ትንተና፡- የኑሮ ውድነት ቋሚ ገቢ ያላቸውን ዜጎች እየተፈታተነ ይገኛል

ጌታሁን ፀጋዬ

አዲስ አበባ ፣ ጥር7/2014 :- የዋጋ ንረት በበርካታ የአገሪቱ ዜጎች ኑሮ ላይ ትልቅ ተጽእኖ ቢኖረውም ደመወዛቸው ምንም ጭማሪ የሌለው የመንግስት ሰራተኞች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል።

“የዋጋ ግሽበት ገቢያቸው ዉስን የሆኑት እንደ መንግሥት ሰራተኞች፣ ጡረተኞች እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኮንትራት ሰራተኞች ላይ የከፋ ነው” በማለት  የገለልተኛ ኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ አቢስ ጌታቸው ያስረዳሉ።

የግብርና ሚኒስቴር ሰራተኛ የሆኑት ወይዘሮ ራቢያ የሱፍ  እንዳብራሩት እንደ ጤፍ፣ ሽንኩርት፣ ድንች፣ ቲማቲም ያሉ የግብርና ምርቶች በህዳር 2014 ዓ.ም ካለፉት ሁለት ወራት ጋር ሲነፃፀር ትንሽ የማይባል የዋጋ ጭማሪ አሳይቷል ብለዋል።

እንደሳቸው ገለፃ “አንድ ኪሎ ጤፍ በጥቅምት ወር 56 ብር  የነበር ሲሆን  በህዳር ወር ግን ወደ 59 ብር ከፍ ብሏል” በማለት አብራርተዋል።

የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በቅርብ ጊዜ ሪፖርቶቹ እንዳስታወቀው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት (በሀገር ደረጃ የሚንቀሳቀሰው የ12 ወራት አማካይ የዋጋ ግሽበት) ከአንድ ዓመት በፊት ተመሳሳይ ወቅት ከታየው ጋር ሲነፃፀር በህዳር 2014ዓ.ም በ25.5 በመቶ ከፍ ብሏል።

በሪፖርቱ መሰረት የምግብ የዋጋ ግሽበት ከፍተኛው ሲሆን ይህም እስከ 30.1 በመቶ  ጭማሪ ያሳየ ሲሆን ምግብ ነክ ያልሆኑ የዋጋ ግሽበት በህዳር 2014ዓም ከህዳር 2013ዓም ጋር ሲነጻጸር በ19.4 በመቶ ከፍ ብሏል። የ12 ወራት አማካይ የዋጋ ግሽበት ፍጥነት በሀገሪቱ ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበትን እንደሚያመለክት መሆኑን ኤጀንሲው ዘግቧል።

በተጨማሪም በህዳር 2014ዓ.ም ከአመት አመት የዋጋ ግሽበት ከህዳር 2012ዓ.ም ከታየው ጋር ሲነጻጸር  በ33 በመቶ ከፍ ብሏል። የምግብ የዋጋ ግሽበት ደግሞ በ38.9 በመቶ ጨምሯል። ኤጀንሲው እንደዘገበው በየወሩ ያለው የዋጋ ግሽበት በ0.6 በመቶ መቀነሱን እና የምግብ ግሽበቱ ከጥቅምት 2014 ጋር ሲነጻጸር በ1.7 በመቶ መቀነሱን አስታውቋል። 

 በህዳር ወር እህል፣ አትክልት እና ጥራጥሬ፤ በስጋ እና በወተት ተዋጽኦዎች ላይ በአንጻራዊ የዋጋ ቅናሽ ሲያሳዩ፣ቅመማ ቅመም (በተለይ ጨው እና በርበሬ) እና የምግብ ዘይት መጠነኛ ቅናሽ አሳይተዋል። በሌላ በኩል ቡና እና አልኮል አልባ መጠጦች  የተወሰነ ጭማሬ አሳይተዋል።

የአባቷ ስም እንዳይጠቀስ የጠየቀችው ወጣት ሲሳይ በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ የሽያጭ ሰራተኛ ስትሆን የዋጋ መናርን “አስደንጋጭ” በማለት ገልጻለች።ከደሞዝዋ ጋር ሲነጻጸር በገበያው የዋጋ ንረት ላይ ያላትን ግርምት በመግለፅ፣ “ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ የአንድ ኪሎ ብርቱካን ዋጋ 100 በመቶ ያህል ጭማሪ አሳይቷል። ከአሁን በኋላ ለመግዛት አቅም የለኝም” በማለት ተናግራለች።

ሌሎች ግን የገጠማቸው ትልቁ ፈተና የቤት ኪራይ ክፍያን ማረጋገጥ ነው ይላሉ። የአባቱ ስም እንዳይጠቀስ የጠየቀው በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነውና የመንግስት ሰራተኛው  አየለ  ሁኔታውን አስመልክቶ “መንግስት የሰጠውን የኪራይ ጭማሪ እገዳ ተከትሎ አከራዬ ቢያንስ ለጊዜው የቤት ኪራይ መጨመር አይችልም።ነገር ግን መግለጫው ሲያልቅ ይጨምራሉ ብዬ እሰጋለሁ” አክሎም፣ “ደሞዜ ምንም ጭማሬ ሳይኖረው የቤት ኪራይ በሚያስደነግጥ ሁኔታ እየጨመረ መሄዱ አሳሳቢ ነው” በማለት ስጋቱን ተናግሯል።

አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገራት ሌላኘዋ የመንግስት ሰራተኛ የሆነችው ትንሳኤ ስትሆን በአሁኑ ሰአት አባዶ ሳይት ባለ አንድ መኝታ ኮንዶሚኒየም ተከራይታ  ትኖራለች። “በየወሩ 6,500 ብር እየከፈልኩ ነበር ያለሁት ነገር ግን በተፈጠረው ግጭት ከወሎ የተፈናቀሉ ጓደኞቼ 7,500 ብር እንዲከፍሉ ተጠይቀዋል” ስትል ተናግራለች። ሆኖም አንዳንድ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እየተመለሱ በመሆኑ የቤት ኪራይ ከጥቂት ወራት በፊት ወደነበረበት እየተመለሰ ነው።” ብላለች።

ወይዘሮ ሜሮን አንተነህ በአዲስ አበባ የግል ትምህርት ቤቶች ክፍያ በመጨመሩ ቅሬታዋን ገልጻለች። ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገረችው  አሁን የ1ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው አንድ ልጇ ላለፉት ሶስት አመታት በዚሁ ትምህርት ቤት እየተማረ መሆኑን ተናግራ “ባለፈው አመት በየሩብ ዓመቱ 4,000 ብር እከፍል ነበር አሁን ግን 6,100 ብር እየከፈልኩ ነው። ይህም የ2,100 ብር ጭማሪ ሲሆን  በዓመት የ8,400 ብር ጭማሪ ነው”  አክላም “እኔና ባለቤቴ የምናገኘውን ገቢ ግምት ውስጥ በማስገባት ካሁን በኋላ ይህን ያህል የትምህርት ቤት ክፍያ መክፈላችንን እርግጠኛ አይደለንም ወይም ሌላ ልጅ የመውለድ እቅድ የለንም” በማለት ተናግራለች።

ነዋሪዎቹ የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠርና ለመቅረፍ መንግስት ከሚወስዳቸው እርምጃዎች የሚጠበቀውን ዉጤት በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ የደሞዝ ጭማሪው ጉዳዩን እንደሚፈታ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።በተያያዘም ሌሎች የአቅርቦት ሰንሰለት፣ የድርጅት ስግብግብነት እና የቤት ባለቤቶች ኃላፊነት የጎደለው ጭማሪ  ለችግሮች መባባስ ምክንያት መሆናቸውን በመግለጽ የተጠያቂነት መጥፋትን ለመፍታት እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል።

የችርቻሮ መሸጫ ሱቅ ባለቤት የሆኑት አቶ አብዲ ናጄ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት መንግስት ሰው ሰራሽ የዋጋ ጭማሪና የሸቀጦች እጥረትን በመፍጠር በተሳተፉ ግለሰቦች ላይ የቅጣት እርምጃ መውሰዱን ካስታወቀ ወዲህ ገበያው የተረጋጋ ነው። እንደ አብዲ አባባል፣ ይህ ሂደት ግን ዘላቂ አይደለም ብሏል።

“ከአንዳንድ የምግብ ዘይት፣ ወተትና ዱቄት በስተቀር ሌሎች የሚበሉም ሆነ የማይበሉ ዕቃዎች ዋጋ ወደ ቀድሞው እየተመለሰ ነው ” በማለት በመርካቶ የሚገኙ ጅምላ አከፋፋዮች ዋጋ ስለጨመሩ፣ የችርቻሮ ዋጋን ከመጨመር ውጪ ሌላ አማራጭ የለኝም” በማለት ተናግሯል።

ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ የነዳጅ ምርቶች ዋጋ መጨመር ነው። የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪው አቶ አሸናፊ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ “የህዝብ ማመላለሻና ሌሎች ሸቀጦች ዋጋ ሊጨምር ይችላል ብዬ እሰጋለሁ” ብለዋል። 

በታህሳስ ወር የፌደራል ባለስልጣናት በተለያዩ የነዳጅ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ማድረጉ የሚታወስ ነው። በታህሳስ ወር ማስተካከያ መሰረት ዋጋው ከ25.86 ብር ወደ 31.74 ብር አድጓል። በመሆኑም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ በህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የታሪፍ ማሻሻያ አድርጓል። 

በመንግስት የተወሰዱ እርምጃዎች

የገንዘብ ሚኒስቴር በህዳር እና ጥቅምት 2014ዓ.ም 4 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ እና 12.5 ሚሊየን ሊትር የምግብ ዘይት መግዛቱን አስታውቋል።እርምጃውም የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት ያለመ መሆኑን ሚኒስቴሩ የገለጸ ሲሆን፥ በጥቅምት ወር የነበረው የ34.2 የዋጋ ግሽበት በህዳር ወር ወደ 33.0 መቀነሱን አስታውሷል።

 ከዚህም በላይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ለመርዳት በማሰብ የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ለሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን ለማቅረብና የእህል የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት እስከ 500 ሚሊዮን ብር ብድር ለመስጠት ወስኗል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩሉ በበጀት አመቱ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ለግሉ ዘርፍ፣ ለግብርና ግብአት እና ለመንግስት ልማት ድርጅቶች ለማቅረብ ማቀዱን አስታውቋል።. ከዚህ ገንዘብ ውስጥ 25 ቢሊዮን ብር ለግሉ ሴክተር፣ 30 ቢሊዮን ለግብርና ግብአቶች፣ ቀሪው ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት እና የስራ እድል ፈጠራን ለማበረታታት የሚውል ነው። 

ባለፈው አመት ነሃሴ ወር መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኑሮ ውድነት ለመቅረፍ መሰረታዊ ሸቀጦችን በመደጎም ያቀደውን የዋጋ ግሽበት ከሁለት አሃዝ ወደ አንድ አሃዝ ለመቀነስ ማቀዱን ይፋ አድርጓል።

 መግለጫው “ከፌዴራል እስከ ወረዳ ድረስ ያለው ግብረ ኃይል ለኢንዱስትሪና ለግብርና ፍጆታ የሚውል ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ሳይኖር የዋጋ ጭማሪ በማድረግ በህብረተሰቡ ላይ ለከፋ ችግር በሚዳርጉ ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ እርምጃ እየወሰደ ነው” ብሏል።

ሚኒስቴሩ ስማቸው ያልተጠቀሱ ግለሰቦች በመሰረታዊ እቃዎች ላይ የሰው ሰራሽ እጥረት በመፍጠር የዋጋ ጭማሪ አድርገዋል ሲል ከሷል። የአቅርቦት ሰንሰለቱን በሚያውኩ ህገወጥ ተግባር ላይ በተሰማሩ ላይ እርምጃ እንደሚወሰድም አስጠንቅቋል።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ምን ይላሉ?

አቢስ ጌታቸው በኢትዮጵያ የዋጋ ንረት ላይ ሰፊ ጥናቶችን ያደረጉ ገለልተኛ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ እና ተመራማሪ ናቸው። አዲስ ስታንዳርድ የዋጋ ግሽበቱ በቋሚ ገቢ የሚኖሩ የመንግስት ሰራተኞችን እንዴት ተፅኖ እንደሚያሳድር ጠይቃ፣ አቢስ እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች በኢትዮጵያ ለሚታየው የማይቀር የዋጋ ግሽበት በጣም የተጋለጡ መሆናቸውን ተናግሯል። “የዋጋ ግሽበት እያሻቀባ  መሄዱ አሳሳቢ ሲሆን የወር ገቢያቸው የማይጨምረውን ህብረተሰብ ህይወትን አስቸጋሪ ያደርገዋል” ሲል አስረድቷል።

በችርቻሮ ነጋዴዎች እና በጅምላ አከፋፋዮች ላይ መንግስት በቅርቡያሳለውን ቋሚ የመሸጫ የዋጋ ትመናን በተመለከተ አቢስ  ጌታቸው ሲያብራሩ፣ እንዲህ ያሉት መለኪያዎች ገበያውን ለተወሰነ ጊዜ ለመቆጣጠር ያላቸው ሚና እምብዛም እንደሆነ አስረግጠው ተናግረዋል። መንግሥት በሀገሪቱ ያለውን አሳሳቢ የዋጋ ንረት ለመቀነስ ወይም ለማቃለል በሚያስችሉ ታላላቅ ኢኮኖሚ ፕሮጀክቶች ላይ ለመስራት ጥረት ማድረግም አለበት ብለዋል ።

አቢስ ለሲቪል ሰርቫንቱ የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ “የደመወዝ ጭማሪ በቋሚ ገቢ የሚኖሩ የመንግስትም ሆነ መሰል ሰራተኞችን የኑሮ ደረጃ አይፈታም። በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ በእቃዎች ላይ የዋጋ ንረት እንዲጨምር ያደርጋል ይህም ሌላ አለመረጋጋት ይፈጥራል’’ በማለት ስጋቻቸውን አጋርተዋል።

“የዋጋ ግሽበቱን ለማስተካከል ብዙም አልረፈደም” ያሉት ኢኮኖሚስቱ “መንግስት እና የሚመለከታቸው አካላት በቤቶች ፣በትራንስፖርት እና በኮርፖሬሽኖች ፕሮጀክቶች ላይ ሊሰሩ ይገባል” ብለዋል ። እነዚህ አካላት በተጠቀሱት ዘርፍ ላይ ስራ ከሰሩ በዝቅተኛ ዋጋ፣ ሸማቾች፣ ቋሚ ገቢ ያላቸውን ሰራተኞች ጨምሮ፣ በገቢያቸው መጠን ለመግዛት እድሎች ይኖራቸዋል በለዋል።

በተጨማሩም ብሄራዊ ባንክ ራሱን የቻለ ፖሊሲ እንዲያዘጋጅ መክረዋል። “የአገሪቱ ብሔራዊ ባንክ ተጠሪነቱ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሳይሆን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀጥታ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ አሁን እያጋጠሟት ያሉትን የተለያዩ የኢኮኖሚ ችግሮች ለማስተካከል የሚረዱ ፖሊሲዎችን በመንደፍ የበለጠ ነፃ ይሆናል ” በማለት አብራርተዋል።

በትግራይ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች እየተካሄደ ያለውን ጦርነት በተመለከተ፣ አቢስ ጦርነቱ የአቅርቦት እጥረትን  ሊያስከትል እንደሚችል ግምታቸውን ተናግረዋል። “በጦርነቱ ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል እንዲሁም የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ወድመዋል፣ ተቃጥለዋል ይህም የብዙዎችን መደበኛ የኑሮ ሁኔታ አመሳቅሏል” ብልዋል።

አክለውም “የምግብ እና ሌሎች አቅርቦቶች ከሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ወደ ጦር ግንባር በመጓጓዛቸው  ለአቅርቦት እጥረቱ እና  ለዋጋ ግሽበቱ አስተዋጽኦ ሳያደርግ አይቀርም” ሲሉ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል። በሰሜን በኩል ያለው ግጭት ካበቃ በኋላ የዋጋ ግሽበቱ እንደሚቀንስ ያላቸውን እምነት ገልጸው፣ በሀገሪቱ ያለውን የዋጋ ግሽበት ለመቆጣጠር መንግስት እና የሚመለከታቸው አካላት ጣልቃ እንዲገቡ ጠይቀዋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.