አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2/ 2015 ዓ.ም፡- ባደጉት ሀገራት በመንገድ ዳር የሚሸጡ ምግቦችን ማየት የተለመ ነው፡፡ በተለይ ቱርክ፣ ቻይና፣ ህንድ፣ ታይላንድ፣ ሜክሲኮ፣ ሲንጋፖር፣ ደቡብ አፍሪካ… የመንገድ ዳር ምግብ ንግድ በስፋት የሚከናወንባቸው ሀገራት መካከል ዋንኞቹ ናቸው፡፡
በመዲናችንም ይህ ንግድ እየተለመደና እያደገ መጥቷል፡፡ በተለይ አመሻሽ ላይ በተለያዩ የመዲናዋ ጎዳናዎች አጠገብ በተንቀሳቃሽ ጋሪ ምግብ እያበሰሉ ለአላፊ አግዳሚ የሚሸጡ ወጣቶች እየተስተዋሉ ይገኛሉ፡፡ ምግቦቹ ቀለል ያሉ በአጭር ግዜ ውስጥ የሚደርሱ ከመሆናቸውም በላይ በዋጋ ቀነስ የሚሉ በመሆኑ በብዙዎች ተመራጭ ያደርጋቸዋል፡፡
መንገድ ዳር ምግብ በመስራት (በፋስት ፉድ ስራ) የሚተዳደርው ታደለ ገ/ዮሃንስ (ታደለ ፋስት ፉድ) በአዲስ አበባ ከተማ ይህንን ስራ በማስጀመር ቀዳሚ መሆኑን ይናገራል፡፡ በስደት ለረጅም አመታት የቆየው ታደለ ወደ አገሩ ተመልሶ የፋስት ፉድ ስራን በመስራት ስኬታማ መሆን መቻሉን ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ባደረገው ቆይታ ገልጿል፡፡ ታደለ ተወልዶ ያደገው አዲግራት ከተማ ሲሆን ከዛም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በስራ በማጣቱ ወደ ሱዳን መሰደዱን ይገልፃል፡፡
ሱዳን ከገባ በኋላም ለሰባት አመት የወርቅ ቁፋሮ ስራ ላይ ተሰማርቶ ሲሰራ ነበር፡፡ ከወርቅ ስራ በተጨማሪም በካርቱምም ጥሩ የማይባል ስራ ውስጥ ተሰማርቶ እንደነበር እነዲሁም በሱስ ተዘፍቆ መቆጣቱን ይናገራል፡፡ ከዛ በመቀጠለም ወደ አውሩፓ ለመግባት ወደ ሊቢያ ባመራበት ወቅት ነበር መንገድ ዳር ምግብ እየሰሩ የሚሸጡ ሰዎችን የተመለከተው፡፡ ከዛም ወደ አውሮፓ የመግባት ሃሳቡን በመቀየር ወደ አዲስ አበባ በመመለስ የፋስት ፉድን ስራ ለመስራት መወሰኑን ይገልፃል፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ በ2011 አነስተኛ ተንቀሳቃሽ ጋሪ በመስራት ስቴድየም አካባቢ ፋስት ፉድ መስራት በመጀመር ለስኬት በቅቻለው ይላል፡፡ ታደለ በዚህ ስራ ጥሩ ውጤት ማየት ሲጀምር የጋሪውን መጠን በማሳደግ በአምስት ካሬ ቦታ ላይ (1.8 በ 3ሜትር) ባለ አንድ ፎቅ ሱቅ ተንቀሳቃሽ ጋሪ በማሰራት የሰዎችን ቀልብ በሚስብ ገፅታ በማሳመር ተጠቃሚዎች ፊት ቶሎ የሚደርሱ ምግቦችን ተጠቃሚው በሚፈልገው ልክ መስራት መቀጠሉን ገልጿል፡፡ በሂደትም አሁን ላይ በዚች አነስተኛ ቦታ ላይ ለሰባት ሰው የስራ እድል መፍጠር ችሏል፡፡
የፋስት ፉድ ሱቆች ለየት የሚያደርጋቸው ዋጋቸው ተመጣጣኝ መሆኑ ዋነኛው ሲሆን ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች በስፋት ይጠቀሙታል፡፡ ታደለ ፋስት ፉድ በቀን ከሶስት መቶ በላይ ተጠቃሚዎችን እንደሚያስተናግድ የሚገልፀው ባለቤቱ እንደዚህ አይነት ስራዎችን መንግስት ቢያበረታታ የኑሮ ውድነቱን ማስታገስ ይቻላል ሲል ገልጧል፡፡ በምሳሌ ሲያስረዳም ሌሎች ምግብ ቤቶች ከሚሸጡበት ወጋ ቀንሰን ነው የምንሸጠው የዚህ ምክኒያቱ ደግሞ እኛ የቦታ ክፍያ ስለሌለብን ነው ይህ ተግባር ቢስፋፋ የኑሮ ውድነቱን መቀነስ ይቻላል ብየ አምናለው ብሏል፡፡
በስደት ቆይታው በሱስ መጠመዱን የገለፀው ታደል ወደ ሀገሩ በመመለስ የራሱን ስራ በመጀመር ከሱስ ተላቆ በስራው ውጤታማ መሆን መቻሉን ተናግሯል፡፡ አክሎም ጠንክሬ በመስራቴ በስራው ስኬትማ በመሆን “ችግርን አሸንፌበታለው” ሲል ገልፆ ወጣቶች ለስራ ተነሳሽነት እንዲኖራቸው ከሱስ ርቀው ስራ ሰይንቁ ዝቅ ብሎ መስራትን መልመድ መሞከር አላቸው ሲል ይመክራል፡፡
“ይህ ስራ ጥሩ ገቢ ያስገኛል፣ ለምሳሌ እኔን ብትወስድ በዚህ ስራ ቤተሰቦቼን አስተዳድርበታለሁ፣የሚስፈልጋቸውንም ነገሮች ማሟላት ችያለሁ፣ በስሬ የሚሰሩትም ቤተሰቦቻቸውን እያስተዳደሩበት ነው፣ ከእኔና ከቤተሰቦቼ አልፎ 17 የጎዳና ተዳደሪዎችን ለመርዳት አቅሙን አግኝቻለሁ፤ ሰዎች ይህ ትንሽ ስራ ነው እያሉ በሚንቁት ስራ ለሌሎች መትረፍ እንደሚቻል ይህ ማሳያ ሊሆን ይችላል” ብሏል፡፡
ስራውን መጀመሪያ ስጀምር ሰዎች ምን ይሉኛል የሚል ስጋት ነበረብኝ የሚለው ታደለ አሁን ግን ቀና ብየ እንድሄድ አስችሎኛል ይላል፡፡ የሽምብራ፣ የአትክልትና የእንቁላል ግብዓትን በመጠቀም የአረቦች መግብን በመስራት እንታወቃለን ያለው ታደለ፤ ፋላፍል ሳንዱች፣ እንቁላል ሳንዱችና እርጥብ ብዙ ተመጋቢዎች በብዛት እንደሚጠቀሙት ይናገራል፡፡
ከታዋቂ፣ ባለሃብት ጀምሮ እስከ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች መጥተው ይጠቀማሉ የሚለው ስራ ፈጣሪው በተለይ ስቴድየም አከባቢ የሚሰሩ የምንግስትና የግል ተቀጣሪዎች በዚች አነስተኛ ቦታ ላይ በቋሚነት እንደሚመገቡ ገልጧል፡፡
ለስራው ፈጣኝ ከሆነብን ነገሮች አንዱ የቴካወይ ማሸግያዎች በበቂ አለመመረትና ውድ መሆን ነው የሚለው ስራ ፈጣሪው መንግስት ለዚህ ማነቆ ትኩረት ሰጥቶ ቢሰራ የዴሊቨሪ ክንውንን ያሳልጣል ሲል ሃሳቡን አካፍሏል፡፡
ፋስት ፉድን በመዲናዋ በማስተዋወቅ ቀዳሚ የሆነው ታደለ የስራው የተሰማሩ ወጣቶችን ልምድ እንዲከፋፈሉ እና የስራውን ባህል ለማስፋት በቅርቡ የፋስት ፉድ ባዛር (አውደ-ርዕይ) በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ለማከናወን እንቅስቃሴ መጀመሩን ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግሯል፡፡
ይህ አውደ-ርዕይ ስራ አጥ ወጣቶችን ወደ ቢዝነሱ እንዲገቡና ልክ እንደኔ ውጤታማ እንዲሆኑ መንገድ ይከፍትላቸዋል የሚለው ታደለ በተለይ የክልል ከተሞች ላይ ይህ ስራ ባለመለመዱ ወጣቶች በስፋት ይህንን ስራ ቢሰሩ ጥሩ ገቢ እንደሚያገኙ ምንም ጥርጥር የለኝም በማለት ገልጿል፡፡
አሁን ላይ የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት ተዕኖን በመቋቋም ለ 7 ወር የዋጋ ጫማሪ ባለማድረግ ቆይተናል፤ ይህም ለተጠቃሚው ፋይዳ ስለሚኖረው ደስተኛ ያደረገኛል ሲል ይናገራል፡፡ ስደት ላይ በነበርኩበት ወቅት ያየሁትን ይህን ስራ ወደ አገራችን በማምጣት በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች ማታ ማታ በተንቀሳቃሽ ጋሪ ፋስት ፉድ ለሚሰሩ ወጣቶች በማስተዋወቅ ደፍረው እንዲሰሩና ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጊለሁ ሲል የሚያስረዳው ታደለ ወጣቶች ሳይታክቱ ቢሰሩ ያሰቡትን ለማሳካት የማይችሉበት ምንም ምክንያት የለም ሲል ይመክራል፡፡
እንደዚህ አይነት ስራዎችን መንግስት ቢደግፍ የግብር ከፋዮች ቁጥር እንዲጨምርና ሰፊ የስራ እድል መፍጠር እንዲቻል መንገድ ይከፍተል በማለት የሚናገረው ታደለ እራሱን እንደ ምሳሌም ያነሳል፡፡ ታደለ በሱስ ውስጥ በቆየባቸው ወቅት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መቆየቱን ገልፆ ወጣቶች ከሱስ እና ከስራ አጥነት በመላቀቅ በገቢ እራስን መቻል እንደሚቻል ከእኔ ልምድ መውሰድ ይችላሉ ሲል ገልጧል፡፡አስ