ትኩስ ዜና፡ ጋዜጠኛ አበበ ባዩ አዋሽ አርባ ታስሮ እንደሚገኝ ቤተሰቦቹ ተናገሩ፣ ጋዜጠኛ ያየሰው እስካሁን የት እንዳለ አልተታወቀም

ያየሰው ሽመልስ እና አበበ ባዩ

በማህሌት ፋሲል

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 27 ቀን፣ 2014 ዓ.ም – “ኢትዮ ፎረም” የተሰኘ የዩቱብ ሚዲያ ጋዜጠኛ የሆነው አበበ ባዩ አዋሽ አርባ ታስሮ እንደሚገኝ ቤተሰቦቹ ተናገሩ ።

የአበበ ቤተሰቦች ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት አርብ ሰኔ15 ቀን 2014 ዓም ከምሽቱ 4 ሰአት ላይ ሲቪል በለበሱ የፀጥታ ሀይሎች ከመኖሪያ ቤቱ እንደተወሰደና የታሰረበትን ቦታ ለማወቅ ተቸግረው እንደነበር የጠቀሱ ሲሆን ትላንት ከአፋር አዋሽ አርባ የተፈቱ እስረኞች አበበ ባዩ አዋሽ አርባ እንደሚገኝ በስልክ እንደነገሯቸው ተናግረዋል።

አበበ ከዚህ ቀደምም በፖሊስ ተይዞ ክስ ሳይመሰረትበት ከወራት በኋላ መፈታቱ ይታወሳል

በተያያዘ ዜና ሰኔ 14 ቀን ጠዋት በፀጥታ ሀይሎች የተወሰደው የቀድሞ የ “ኢትዮ ፎረም” ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ አሁንም የት እንደታሰረ እንደማይታወቅ ቤተሰቦቹ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል። ሲቪል በለበሱ የፀጥታ ሀይሎች ከመኖሪያ ቤቱ የተወሰደው የቀድሞው የኢትዩ ፎረም አዘጋጅ ጋዜጠኛ ያየስውን ለማግኘት ፌደራል ፖሊስም ሆነ አዲስ አበባ ፖሊስ ብንጥይቅ እኛ ጋር የለም ተብለናል ሲሉ የጋዜጠኛው ቤተስቦች ለአዲስ ስታንዳርድ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

ሰኔ 21 ቀን እንደገና ከመታሰሩ በፊት ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ ሰሞኑን ከተጠረጠረበት “ሁከትና ብጥብጥ ማስነሳት” ወንጀል ሰኔ 13 ቀን 2014 ዓም በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት በሰጠው የ10,000 ብር የዋስትና መብት ከእስር መፈታቱ ይታወሳል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.