ ለማቅረብ ከፍተኛ ጥረትና ርብርብ እያደረገ እንደሆነ ገልፆ የሶማሌ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ ሙሀመድ እና ም/ርዕሰ መስተደድር ኢብራሂም ኡስማን የተካተቱበት የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ልኡካን ቡድን ተፈናቃዮች በሚገኙበት በሲቲ ዞን በመገኘት ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ በማስተባበር ላይ እንደሚገኙ መገለፁ የሚታወስ ነው።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.