እለታዊ ዜና፡ የአክሱም ሐውልት ከዛሬ ጀምሮ ዳግም ለጎብኚዎች ክፍት ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6/2015 ዓ.ም፡- በትግራይ ክልል በተቀሰቀሰው ጦርነት ሳቢያ ከሁለት አመታት በላይ ተዘግቶ ጠቆየው አክሱም ሐውልት ከዛሬ ሰኔ 6 2015 ጀምሮ ዳግም ለጎብኚዎች ክፍት መደረጉን የአክሱም ከተማ ባህል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የአክሱም ከተማ ባህል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረመድኅን ፍፁም ብርሀን ለኢዜአ እንዳስታወቁት በአክሱም ከተማ እና አካባቢው የሚገኙ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ጥንታዊ ቅርሶች ለቱሪስቶች ክፍት ተደርገዋል።

የቱሪዝሙን ዘርፍ ወደነበረበት ለመመለስ እና ኅብረተሰቡ ለቱሪስቶች የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሳደግ ለፎቶ አንሺዎች፣ አስተርጓሚዎች፣ ለባህላዊ ጌጣጌጦች እና ቅርፃቅርፅ ባለሙያዎች እንዲሁም ለባለ ሆቴሎች ሥልጠና መሰጠቱን አሰረድተዋል።

በአክሱም እና አካባቢው የሚገኙ ቅርሶች እና ሙዚየም ለቱሪስቶች ተደራሽ ለማድረግ ክፍት መደረጋቸውን ገልፀዋል፡፡ ኃላፊው አቶ ገብረመድኅን ቅርሶቹ ዳግም ለጎብኚዎች ክፍት እንዲሆኑ ኅብረተሰቡ በጉልበቱ፣ በገንዘቡ እና በሙያው ያደረገው ተሳትፎ የላቀ እንደነበረም ተናግረዋል።

በአክሱም እና አካባቢው የሚገኙ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ጥንታዊ ቅርሶች ለመጎብኘት እና ለማየት በየዓመቱ ከ30 ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ይጎበኙት እንደነበር አስታውሰዋል። ጎብኝዎቹ በአክሱም እና አካባቢ በሚኖራቸው ከ2 እስከ 3 ቀናት ቆይታ ከሚያገኙት አገልግሎት የቱሪዝም ፅህፈት ቤት እና ነዋሪው በዓመት ከ180 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ያገኝ እንደነበረም መጥቀሳቸው በዘገባው ተካቷል።

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.