አዲስ አበባ፣ ህዳር 9/ 2015 ዓ.ም፡– የትራንስፓርት አገልግሎት በሚሰጡ የራይድ ሹፌሮች ላይ በተደራጀ ሁኔታ ግድያንና ከባድ ወንጀልን በፈፀሙ 12 ተጠርጣሪዎች ላይ በከባድ ወንጀል ክስ መመስረቱን ፍትህ ሚንስቴር አስታወቀ፡፡
ሰዎችን በመግደል ውንብድ እና በህገ-ወጥ መንገድ ገንዘብን በመሰብሰብ ከባድ ወንጀል ክሱን የመሰረተው ወንጀሎቹ ከተፈፀሙበት ጊዜ ጀምሮ የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ከአዲስ አበባ ፓሊስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር መረጃዎችን የመመርመር ስራውን በማጠናቀቁ ነው፡፡
ወንጀሉን ሲፈፅሙ የነበሩ ሰዎችን በመያዝ እና ከዘጠኝ የምርመራ መዝገቦች መካከል ስድስቱን በማጠናቀቅ በወንጀል ተጠርጣሪዎች ላይ ከባድ የወንጀል ክስ መመስረቱን ሚኒሰቴር መስሪያ በቱ ይፋ አድርጓል፡፡
ወንጀሉን የሚፈፅሙ ቡድኖች ወንጀሉን ከመፈፀማቸው በፊት ከሹፌሮቹ ጋር መልካም ግንኙነት በመፍጠር ተበዳይ በሆኑት ሹፌሮች ላይ እምነት እንዲያድርባቸው ካደረጉ በኋላ መሆኑንም መግለጫው ጠቁሟል፡፡
ወንጀሉን የሚፈፅሙት ከአዲስ አበባ ውጭ ወዳሉ ከተሞች የትራንስፓርት አገልግሎት እንዲሰጣቸው በአዲስ አበባም ራቅ ወዳሉ ሰዎች ወደማይበዙባቸው ቦታዎች በምሽት እንዲያደርሷቸው በማድረግ ነው ብሏል መግለጫው፡፡
መግለጫው አክሎም የምርመራ ግኝቱ እንደሚያመላክተው አሽከርካሪዎችን በስለት በመውጋት፣ በገመድ አንገታቸውን በማነቅና በሽጉጥ ተኩሰው በመግደል አስክሬናቸውን በመጣል ተሽከርካሪዎቹንና ሌሎች ንብረቶችን ይዘርፋሉ ብሏል፡፡
ተሽከርካሪዎችን ከዘራፊዎቹ በዝቅተኛ ዋጋ ያለምንም ህጋዊ ሰነድ በመግዛት አይነታቸውን በመቀየር፣ ታርጋ በመለጠፍ ለሽያጭ የሚያቀርብ ሌላ የተደራጀ ቡድን መኖሩንም በምርመራ መረጋገጡን ፍትህ ሚንስቴር አስታውቋል፡፡
አብዛኛዎቹ ወንጀል ፈፃሚዎች መዋላቸውን የጠቆመው መግለጫው ክስ በተመሰረተባቸው መዝገቦች ላይ ቡድኑ ሶስት የሚሆኑ ሰዎችን በመግደል ሟቾች ሲያሽከረክሩት የነበሩ ተሽከርካሪና ሌሎች ንብረቶችን የወሰዱ ይገኙበታል፡፡
አዲስ ስታንዳርድ በሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም በራይድ ታክሲ የትራንስፓርት አገልግሎት በሚሰጡ አሽከርካሪዎች ላይ ሞት እና ዘረፋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ መምጣቱን በተመለከት ትንታኔ መስራቷ ይታወሳል፡፡
በትንታኔውም ስድስት የሚሆኑ የግል የትራንስፖርት ሰጪ አሽከርካሪዎች መሞታቸውን የተለያዩ ሚዲያዎች ዋቢ በማድረግ ተዘግቧል፡፡
በወቅተሩ በርካታ ተሸከርካሪዎችም እየተዘረፉ መሆናቸውንና በ15 ቀን ውስት ብቻ ዘጠኝ የግል ትራንስፖርት ተሸከርካሪዎች የኮድ 3 ሜትር ታክሲ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች መዘረፋቸውን አስነብቦ ነበር፡፡ አስ