ዜና ትንታኔ፡ እየተበራከተ የመጣው የግል ትራንስፖርት ሰጪ አሽከርካሪዎች ሞት እና ዘረፋየአሽከርካሪዎች ተቃዉሞ በስራ ባልደረቦቻቸው ላይ እየተደረገ ያለውን በጭካኔ የተሞላ ግድያ አስመልክቶን ሀምሌ14 ምስል ከእስክሪን የተወሰደ

በብሩክ አለሙ @Birukalemu21

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28/2014 ዓ.ም፡-የግል የትራንስፖርት ሰጪ አሽከርካሪዎች ሞት እና ዘረፋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ መጥቷል፡፡ እስካሁንም ድረስ ስድስት የሚሆኑ የግል የትራንስፖርት ሰጪ አሽከርካሪዎች መሞታቸውን የተለያዩ ሚዲያዎች እየዘገቡ ይገኛል፡፡በርካታ ተሸከርካሪዎችም እያተዘረፉ ሲሆን በ15 ቀን ውስት ብቻ ዘጠኝ የግል ትራንስፖርት ተሸከርካሪዎች (የኮድ 3 ሜትር ታክሲ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች) ተዘርፈዋል፡፡

በኮድ 3 የግል አውቶሞቢል የትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጡ ጥቃት ከተፈፀመባቸው መካከል ቴዎድሮስ አበባው (ቴዲ ቡናማው)፣ አቤል አማርከኝ፣ ሳላሃዲህ ሀሰን፣ ይበልጣል፣ አቶ ሀብቴ ተመስገን የተባሉ በእድሜ የገፉ የ3 ልጆች አባት እና፣ ተወልደ የተባሉ አሽከርካሪዎች ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ሹፌሮች ተሳፋሪ ነን ብለው በተሳፈሩ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ ናቸው።

የሰሌዳ መለያ ቁጥር ኮድ 3 ያላቸው የግል የከተማ ውስጥ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች አሽከርካሪዎች እና ባለንብረቶች ” ሞት ይብቃ ፣ መንግሥት የደኅንነት ከለላ ይስጠን” ሲሉ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በመዲናይቱ አዲስ አበባ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ መንግስት አስፈላጊውን የደህንነት ጥበቃ እንዲያደርግለቸው መጠየቃቸው ይታወሳል። ከተለያዩ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች ጋር በሚያደርጉት የሥራ ግንኙነት ውል መሠረት የሚሠሩት አቤቱታ አቅራቢ አሽከርካሪዎች ተሳፋሪ መስለው አገልግሎት በሚጠይቁ ወንበዴዎች እና ነፍሰ ገዳዮች በስለት ተወግተው እየተገደሉ፣ በገመድ እየታነቁ ከመገደላቸው ባለፈ ንብረታቸውም እየተዘረፈ መሆኑን  በምሬት ገልፀዋል

ማክሰኞ ሐምሌ 12 ቀን 2014 ዓ.ም የኤሌክትሮኒክ ትራንስፖርት በመስጠት ላይ የነበረ ሳላዲን ሐሰን የተባለ ሹፌር ገርጂ 24 ልዩ ቦታው ኤርትራ ቆንጽላ የሚባል አካባቢ ከቀኑ 10 ሰዓት በስለት ተወግቶ ተገድሎ መኪናው ተዘርፏል። አዲስ አበባ ከተማ 70 ደረጃ አካባቢ ተወልዶ ያደገው ሳላዲን ሐሰን የ24 ዓመት ወጣት ሲሆን የግል ታክሲ አገልግሎት በመስጠት ቤተሰቦቹን ለመርዳትና ኑሮን ለማሸነፈፍ የሚጥር አሽከርካሪ ነበር፡፡

የሰላዲንን ግድያ ተከትሎ የራይድ ሹፌሮች ተሰባስበው ለሰላዲን ፍትህ እንዲሰጠው ጠይቀዋል። ሹፌሮቹ በመዲናችን አዲስ አበባ መሰል የወንጀል ድርጊቶች መበራከታቸው ጠቅሰው፤ “እየሰሩ መሞት ይብቃ” የሚል መሪ ቃል በመያዝ  መንግስት ለጉዳዩ የተለየ ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል። በአዲስ አበባ በጠራራ ጸሀይ ጋሻ መከታዬ የሚሉትን ልጃቸውን የተነጠቁት የሳለዲን እናትና አባት ፍትህ ይሰጠን ሲሉ በሲቃ ሲማፀኑ ቆይተዋል። የልጃቸው ሞት ለማመን የከበዳቸው እናቱም ፤ መንግስት የጸጥታ አካላት የልጄን ገዳይ ለህግ ያቅርብልኝ ሲሉ ተማፅነዋል።

በበጎ ስራዎቹ እና በኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ደጋፊነቱ የሚታወቀው ወጣት ቴዎድሮስ አበባው(ቴዲ ቡናማው) መጋቢት 6 ቀን 2013 ዓ/ም በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ቤተል አዲስ ተስፋ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በግምት ከምሽቱ 5 ሰዓት ገደማ ባልታወቁ ሰዎች በተፈፀመበት ወንጀል ህይወቱ አልፎ መገኘቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል፡፡

በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ግለሰቦች ላይ ተመሳሳይ ወንጀሎች ተፈፅመው ፖሊስ ባደረገው ክትትል ፈፃሚዎቹን በአጭር ቀናት ውስጥ በቁጥጥር ስር አውሎ ለህዝብ ይፋ ማድረጉን ያስታወሰው ኮሚሽኑ በተለይም የግል ትራንስፖርት አገልግሎት በሚሰጡ አሽከርካሪዎች እና ተሽከርካሪዎች ላይ ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ 8 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ በማጣራት ላይ እንደሚገኝም በጊዜው አክሎ አስታውቋል ።

በተመሳሳይ የራይድ ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ሰኔ 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ከቤቱ የወጣው የሶስት ልጆች አባት የነበረው ሀብቴ ተመስገን ለ15 ቀን የት እንደደረሰ ሳይታወቅ ቆይቶ ፖሊስ ቱሉ ዲምቱ አካባቢ ላይ ተገድሎ ማግኘቱን ለቤተሰብ አሳውቋል። ልጆቹን ለማሳደግ በዚህ ስራ ላይ የተሰማራው ይህ አባት ያሳፈራቸው ግለሰቦች ገድለውት ልጆቹን ያለ አባት ማስቀረታቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

በሰኔ ወር ሚኪያስ ተፈሪ የተባለ ራሱንና ቤተሰቡን ለማስተዳደር ራይድ የሚሰራባትን መኪና ይዞ እንደተለመደው ቆሞ ሥራ ይጠባበቃል። ሥራውም ከራይድ ኮል ሴንተር ተደውሎ ከሳሪስ ጀሞ ሥራ እንዲሄድ ይጠየቃል። ሚኪያስም እንጀራው ነውና የድርጅቱን ትእዛዝ ተቀብሎ ሦስት ሰዎችን አሳፍሮ ወደታዘዘበት ጀሞ ይሄዳል። ጀሞ እንደደረሱ  በያዙት ስለት ሚኪያስን አስፈራርተው መኪናውን ነጥቀው ተሰውረዋል።

ህአይነቱ ድርጊት በከተማዋ ውስጥ እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ የግል ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ሹፌሮች አገልግሎቱን የሚሰጡት ብቻቸውን ስለሆነ እንዲሁም አግልግሎት የሚሰጡበት ስማርት ስልኮች እና የሰሩበትን ብር ስለሚይዙ የስራ ዘርፉን  ለዘረፋ እና ለግድያ ወንጀል አመቺ አድርጎታል ሊባል ይችላል፡፡

አዲስ ስታንዳርድ ያናገረቻቸው የግል ትራንስፖርት ሰጪ ሹፌሮች መንግስት በከተማው ውስጥ እየተስተዋለ ያለውን የፀጥታ ስጋት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራበት አሳስበዋል፡፡ ሹፌሮቹ በመዲናዋ ውስጥ ዘረፋና ግድያ አየተበራከተ በመምጣቱ  ሰርቶ መብላትና በነፃነት መንቀሳቀስ አስቸጋሪ እንደሆነባቸውም አክለው ገልፀዋል፡፡

ስሙ እንዲገለፅ ያልፈለገ የራይድ አሽከርካሪ ከአዲስ ስታንዳረድ ጋር ባደረገው ቆይታ በከተማዋ ውስጥ ያለው የፀጥታ ሃይል ማነስ የዝርፊያና የግድያ ወንጀሎች እንዲበራከቱ አስችሏል ያለ ሲሆን አክሎም የግል ትራንስፖርት ተሸከርካሪዎች  ሲዘረፉ ተከታትሎ የሚያስመልስ አካል ባለመኖሩ ዘራፊዎቹ የሹፌሮችን ህይወት እያጠፉ ተሸከርካሪዎቻቸውን የመዝረፍ ተግባራቸውን ቀጥለውበታል ሲል ያስረዳል፡፡

ስሜ አይጠቀስ ያለ ሌላኛው አሽካርካሪ ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ቆይታ ያደረገ ሲሆን እየተፈፀመ ያለው ወንጀል አሳሳቢ ከመሆኑ የተነሳ የስራ ሰዓቱን ለመቀነስ እንዳስገደደው ተናግሯል። “የማሽከረክረው ቶዮታ ቪትዝ ሲሆን ለማለንብረቱ የነዳጅ ወጪን ችዬ በቀን 700 ብር ማስገባት ይጠበቅብኛል።የቤተሰብ አስተዳዳሪ ከመሆኔም ባሻገር የምንኖረው በኪራይ ቤት ነው። ለልጆቼ መኖር ስላለብኝ ለአይን ከያዘ በኋላ ማሽከርከር አቆማለሁ” ሲል ያለበትን ፈተና አስረድቷል። አክሎም የራይድ እና መሰል አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች የአሽከርካሪውን ደህንነት ሊያስጠብቁ የሚችሉ መተግበሪያ ወይም የተሳፋሪውን ማንነት የሚያረጋግጥ የህግ ከለላ ሊሰጡ ይገባል ያለ ሲሆን ዘርፉ ይህን የማያደርግ ከሆነ አሽከርካሪው፣ ተጠቃሚው እና ኩባንያዎች ወዳልተፈለግ እንግልት ሊያመሩ እንደሚችሉ ተናግሯል። 

አዲስ ስታንዳርድ ቃለ መጠይቅ ካደረገችላቸው አሽከርካሪዎች መካከል ‘መልኬ’ [ስሙ በጠየቀው መሰረት የተቀየረ] አንዱ ሲሆን “በፈጣሪ ቸርነት እሱን አምኜ ወደ ስራ እገባለሁ” ሲል ያለውን አሳሳቢ ሁኔታ ተናግራል። ምንም እንኳን የሚያሽከረክረው መኪና የግሉ ቢሆንም በተደጋጋሚ የሚስተዋለው ዘግናኝ የግድያ እና ዝርፊያ ወንጀሎች ከዚህ በፊት ይሰራበት በነበረው ልክ እንደማይሰራ አስረድቷል። “ምንም አይነት ደህንነት አይሰማኝም፤ ስለሆነም በጊዜ ወደ ቤቴ እየገባሁ ነው” ያለው መልኬ “መንግስት አስፈላጊውን ክለላ ያድርግልን እንዲሁም በአገልግሎቱ የተሰማሩ ኩባንያዎች አስገዳጅ የደህንነት ማረጋገጫ ማዕቀፍ ውስጥ ሊገቡ ይገባል” ብሏል። 

ሌላኛው የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ “የግል ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ መስራት ስጋት ስለሆነብኝ በዋና መንገዶች ላይ ብቻ ያሉ ተሳፋሪዎችን ብቻ ማጓጓዝ ጀምሬያለው አምሽቸ መስራትም አቁሚያለው” ብሏል፡፡

የኮድ 3 ሜትር ታክሲ ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች እና ባለንብረቶች ማኅበር በአዲስ አበባ እስካሁን ስድስት አሽከርካሪዎች ተሳፋሪ ነን ብለው ጥሪ ባደረጉ አካላት በአሰቃቂ ሁኔታ ተግድለዋል ሲል መግለፁን ዶቸ ቨለ ዘግቧል። የሜትር ታክሲ አገልግሎት ማእቀፍ ዘርግተው አሽከርካሪዎችንና የ ኮድ 3 የግል አውቶሞቢሎችን አቅፈው የከተማ ውስጥ የሕዝብ ማጓጓዝ ሥራ ላይ የተሰማሩት ኩባንያዎች ለአሽከርካሪው ደኅንነት ዋስትና ሊሰጡ አልቻሉም የሚሉት አሽከርካሪዎቹ መንግሥት በሌሊት ይፈፀም የነበረው ግድያ እና የንብረት ቅሚያ በቀን ሲፈፀም በመደጋገሙ የጉዳዩን አሳሳቢነት ተገንዝቦ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

የኮድ 3 ሜትር ታክሲ ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች እና ባለንብረቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ሄኖክ ተስፋዬ “መንግሥት በየ ዓመቱ ከ 450 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ገቢ የሚሰበስብበት ዘርፍ ነው” በማለት እስከ 45 ሺህ የሚደርሱ አሽከርካሪዎችን አቅፎ የያዘውን ዘርፍ በትኩረት ሊመለከተው እንደሚገባ ገልፀዋል። አሽከርካሪዎቹ ከሰሞኑ መገደሉ ሳያንስ በልፋቱና በጥረት የገዛው ተሽከርካሪ ጭምር የተዘረፈበትን ሾፌር ለማሰብ በተሰባሰቡበት ወቅት ስጋታቸውን ጭምር ገልፀዋል።

መሰል ጥቃቶች መሃል ከተማ ውስጥ ከሌሊት  የጨለማ ጊዜ አልፎ በቀንም በጠራራ ፀሐይ መፈፀሙ ፍርሃት ውስጥ ከቷቸዋል። የኮድ 3 ሜትር ታክሲ ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች እና ባለንብረቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ሄኖክ ተስፋዬ አሽከርካሪዎቹን አቅፈው ከሚሰሩት የትራንስፖርት ኩባንያዎች መካከል ኢትዮጵያዊ ያልሆኑን ሰዎች በዚህን መሰል ወንጀል ውስጥ እየገቡ ስለሆነ መንግሥት ክትትል አድርጎ እርምት ሊወስድ ይገባል ሲሉም ተማጽነዋል። በኢትዮጵያ እየተለመዱ ከመጡ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መካከል የሆነዉ የሜትር ታክሲ አገልግሎት የመክፈል አቅም ላላቸው ሰዎች ተመራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት መሆን ከመቻል አልፈው  በብዙ ሺህዎች ሰፊ የሥራ እድል እንዲያገኙ ማድረግ ችሏል። ይሁን እና የአሽከርካሪዎች ካሰቡት ደርሶ በሰላም የመመለስ፣ የተሽከርካሪ ባለንብረቶች የንብረታቸው የመዘረፍ እና የተሳፋሪዎች ደህንነት ሥጋት ውስጥ እየወደቀ ይገኛል።

ራይድ የግል ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በተለያዩ ጊዜያት የተገበራቸውን የደህንነት ግንዛቤ ማስጨበጫ (Safety Features) እንዲሁም አሰራሮች ለሁሉም የራይድ አሽከርካሪዎች ተደራሽ በሆነ መልኩ በተለያዩ የአዲስ አበባ ክፍሎች ከሐምሌ 29 እስከ ነሃሴ 4 2014 ዓ.ም ድረስ የሚተገበር መርሃ-ግብር መዘጋጀቱን በማህበራዊ ገፁ አሳውቋል፡፡ ራይድ ይህ የደህንነት ማስጨበጫ መርሀ ግብር አባላቶቹን ሙሉ ግንዛቤ እንዲወስዱና ከድርጅቱ ሊያገኙ የሚችሉትን የደህንነት ቴክኖሎጂዎች መጥተው በፍጥነት እንዲተገብሩ ለማገዝ የታለመ ነው ብሏል፡፡

ድርጅቱ ይህን መርሃ-ግብር እንደሚዘጋጅ ያስታወቀው እየተበራከተ የመጣውን የሹፌሮች ግድያ እና የተሽከርካሪዎች ዝርፊያ መበራከቱን እንዲሁም የሰላዲን ግድያ ተከትሎ ነው፡፡

ራይድ የግል ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ከሐምሌ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ጥሪ ማእከል ሳይደወል ለሚደረጉ የትራንስፖርት አገልግሎት( street pick up) ሹፌሩ ደንበኛውን በስልኩ ፎቶ በማንሳት ምስሉን በቀጥታ ወደ ድርጀቱ ሰርቨር በመላክ ወንጀልን ለመከላከል ያስችላል ያለውን አሰራር እያተገበረ ይገኛል፡፡

ይህ ድርጅት ከዚህ በፊትም ለደህንነት ይረዳል ያላቸውን የተለያዩ አሰራሮችን ቢተገብርም የአሽርካሪዎች ሞትንና ዘረፋ ሊቆም ግን አልቻለም፡፡

የሰላዲን ሞትን ተከትሎ የራይድ አሽከርካሪዎች ፍትህ ለመጠየቅ በውጡበት ወቅት በ15 ቀናት ውስት ብቻ ወደ ዘጠኝ የሚሆኑ መኪናዎች መሰረቃቸውን ገልፀው በራሳችን ጥረጥ አንድ መኪና ብቻ ሊገኝ ችሏል ብለዋል፡፡ አክለውም ባለው ሁኔታ ወደ ስራ መግባት አለመቻላቸውን ጠቅሰው የሚያሰሩን ድርጅቶች ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግስት  አካል እጃቸውን አስገብተው እንዲያግዟቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አዲስ ስታንዳርድ የችግሩን አሳሳቢነት አስመልክታ ወደተባሉት የአገልግሎቱ ሰጪ ኩባንያዎች (በተለይ ራይድ እና ፈረስ) በተደጋጋሚ ስልክ ብትመታም የጥሪ ማዕከሉን ከማናገር ውጪ ጉዳዩ የሚመለከተውን ክፍል ማግኘት ሳትችል ቀርታለች። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.