አዲስ አበባ፤ በሳውዲ አረቢያ የተለያዩ ከተሞች በእስር ላይ የሚገኙትን ኢትዮጵያውያንን ጉዳይ ለመፍታት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተላከው የልዑካን ቡድን ስይሳካለት መመለሱን ተሰማ። በገንዘብ ሚንስትር አህመድ ሺዴ የተመራው የልኡካን ቡድን በሳውዲ አረቢያ ከሚገኙ ባለስልጣናት ጋር ስምምነት ላይ መድረስ አለመቻሉን ጅራ የተባለ መቀመጫውን በአውስትራሊያ ያደረገ እና የእስረኞቹን ጉዳይ ሲከታተል የቆየ የበጎ አድራጎት ድርጅት አስታውቋል። የቀድሞ የሳውዲ አረቢያ ነዋሪ የነበረው ጋዜጠኛ እና የማህበረሰብ ተሟጋች ነብዪ ሲራክ በበኩሉ የልዑካን ቡድኑን ያለ ውጤት መመለስ “አሳፋሪ ነው” ብሏል።
በጥር ወር የውጭ ጉዳይሚኒስቴር የልዑካን ቡድኑ እስር ቤት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አያያዝ እንዲሻሻል፣ የመኖሪያ ፈቃዳቸው የተቃጠለና የተለያዩ ቅጣቶች የሚጠብቋቸው ነገር ግን በራሳቸው ገንዘብ ተሳፍረው አገራቸው መግባት ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ቅጣት ተነስቶላቸውና ምህረት ተደርጎላቸው ወደ ሀገራቸው መመለስ የሚችሉባቸው ሁኔታዎች እንዲመቻቹ ከሳዑዲ አረቢያ ባለስልጣናት ጋር መምከሩን ገልጾ ነበር ። ጉዳዩን ለመፍታት በኢትዮጵያ በኩል ቅድሚያ የሚሰጣቸዉን ተግባራት የመለየት ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸው እና በሳውዲ አረቢያ እና በኢትዮጵያ መካከል የበለጠ መተማመን እና ትብብርን ለማጠናከር የተካሄደው ውይይት ውጤት “ተስፋ ሰጪ ነው” ሲል የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዛኑ ወር በማህበራዊ ትስስር ገጹ ላይ አስፍሯል።
የእስረኞችን ቁጥር ‘በአስር ሺዎች’ እንደሚቆጠሩ የሚናገረው ጅራ የበጎ አድራጎት ድርጅት በሳዑዲ የሚገኙ የማህበረሰብ አስተባባሪዎችን ጠቅሶ እንደገለጸው የሳዑዲ አረቢያ ባለስልጣናት ኢትዮጵያውያን የጉዞ ወጪያቸውን በመሸፈን ወደ አገራቸው ለመመለስ ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጿል። ቢሆንም የኢትዮጵያ ባለስልጣናት፣ ከስደት ተመላሾቹ ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ የሳዑዲ አረቢያ መንግስትየመቋቋሚያ ገንዘብ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል ይላሉ የማህበረሰቡ አስተባባሪዎቹ። የሳውዲ አረቢያ መንግስት በበኩሉ “ጥያቄውን “ጥያቄውን ለአለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች አቅርቡ” በማለት ጥያቄውን ውድቅ አድርጓል። ልኡካን ቡድኑ ከሳውዲ አረቢያ ባለስልጣናት ጋር ስምምነት ላይ መድረስ ያልቻለውም በዚህ ምክንያት ነው ሲሉ የማህበረሰቡ አስተባባሪዎች ይናገራሉ።
በገንዘብ ሚኒስቴሩ መሀመድ ሺዴ የተመራው የሉዑካን ቡድኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ፣ በሳዑዲ አረቢያ የኢትየጵያ አምባሳደር ሌንጮ ባቲ እንዲሁም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር ዶ/ር ተቀዳሚ ሙፍቲህ ሐጂ ዑመር ኢድሪስን ጨምሮ ከኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የተውጣጡ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮችን ያካተተ ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ እስካሁን የሉዑካን ቡድኑ የደረሰበትን ነገር ይፋ ባያደርግም በእስር ቤቶቹ ውስጥ የተቀዱ እጅግ አሰቃቂ የሆኑ ምስሎች እና የድምፅ ቅጂዎች ላለፉት ተከታታይ ሳምንታት ለአዲስ ስታንዳርድ ሲላኩ ቆይተዋል ።
ጅዳ በሚገኝ እስርቤት ታስሮ የሚገኘው አህመድ ለአዲስ እስታንዳርድ በስልክ እንደገለፀው ሰቆቃው ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ ይገኛል። በየመን በኩል ወደ ሳዉዲ አረቢያ የገባው አህመድ ያለፉትን 11 ወራት በቁጥጥር ስር ሲውል ለብሶት በነበረው ልብስ ነው የቆየው። “ልብሳችን እላያችን ላይ በማለቁ አሁን ላይ የምንለብሰው እና እንደ ብርድ ልብስ የምንጠቀመው ፌስታል ነው።”
እንደ ሌሎቹ እስረኞች ሁሉ አህመድም ግፋ ቢል 60 ሰዎች ብቻ በሚችል ክፍል ውስጥ ከ300 በላይ እስረኞች መታጎራቸውን አረጋገግጧል። ” በእስርቤቶች ውስጥ የሚሞቱ እና እየሞቱ ያሉ ጨቅላ ህፃናት እና ልጆች ሁኔታ በጣም ልብ ይሰብራል” ይላል አህመድ። ጨምሮም “በ 70 እና 80 አመታቸው በእስር የሚማቅቁ አዛውንቶች አሉ። ” እንደ አህመድ ገለፃ በእስርቤቶች ውስጥ በሚያጋጥመው የአእምሮ መታወክ ሳቢያ የእስረኞች እራስን ማጥፋት የተለመደ ነው። ” በሁኔታው አስከፊነት የተነሳ አንዳንዴ መፀዳጃ ቤት እንኳን በሁለት እና በሶስት ወር አንዴ ነው ምንጠቀመው።”
“እንደሰማሁት ከሆነ በሴቶች እስርቤት ውስጥ እናቱ መሞቷን ሳያውቅ ጡቷን ሲጠባ የነበረ ጨቅላ ህፃን ፖሊስ አንስቶ ወስዶታል። እኔ ራሴ በህይወት ያለ መስሎት ፖሊሱ የሞተን ሰው ሲደበድብ አይቼአለሁ።” ይላል አህመድ አሁንም ድረስ ጅዳ በሚገኘው እስርቤት የሚያየው ሰቆቃ እያንገፈገፈው።እንደ አህመድ ከሆነ እስረኞቹ ወደ ሳውዲ አረቢያ ከተጓዘው ከፍተኛ የመንግሥት ባልስልጣናት እና የሀይማኖት መሪዎች ልኡክ ዘላቂ የሆነ መፍትሄ ለመስማት በጣም ጓግቶ እየጠበቀ ነው። ” ልኡኩ ከሳውዲ አረቢያ ንጉስ ጋር ያደረጉትን ውይይት ውጤት ለህዝቡ ማሳወቅ አለባቸው ።”
በተመሳሳይ መልኩ፣ ሪያድ ውስጥ ከሚገኝ እስር ቤት ለአዲስ እስታንዳርድ የተላከው የአራስ እናቶች የድምፅ ቅጅ እንዲህ ይላል፣ “ይሄን መልእክት እየሰማችሁ ያላችሁ ሁሉ እባካችሁ የኢትዩጵያ መንግስት እንዲደርስልን ግፊት አርጉልን። በማንኛውም እምነት ውስጥ ያላችሁ ሁሉ ጸልዩልን ከጨቅላ ልጄ ጋር ከታሰርኩኝ ዘጠኝ ወር ሆነኝ። በስልክ ዉስጥ እንደምትሰሙት ቀን እና ሌሊት ያለቅሳል። የምመግበዉ ምንም የለኝም ፣ ታሞ ነው የሚገኘው። ይሞትብኛል ብዬ በጣም እየፈራሁ ነው።”
የልኡካኑ መሪ የሆኑትን አህመድ ሽዴ ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ የሆኑት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንዲሁም በጅዳ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤት፣ በጉዳዩ ዙርያ ለማናገር የተደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም። አስ