ዜና፡ ዩክሬን ለኢትጵያ እና ሶማሊያ በእርዳታ መልክ ያበረከተችውን 50,000 ሺህ ቶን ስንዴን ጀርመንና ፈረንሳይ ለማጓጓዝና ለማከፋፈል ድጋፍ አደረጉ

የዩክሬንን ስንዴ የጫነ መርከብ ከኦዴሳ ወደብ ሲወጣ የሚያሳይ ፎቶ:: ፎቶ: ©አሊያንስ/የጀርመን የውጭ ጉዳይ ቢሮ

በአዲስ ስታንዳርድ ሪፖርተሮች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27/2015 ዓ.ም በአፍሪካ ቀንድ በድርቅ ክፉኛ ለተጎዱት እንዲውል ዩክሬን ለኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ያበረከተችውን 50,000 ሺህ ቶን ስንዴን ጀርመንና ፈረንሳይ ለማጓጓዝና ለማከፋፈል ድጋፋቸውን ገልፀዋል፡፡

ለአዲስ ስታንዳርድ በተላከው መግለጫ ሁለቱ ሃገራት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአለም የምግብ ፕሮግራም በኩል እያንዳንዳቸው 14 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ ማድረጋቸውን አሳውቀዋል፡፡ በመግለጫው “ጀርመን ወደ ኢትዮጵያ ለማድረስ የሚያስፈልገውን ወጭ የምትሸፍን ሲሆን፣ ፈረንሳይ ደግሞ ወደ ሶማሊያ ለማድረስ የሚያስፈልገውን ወጭ እንደምትሸፍንም” ተገልጿል፡፡

የዩክሬን ካቢኔ ሚኒስቴር በመስከረም ወር ዩክሬን ለኢትዮጵያ እና ሶማሊያ 14 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጭ የሚጠይቅ ስንዴ እንደምትልክ ማሳወቁ ይታወሳል፡፡ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ በ77ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ባደረጉት ንግግር በጦርነቱ ምክኒያት ችግሮች ቢያጋጥሙንም ዩክሬን ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ እርዳታ ለመስጠት እና ተጨማሪ ስንዴ ለኢትዮጵያ ህዝብ ለመላክ መወሰኗን ገልፀው ነበር፡፡

“ምንም አንኳ ዩክሬን የጦርነት ጥቃት እየደረሰባት ቢሆንም ልገሳው ታላቅ የአብሮነት ምልክት ነው፡፡ ለራሷ እርዳታ የሚያስፈልጋት ሀገር፣ በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ሰዎችን ከርሃብ ለማዳን ትለግሳለች፡፡ ከዩክሬን የሚገኘው እህል በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ በምግብ እጥረት የተቸገሩ ዜጎች ለአንድ ወር ያህል የሚሆን ስንዴ እንዲያገኙ ያሰችላል” ሲል ትናንት የወጣው መግለጫ ገልጧል፡፡ አክሎም “የምግብ እርዳታው የቤተሰብን መሰረታዊ ፍላጎቶች ለማሟላት ሚረዳ ሲሆን፣ ያላቸውን ትንሽ ገንዘብ እንደ አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ አሳ ወይም ስጋ ባሉ የሀገር ውስጥ ምግቦች ላይ የበለጠ ሊያውሉት ይችላሉ” ብሏል ፡፡

በሶማሊያ ግማሽ የሚሆነው ህዝብ በሰብዓዊ እርዳታ ላይ የተመሮከሰ ሲሆን፣ 121,000 ሺህ ሰዎች በርሃብ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ይህም ቁጥር በታህሳስ ወር 300,560 ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 24.1 ሚሊዮን ሰዎች በድርቅ የተጎዱ ሲሆን ከ20 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት በሀገር አቀፍ ደረጃ የምግብ ዋስትና እጦት ተደቅኖባቸዋል፡፡ በድርቅ በተጎዱ ሀገሮች በኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ኬንያ በድምሩ ከ20.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡

በ2014 የጀርመን መንግሰት ለኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ኬንያ 126 ሚሊዮን ዩሮ ለሰብዓዊ እርዳታ መድቧል፡፡ በባለፈው ዓመት ለአለም የምግብ ፕሮግራም ከ700 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ድጋፍ በማድረግ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች የምግብ እርዳታ አቅርቧል፡፡ በተጨማሪም ለጤና፣ ለውሃ አቅርቦት እና ለአደጋ መከላከል ተጨማሪ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡

በተመሳሳይ ፈረንሳይ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ለሚገኙ ተጋላጭ ህዝቦች የምግብ ዋስትናን እና የኑሮ ሁኔታን ለማሻሻል ለአለም የምግብ ፕሮግራም፣ የተባበሩት መንግስታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (FAO)፣ እንዲሁም እንደ ACTED ወይም Action Against Hunger ያሉ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን እየደገፈች ነው፡፡ በ2022 መጨረሻ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በፈረንሳይ የምግብ እርዳታ ተጠቃሚ ከሚሆኑ ሀገራት መካከል ናቸው፡፡ አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.