ዜና፡ በህገ-ወጥ የሐዋላ ሥራ ላይ የተሰማሩ 391 የሚደርሱ ተጠርጣሪዎች የባንክ ሒሳባቸው መዘጋቱን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ፡፡ ፎቶ፡- የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

በአዲስ ስታንዳርድ ሪፖርተሮች

አዲስአበባ፣መስከረም27/ 2015 .ም፡ የውጭ አገራት ገንዘቦችን በህገ-ወጥ የሃዋላ አገልግሎት ሲመነዝሩ የነበሩ 391 ተጠርጣሪዎች የባንክ ሂሳባቸው እንዲዘጋ መደረጉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ በህገ-ወጥ መልኩ የሚከናወን የውጭ አገራት ገንዘብ ምንዛሬ ለዋጋ ግሽበትና ለንግድ ስርዓቱ የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ገልፀው በጥቁር ገበያ የምንዛሬ ስራ ሲሰሩ የተደረሰባቸው 391 ተጠርጣሪ ሰዎች የባንክ ሂሳባቸው እንዲዘጋ መደረጉን ተናግረዋል።

በወንጀሉ ላይ ተሳታፊ የነበሩ የግለሰቦችን ስም ዝርዝርም ለፍትህ ሚኒስቴር በመላክም የምርመራ ስራው እንዲቀጥል መደረጉን የጠቀሱት ዶክተር ይናገር እንዲህ አይነት ወንጀሎችን ለመከላከልና አጥፊዎችን ተጠያቂ ለማድረግ የተጠናከረ የቁጥጥር ስራ ይደረጋል ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያንም በግለሰብ ደረጃ ከ100 ሺህ ብር በላይ ለድርጅቶች ደግሞ ከ200 ሺህ ብር በላይ በቤት ውስጥ ማስቀመጥ የተከለከለ መሆኑን መገንዘብ እንደሚኖርባቸውም አሳስበዋል። በመሆኑም በውጭ አገራት ገንዘብ ግብይት መፈጸምም ሆነ በህገ-ወጥ መንገድ ይዞ መገኘት እንደማይቻል እና በህገ-ወጥ መልኩ ወርቅ ቤት ውስጥ ማከማቸት የማይቻል መሆኑን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ይህን ሕገወጥ ድርጊት ለሚጠቁሙ ዜጎች የወሮታ አከፋፈል ሥርዓት የተዘጋጀ መሆኑን የገለፁት ዶክተር ይናገር በተለይም ከተፈቀደው በላይ በቤት ውስጥ የብር ክምችት የሚያደርጉ፣ የሐሰተኛ የገንብ ኖቶችን የሚሠሩና የሚያሠራጩ አካላት እንዲሁም በሕገወጥ መልኩ የሐዋላ አገልግሎት የሚሠጡ ወይም በጥቁር ገበያ ላይ የተሰማሩ አካላትን ለሚጠቁሙ ዜጎች ደኅንነታቸውና ሚስጥራዊነታቸውን በጠበቀ መልኩ የሚሸልምና ወረታውን የሚከፍል መሆኑን አስታውቀዋል።

መንግሥት የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠር የፈቀደውን የፍራንኮ ቫሉታ ፍቃድ እንደ እድል በመውሰድ በሕገወጥ መንገድ ዶላር በመጠቀም ሸቀጦችን የማስገባት ተግባር የተስተዋለ በመሆኑ በዚህ ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች የባንክ ማስረጃ ለብሔራዊ ባንክ እንዲያቀርቡ የሚደረግ መሆኑም እንደተገለጸ ኢፕድ ዘግቧል።

መስከረም 16 ቀን 2015 ዓ.ም. የፌዴራል የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት፤ በህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ተግባር  ላይ የተሰማሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማስጠንቀቁ ይታወሳል፡፡

የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት አንዳንድ አካላት በህጋዊ የገንዘብ ማስተላለፍ (ህጋዊ ሐዋላ) ሽፋን ገንዘብ የማስተላለፍ ድርጊት እየፈጸሙ እንደሚገኙ ጠቅሶ ተቀማጭነታቸውን ከኢትዮጵያ ውጭ በማድረግ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሆኑ ግብረአበሮቻቸው ጋር በመመሳጠር በህጋዊ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ መግባት የሚገባውን የውጭ ምንዛሪ በውጭ ሀገራት በማስቀረት ክፍያውን በኢትዮጵያ ብር የሚፈፅሙ መሆናቸውም ተመላክቷል።

በተለይም ‘አዶሊስ’ ፣ ‘ሸጌ’፣ ሠላም ፣ ሬድ ሲ የተባሉና በውጭ ሀገር በገንዘብ ማስተላለፍ ተግባር ላይ የተማሩት አካላት በህጋዊ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ መግባት የነበረበትን የውጭ ምንዛሪ ለኢትዮጵያ ባንኮች የላኩ በማስመሰል ሀሰተኛ ደረሰኝ ጭምር በማዘጋጀትና በመጠቀም የውጭ ምንዛሪውን በውጭ ሀገራት በማስቀረት በኢትዮጵያ ውስጥ የውጭ ሀገራት ገንዘብ ምንዛሪና የኑሮ ውድነት እንዲባበስ በማድረግ ላይ ናቸው ማለቱ ይታወሳል።

እነዚህ የገንዘብ አስተላላፊዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ግብረ አበሮቻቸው ከሆኑ ከ600 በላይ የሂሳብ ምንጮች በብር ክፍያ ሲፈፅሙ እንደነበርም ከአገልግሎቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢፌዲሪ ፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት  ህገወጥ የገንዘብ ማስተላለፍ ተግባርን ጨምሮ መሰል የፋይናንስ ወንጀሎች የሚፈፅሙ አካላትንና በድርጊቱ የተሳተፉ ግብረ አበሮቻቸውን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ከሀገር ውስጥ ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ከውጭ ሀገራት አጋር ተቋማት ጋር በማካሄድ ላይ ያለውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አሳስቦ ነበር፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.