ዜና:- ኦፌኮ መንግስት በሳውዲ አረቢያ የታሰሩ ኢትዮጵያዊያንን ስቃይ እና ሞት በአስቸኳይ እንዲያስቆም ጠየቀ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 4/2014 – የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ትላንት አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ በሳውዲ አረቢያ በሚገኙ እስር ቤቶች ኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰው ሰቆቃ በአገራችን የሚነደፉት የዕድገት አቅጣጫዎች (ፖሊሲዎች) አሳታፊና ትክክለኛም ባለመሆናቸው የችግሩ መንስኤ ነው በማለት ተችቷል ። “ማለቂያ የሌለውን የዜጎቻችንን ሰቆቃ መስማት ራሱ ያሰቅቃል” ያለው ፓርቲው “የዕድገት አቅጣጫዎች በተወሰነ ደረጃ ቢተገበሩም እንኳን የተወሰኑ ግለሰቦችና ቡድኖች ፍላጎትን ለማሟላት ማዕከል ስለሚያደርጉ፤ የሕዝቦቻችንን ፍላጎት አያሟሉም” ሲል ወቅሷል። 

በሳዉዲ አረቢያ ከጊዜያት ወዲህ የጨመረው የስየተኞች እስራት ኢትዮጵያውያን ላይ እንደሚበረታ አዲስ ስታንዳርድ ከዚህ ቀደም በእስር ላይ የሚገኙ ዜጐችን በስልክ አነጋግሮ ባወጣቸው ተከታታይ ዘገባዎች አስነብቧል ። 

ጨቅላ ህጻናትን እንዲሁም ያረገዙ እናቶች ሳይቀር በቂ ምግብ፣ መድኃኒት እና መተኛ በሌለበት ታስረው እንደሚገኙ ዘገባዎቹ ያመላክታሉ። እስረኞቹ መንግሥት እንዲደርስላቸው በተደጋጋሚ ያደረጉትን ተማጽኖ በሳውዲ አረቢያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በቸልተኝነት በማለፍ ለዜጐቹ ያለበትን ሀላፊነት አልተወጣም ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል ። 

ኦፌኮ በመግለጫው ከአገር የሚሰደዱ ዜጎች ቁጥር ማሻቀብ ከሀገሪቱ የፖለቲካ አመራር  መዛባት ጋር የተገኘ ነው ያለ ሲሆን ተመዝግቧል የሚባለው የምጣኔ ልማት የጥቂቶችን ሀብት እድገት ከማሳየት በስተቀር  በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች የሚደረግላቸው ትኩረት አነስተኛ እንደሆነ አትቷል። “ሰፊ መሬትና ብዙ የተፈጥሮ ሀብት እያለን ባለመልማቱ ዜጎች ለራሳቸውም ሆነ ለቤተዘመዶቻቸው የተሻለ የኑሮ ሁኔታ ለመፍጠር ሲሉ ስጋት በተሞላበት ሁኔታ ወደ ስደት ያመራሉ፡፡” በማለት ባለፉት ሰላሳ ዓመታት የዜጎች ወደ ውጪ አገራት በተለይም ወደ ዓረብ አገራት መሰደድ “የፖለቲካም ሆነ የኤኮኖሚ ፍላጎታቸው ባለመሟላቱ ነዉ” ሲልም ሞግቷል።   

በሊቢያ የባህር ዳርቻ ‘የታረዱትን’ ኢትዮጵውያን ወጣቶች ያወሳው ፓርቲው “በሳውዲ አረቢያ ግለሰቦች ቤትና ሰሞኑን ደግሞ በጅምላ እስር ቤት ታጉረው ያሉበት ሰቆቃ እጅግ ያሰቅቃል ብዙ ነገሮች ለተወሰኑ ጊዜያት ቀርተውብን መንግስት የእነዚህን ወገኖቻችንን ሕይወት ቢታደግ የተሻለ ነው የሚሉ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ  ወገኖችን ሐሳብ  ኦፌኮም እንደሚደግፍ አስታውቋል፡፡

“እስካሁን ብዙዎችን በሞት የተነጠቅን ቢሆንም መንግስት የቀሪ ወገኖቻችንን ሕይወት ለማትረፍ አስቸኳይ ዕርምጃ እንድወስድ እንማፀናለን ” በማለት  ኦፌኮ መግለጫውን አጠቃሏል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.