ዜና፡ የእስራኤል ባለስልጣናት በጎንደር የታገተው ቤተ እስራኤላዊ የውሸት ነው የሚል እምነት ስላደረባቸው ለማስለቀቅ የሚደረገው እንቅስቃሴ እንዲቋረጥ ማድረጋቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10/2015 ዓ.ም፡- ከቀናት በፊት በጎንደር አቅራቢያ ታግቶ የነበረው እስራኤላዊ በሀሰት ታግቻለሁ በማለት ገንዘብ ከቤተሰቦቹ ለመውሰድ በማለም ያደረገው ተግባር ነው መባሉን የእስራኤል የዜና አገልግሎት በዘገባው አስታውቋል። በዚህም ሳቢያ ታጋቹን እስራኤላዊ ለማስለቀቅ የሚደረገው ጥረት በእስራኤል ባለስልጣናት እንዲቋረጥ መደረጉን ዘገባ አመላክቷል።

የ79 አመቱ እስራኤላዊ ፍራንሲስ አደባባይ እገታ እንደተፈጸመበት በማስመሰል ከቤተሰቦቹ የሚገኝን ገንዘብ ለመውሰድ በማለም የፈጸመው የማጭበርበር ተግባር ነው ብሎ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ማመኑን ዘገባው አመላክቷል።

አጋቾቹ ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊየን ብር ለማስለቀቂያ መጠየቃቸውን ዘገባው አስታውቋል።

ታጋቹ ቤተእስራኤላዊ ፍራንሲስ አደባባይ ከእስራኤል ሀገር ለሚደወልለትን ስልክ ምላሽ በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ያረጋገጡት የእስራኤል ባለስልጣናት ለማስለቀቅ የሚደረገው እንቅስቃሴ እንዲቋረጥ ማድረጋቸው ዘገባው አስታውቋል።

ቤተሰቦቹ በበኩላቸው በባለስልጣኑ ግኝት ላይ አለመስማማታቸውን እና ፍራንሲስ አደባባይ አሁንም በእገታ ላይ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው ዘገባው ጠቁሟል።

በዜግነት እስራኤላዊ የሆነው አደባባይ በሰሜን ኢትዮጵያ በአማራ ክልል በጎንደር ታግቶብኛል ሲል የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል። እስራኤላዊው የታገተው ማስለቀቂያ ገንዘብ በፈለጉ ሀይሎች መሆኑም በዘገባው ተጠቁሟል። የእስራኤል የጸጥታ ሀይሎች ታጋቹን ለማስለቀቅ ከኢንተርፖል እና ከአከባቢው የጸጥታ ሀይሎች ጋር ሲሰሩ እንደነበር ዘገባው አስታውሷል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.