አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2014 – በኦሮሚያ ልዩ ዞን ፊንፊኔ ዙሪያ በቡራዩ ከተማ በጸጥታ ሃይሎች እና የጥምቀት በዓል ተሳታፊዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የሁለት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በርካቶች ቆስለዋል።
የአይን እማኞች ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት የወይብላ ማሪያም ታቦታትን ከጥምቀተ ባህር ወደ መንበር በመመለስ ላይ የነበሩ ምእመናን የቤተክርስቲያኗ አርማ ያለበትን አረንጓዴ ቢጫ እና ቀይ ባንዲራ ይዘው ወደ ቡራዪ ከተማ እንዳይገቡ ተከልክለዋል። እንደ እማኞቹ ገለጻ የጸጥታ ሃይሎች አስለቃሽ ጥይት እንዲሁም ተኩስ ህዝቡ ላይ በመክፈታቸው ግጭቱ በፍጥነት ተባብሷል። ህጻናትና አዛውንቶችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች በመረጋገጥ መቁሰላቸውን እማኞቹ ተናግረዋል።
እማኞቹ ጥቃት ፈጻሚዎቹ የቡራዩ ከተማ ፖሊስ እንደሆኑ ሲገልጹ፣ አንዳንድ የአካባቢው ማህበረሰቦችም በህዝቡ ላይ ጥቃት እንደሰነዘሩ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመገናኛ ብዙኃን ቦርድ አባል በሰጠው አስተያየት የክልልና የፌዴራል የጸጥታ ኃይሎችን አስቀድመው ወደ አካባቢው ማሰማራት ባለመቻላቸው መንግሥትን ተጠያቂ አድርጓል።
የቡራዩ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ በበኩላቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ከፌደራል ፖሊስና ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጋር እንዲሁም ከክልሉ ፖሊስና ከአካባቢው ሚሊሻዎች ጋር በመሆን ሁኔታውን ለመቆጣጠር ጥረት በማድረግ ላይ እንደነበሩ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ስለሁኔታው ሲገልጹ “የአዲስ አበባ ወጣቶች በህግ የተከለከለውን ህገ ወጥ ባንዲራ ይዘው ወደ ቡራዪ ከተማ ለመግባት ሞክረዋል” ብለዋል። እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ ወጣቱ ታቦቱ ከመድረሱ በፊት ወደ ከተማዋ በመግባት የጸጥታ ሃይሎችን እና ብረት ለበስ ተሸከርካሪዎቻቸው ላይ ድንጋይ መወረወር ብሎም ከጸጥታ ሃይሎች የጦር መሳሪያ ለመውሰድ ሞክረው እንደነበር ተናግረዋል ። “ማን ተኮሰ የሚለውን ባናቅም የተኩስ ልውውጥ ተደርጓል። ” ሲሉ አስረድተዋል ። የጸጥታ ሀላፊው የቡራዪ ከተማ ነዋሪዎች ተጨማሪ አደጋ እንዳይፈጠር ማድረጋቸውን አመስግነዋል።
የደህንነት ኃላፊው አክለውም “በጠፋው የሰው ህይወት አዝነናል፣ አጥፊዎችም በህግ ይጠየቃሉ” ብለዋል። የፌደራል መንግስትም ድርጊቱን አጣርቶ ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ ቃል ገብቷል። አስ