ዜና:- አምነስቲ የትግራይ ኃይሎች ቆቦ እና ጭናን ተቆጣጥረው በቆዩባቸው ጊዜያት ሰላማዊ ዜጎች ላይ ግድያ እና የአስገድዶ መድፈር ጥቃቶችን አድርሰዋል አለ

አዲስ አበባ፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በትላንትናው እለት ባወጣው  ዘገባ በአማራ ክልል ጭና እና ቆቦ ከተሞች ከህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጋር ግንኙነት ያላቸው ተዋጊዎች በርካታ ሰዎችን ገድለዋል፣  ሴቶችን እና ህጻናትን በቡድን ደፍረዋል ያለ ሲሆን የግል እና የህዝብ ንብረት ዘረፋ መፈጸሙን አረጋግጫለሁ ብሏል። 

አለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች እንደገለጸው ፣  ግድያዎቹ የተፈፀሙት በነሀሴ ወር መጨረሻ እና መስከረም 2013 ዓመተ ምህረት ሲሆን ይህም የትግራይ ሀይሎች በሀምሌ ወር አካባቢውን ከተቆጣጠሩ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ነው።  አምነስቲ የዓይን እማኞችን ወቢ አድርጎ የጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ጋር በሁለቱ ከተሞች ስለመፈጸማቸው የሚያመለክቱ ማስረጃዎች መኖራቸውን አመልክቷል።  ከጥቃቶቹ በተጨማሪ የግድያ ዛቻዎች እና ብሔር ተኮር ስድቦች በነዋሪዎች ላይ እንደደረሱ ተጠቁሟል። 

አምነስቲ ኢንተርናሺናል በቆቦ ከተማ ሬሳዎችን ለመሰብሰብ እና ለመቅበር የረዱትን ጨምሮ 27 ምስክሮች እና በህይወት የተረፉ ሰዎችን ቃለ መጠይቅ በማድረግ እንደዘገበው የትግራይ ሀይሎች ሆን ብለው ያልታጠቁ ሰላማዊ ዜጎችን የገደሉ ሲሆን ይህም በአማራ ታጣቂዎች እና ሚሊሻዎች የደረሰባቸውን ጉዳት ለመበቀል የተደረገ ነው ይላል ዘገባው ። 

“መጀመሪያ ወንድሜ ታደሰን በጥይት መቱት…በቅጽበት ህይወቱ አለፈ። ሌላኛው ወንድሜ እና የባለቤቴ ወንድም ለማምለጥ ሞክረው ሁለቱም ከኋላ በጥይት ተመትተው ተገደሉ… እኔን በግራ ትከሻዬ ተኩሰው መቱኝ…  የሞትኩ መስዬ በወደኩበት ተኝቼ ቀረሁ” ሲል ከግድያዎቹ የተረፈ የቆቦ ከተማ ነዋሪ ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል ተናግሯል።

ከባህር ዳር አቅራቢያ በምትገኘው ጭና እድሜያቸው ከአስራ አራት የማይበልጡ ህጻናትን ጨምሮ በርካታ ሴቶች በቡድን መድፈራቸውን የኘለከተው ዘገባ ጾታዊ ጥቃቱ ድብደባ፣ የግድያ ዛቻ እና ብሔር ተኮር ስድብን ጨምሮ በሌሎች የጭካኔ ድርጊቶች የታጅበ ነበር ብሏል። 

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ካነጋገራቸው ጾታዊ ጥቃት ከደረሰባቸው 30 ሴቶች መካከል 14ቱ በበርካታ የትግራይ ተዋጊዎች በቡድን እንደተደፈሩና የተወሰኑት ደግሞ በልጆቻቸው ፊት ነበር የተደፈሩት። የጾታዊ ጥቃቱ ሰለባ ከሆኑታ መካከል ሰባቱ ከ18 ዓመት በታች መሆናቸው ታውቋል።

እንደ ዘገባው ከሆነ በቆቦም ሆነ በጭና የህክምና ተቋማትን እና ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ የግል እና የህዝብ ንብረቶች ላይ ዝርፊያ ተፈጽሟል።  በህክምና ተቋማት ላይ የደረሰው ዘረፋ እና ውድመት ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው እና ሌሎች የህክምና እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ነዋሪዎች በአካባቢያቸው ህክምና ማግኘት ባለመቻላቸው ለመታከም ሳምንታት ጠብቀው በደባርቅ፣ ጎንደር እና ባህርዳር የሚገኙ ሆስፒታሎች ድረስ ለመሄድ ተገደዋል ። 

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ አፍሪካ፣ የአፍሪካ ቀንድ እና ታላላቅ ሐይቆች አካባቢ የቀጠና ምክትል  ዳይሬክተር ሳራህ ጃክሰን እንደገለጹት፣ ሕወሃት በጦርነት ውስጥ ያሉ ሁሉም ኃይሎች ሊያከብሩት የሚገባ  መሰረታዊ ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕጎችን አላከበረም፤ እንዲሁም ቡድኑ በአማራ ክልል የጦር ወንጀልና በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸም ወንጀል መፈጸሙን የሚያሳዩ ማስረጃዎች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡

“የትግራይ ተዋጊ ሀይሎች ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ሊከተሏቸው የሚገቡትን መሰረታዊ የአለም አቀፍ የሰብአዊ ህግ ደንቦችን አላከበሩም፤ ይህም ግድያ እና የአስገድዶ መድፈር ጥቃቶችን እንዲሁም ከሆስፒታሎች ጭምር  የተደረገውን ዘረፋን ይጨምራል” ብለዋል ምክትል ዳይሬክተሯ። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.