አስተያየት: በኢትዮጵያ የሚከሰተው ሕገ መንግስታዊ ቀውስና የፖለቲካዊ መፍትሄ አስፈላጊነት

ጀዋር መሃመድ @Jawar_Mohammed

አዲስ አበባ, ሚያዚያ 25, 2012 – የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ መጋቢት 21, 2012 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በዚህ ዓመት በፌደራልና በክልል ደረጃ ነሐሴ 14 ይካሄዳል ተብሎ የነበረውን ምርጫ በኮቪድ-19 ምክንያት ማስፈፀም እንደማይችል አሳውቋል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ ቦርዱን ውሳኔ ሚያዝያ 22, 2012 ዓ.ም ካፀደቀ በኋላ ጉዳዩ የበለጠ ውይይት እንዲደረግበት ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የፌደራልና የክልል ሕግ አውጪ አካላት እንዲሁም የአስተዳደሮች የሥራ ዘመን መስከረም 30 ላይ ያበቃል፡፡ በመሆኑም ገዢው የብልጽግና ፓርቲ ከመስከረም በኋላ ሕገ መንግስታዊ የሆን የማስተዳደር ሥልጣን አይኖረውም ማለት ነው፡፡
ይህ ልዩ ተግዳሮትን ያመጣል፡፡ ከመስከረም 30 በኋላ ኢትዮጵያውያን የሚያስተዳደራቸውን መንግስት መምረጥ እስከሚችሉበት ጊዜ ድረስ የማስተዳደር ሥልጣን የሚኖረው ማነው?
መንግስት ከዚህ ሕገ መንግስታዊ ቀውስ መውጫ የሚሆን መፍትሄ ይሰጣሉ ያላቸውን አራት አማራጮች አቅርቧል፡- ፓርላማውን መበተን፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ፤ ሕገ መንግስቱን ማሻሻል፤ እና የሕገ መንግስት ትርጉም ማፈላለግ ናቸው፡፡አራቱም አማራጮች ያሉባቸውን ጉድለቶች በአጭሩ ካስረዳሁ በኋላ አማራጭ የመፍትሄ ሃሳብ አቀርባለው፡፡

የመጀመሪያው አማራጭ አሁን በሥራ ላይ ያለው ፓርላማ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 60 መሰረት እንዲፈረስ ከተደረገ በኋላ በስድስት ወራት ውስጥ ምርጫ ማካሄድ እንደሆነ መንግስት አስረድቷል፡፡ ነገር ግን ይህ አንቀጽ የሚመለከተው በፖለቲካ ፓርቲዎች አለመግባባት ምክንያት በጥምረት የተመሰረተ መንግስት በሚፈርስበት ወቅት በፓርላማው አብላጫ መቀመጫ ያለው ፓርቲ የማይኖርበትን ሁኔታ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ሲፈጠር ጠቅላይ ሚኒስተሩ ፓርላማውን ከበተነ በኋላ አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ ጥሪ የማቅረብ ሥልጣን በሕገ መንግስቱ ተሰጥቶታል፡፡ ነገር ግን በአንቀጽ 60 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ እንደተቀመጠው ይህ ተግባራዊ ሊደረግ የሚችለው በጠቅላይ ሚኒስተሩ ወይም በምክር ቤቱ የሥራ ዘመን ውስጥ ስለሆነ የሥራ ዘመኑ ያለቀ መንግስት ሥልጣን ላይ ለመቆየት እንደፈለገ የሚጠቀምበት መሣሪያ አይደለም፡፡

ሁለተኛው አማራጭ ምርጫ ከተካሄደ በኋላ ሥልጣን የሚይዝ መንግስት እስከሚኖር ድረስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተፈፃሚ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 93 እንደሚደነግገው ሌሎች ጉዳዮችን ጨምሮ የሕዝብ ጤንነትን አደጋ ላይ የሚጥል ወረርሺኝ ሲከሰት መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ ይችላል፡፡ ሆኖም ይህን ሁኔታ ከግምት ውስጥ ለማስገባት በቅድሚያ እስከመስከረም ድረስ ወረርሺኙን መቆጣጠር እንደማይችልና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማራዘም እንደሚያስፈለግ ሊወሰን ይገባል፡፡ሁለተኛ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መስከረም ላይ ቢራዘምም እንኳን አሁን ያለው መንግስት ከመስከረም 30 በኋላ ሥልጣን ይዞ መቀጠል የሚችል መሆኑን የሚያሳይ አይደለም፡፡ ወረርሺኙ በዚሁ ከቀጠለ የአዋጁን መፈፀም የማረጋገጥና የሕብረተሰቡን ጤንነት የመጠበቅ ኃላፊነት አሁን ያለውን መንግስት የሚተካው የአዲሱ ባላደራ አካል ኃላፊነት ይሆናል፡፡

ለውይይት የቀረበው ሦስተኛው አማራጭ ሕገ መንግስቱን ማሻሻል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት አንቀጽ 54 የፓርላማው አባላት በየአምስት አመቱ በሕዝብ እንደሚመረጡ ይደነግጋል፡፡ ስለዚህ የዚህ አማራጭ ሃሳብ ይህን አንቀጽ ማሻሻል ነው፡፡ ይህ የሚሆነው በፓርላማውና በፌደሬሽን ምክር ቤቱ የጋራ ስብሰባ በሁለት ሦስተኛ ድምፅ እንዲሁም ከፌደሬሽኑ አባል ክልሎች ምክር ቤቶች ውስጥ ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት በአብላጫ ድምፅ ውሳኔውን ካጸደቁት ነው፡፡ ይህ አማራጭ በዚህ ጊዜ ላይ ተግባራዊ ከተደረገ የሕጋዊነት/የተቀባይነት ቀውስ ማስነሳቱ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት በፌደራልም ሆነ በክልል ደረጃ ያሉት ሕግ አውጪ አካላት 100% መቀመጫ እንዳለው ይታወቃል፡፡ ይህን ያህል መቀመጫ ያገኘው ደግሞ በ2007 ዓ.ም በተደረገው የተጭረበረ ምራጫ ነው፡፡ሙሉ በሙሉ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት የሚቆጣጠራቸው ፓርላማ፣ የፌደሬሽን ምክር ቤትና የክልል ምክር ቤቶች የዚህ መንግስት ሥልጣን ይራዘም ወይስ አይራዘም በሚለው ጉዳይ ላይ ውሳኔ እንዲሰጡ ሃሳብ ማቅረብ ማለት አጠቃላይ ሂደቱ ለገዢው ፓርቲ ብቻ ሊተው ይገባል እንደማለት ነው፡፡ ይህ ጉዳይ እጅግ ጉዙፍ በመሆኑ ሥልጣን ይዞ ለመቀጠል የተቻለውን ሁሉ ለሚያደረግ ፖለቲካዊ አካል ሊተው አይገባም፡፡ ይህ ሂደት የፓለቲካ ፓርቲዎችንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በመግፋት ታዛቢዎች ብቻ እንዲሆኑ ካደረገ ከጅምሩ ተቀባይነቱን ያጣል፡፡ የዚህ ዓይነት ድንጋጌዎችን በመጠቀም የሥልጣን ጊዜን ማራዘም አምባገነን በሆኑ መንግስታት ውስጥ የተለመደ አሰራር ሲሆን በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት በዚህ መንገድ መጓዝ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፡፡ በዚህ መንገድ ከተጓዘ ግን መንግስት የአገሪቱን ዴሞክራሲ ለማረጋገጥ የገባውን ቃል እያጠፈ መሆኑን የሚያረጋገጥ ሌላ ማሳያ ይሆናል፡፡ በሕገ መንግስቱ መሠረት መካሄድ የነበረባቸው ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁት ሕዝባዊ ምክክሮችንና ውይይቶችን ማካሄድ አለመቻሉም መዘንጋት የለበትም፡፡

አራተኛውና የመጨረሻው አማራጭ መንግስት የሕገ መንግስት ትርጉም እንደያፈላልግ ማድረግ ነው፡፡ በእርግጥ የፌደሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግስቱን የመተርጎም ሥልጣን በሕገ መንግስቱ ተሰጥቶታል፡፡ ነገር ግን ይህ አማራጭ በሁለት ምክንያቶች የተነሳ መውጫ ወደሌለው አጣብቂኝ የሚመራ አማራጭ ነው፡፡
የመጀመሪያው የፌደሬሽን ምክር ቤት ትርጉም ሊሰጥ የሚችለው በሕገ መንግስቱ ለተፃፈ ድንጋጌ ነው፡፡ ሕገ መንግስቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተከሰተ ወረርሺኝ ጋር በተያያዘ ምርጫ የሚራዘምበትን አግባብ የሚመለከት ድንጋጌ የለውም፡፡ ማለትም ከምርጫ መራዘም ጋር የተያያዘ ፍርድ ቤት የቀረበ ጉዳይን የሚመለከት ድንጋጌ በሕገ መንግስቱ ውስጥ የለም፡፡ ክርክር የተነሳበት ድንጋጌ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ የፌደሬሽን ምክር ቤቱ ጣልቃ መግባት የሕግ ትርጉም እንደመስጠት ሳይሆን አዲስ ሕግን እንደመፃፍ ይቆጠራል፡፡ እንደዚህ አይነት ድንጋጌዎች ሕገ መንግስቱ ውስጥ እንዳይካተቱ የተደረገው በፓርላመው ውስጥ አብላጫ መቀመጫ ያለው ፓርቲ ድንጋጌዎቹን በመጠቀም ሥልጣኑን ለማራዘም እንዳይሞክር ነው፡፡

ሁለተኛይህን አማራጭ ለመውሰድ ብንስማማ እንኳን ጉዳዩ ሙሉ በሙሉ በሥልጣን ላይ ባለው መንግስት ቁጥጥር ሥር ወደ ሆነው የፌደሬሽን ምክር ቤት ይሄዳል ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በሁሉም ባለድርሻ አካላት ፍትሃዊና ተቀባይነት ያለው ተደርጎ ስለማይታይ የተቀባይነት ቀወስ መፈጠሩ አይቀርም፡፡
በመንግስት የቀረቡትን አራቱንም አማራጮች በጥንቃቄ ከመረመርኩ በኋላ ሁሉም አማራጮ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የተጋረጠብንን ሕገ መንግስታዊ ቀውስ ለመፍታት የማይችሉና የተፈፃሚነት ወይም የተቀባይነት ውስንነት ያለባቸው ሆነው አግኝቻቸዋለው፡፡ በጉዳዩ ላይ በሕግ ባለሙያዎች እየቀረቡ ያሉትንም ክርክሮች አንብቢያለው፡፡ ፖለቲካዊ መግባባታን በመፍጠር አስፈላጊውን ተቀባይነት/ሕጋዊነት ማረገገጥ ካልተቻለ ሕገ መንግስታዊ መፍትሄን መከተል ብቻ በቂ እንደማይሆን የመንግስትን አቋም የሚደግፉት እንኳን የሚስማሙበት ጉዳይ ነው፡፡

ስለዚህ መፍትሄው ሕገ መንግስታዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ ነው ማለት ነው፡፡ ለትርጉም በሚያመች መልኩ የትኛውንም የሕገ መንግስት ድንጋጌ ለመለጠጥ ቢሞከር እንኳን አንዱም ድንጋጌ አሁን ያለውን መንግስት ሥልጣን ከመስከረም በኋላ ሊያራዝም አይችልም፡፡ አገራዊ ምርጫ የሚካሄድበትን ቀን የሚመለከት ውሳኔ እንዲሁም ከመስከረም 30 በኋላ ምርጫው እስኪካሄድ ድረስ ምን አይነት ጊዜያዊ አስተዳደር ሊኖር እንደሚገባ የሚደረግ ውሳኔ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪል ማህበራትን ጨምሮ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በሚያደረጉት ውይይት ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ ብቻ ሊወሰን የሚገባው ነው፡፡ከዚያ ያነሰ ማንኛውም አካሄድ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ከመስከረም 30 በኋላ ለማስተዳደር ሕገ መንግስታዊ ሥልጣን ያለው አካል አይኖረም፡፡

ፖለቲካዊ መፍትሄ ስል ምን ማለቴ ነው?
የመጀመሪያው ጥያቄ የሚሆነው ሕገ መንግስቱ ምንድነው የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ሕገ መንግስት የአንድ አገር ዜጎች ሊገዙባቸው የተስማሙባቸውን መርሆች የሚያካትት ሰነድ ነው፡፡ እነዚህ መርሆች በግለሰቦችና በቡድኖች መካከል ያለውን የጎንዮሽ ግንኙነት እንዲሁም በግልሰቦች/በቡድኖች እና በመንግሰት መካከል ያለውን ግንኙነት የሚገልጹ መርሆች ናቸው፡፡ በሌላ አገላለፅ ሕገ መንግስት የመንግስትንና የዜጎችን ኃላፊነቶች፣ መብቶችና ግዴታዎች የሚዘረዘር ሰነድ ነው፡፡ በሕገ መንግስት ውስጥ የሚካተቱ መርሆች በአብዛኛው በባለሙያዎች ድጋፍ በተለያዩ የፖለቲካ ፍላጎቶች ተወካዮች መካከል ከሚደረግ ሰፊ ምክክር፣ ውይይትና ክርክር በኋላ የሚዘጋጁ ናቸው፡፡ ብዙውን ጊዜ በውይይቱ ውስጥ የሚሳተፉት ሰዎች በሕገ መንግስት ጉባዔ ውስጥ እንዲሳተፉ በዜጎች የሚመረጡ ናቸው፡፡ ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው መርሆች ለተጨማሪ ውይይት በሕዝባዊ መድረኮች ላይ ከቀረቡ በኋላ በሪፈረንደም መልክ ይፀድቃሉ፡፡ ሰነዱ ከፀደቀ በኋላ የአገሪቱ የበላይ ሕግ ይሆናል፡፡

ፍርድ ቤቶች ክርክሮች ላይ ውሳኔ ለመስጠት እንደመሪ ሰነድ ይጠቀሙበታል፡፡ የሕገ መንግስቱን መርሆች ለማስፈጽም ተጨማሪ ዝርዝር ካስፈለገ ሕግ አውጪው አዋጆችንና ደንቦችን ያወጣል፡፡፡ በሰነዱ ውስጥ የተካተቱት መርሆች ትርጉም በሚመለከት ክርክር ከተነሳ ሕገ መንግስቱ ራሱ የሚየቋቁመው አካል በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡ በበርካታ አገራት ይህ ሥልጣን ለጠቅላይ ፍርድ ቤቶችና በልዩ ሁኔታ ለተቋቋሙ ኮሚሽኖች የተሰጠ ሥልጣን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ይህ ሥልጣን የተሰጠው ለፌደሬሽን ምክር ቤት ሲሆን የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ደግሞ ከሕገ መንግስት ጋር የተያያዙ ክርክሮቹን የመመርመር ሥልጣን ተሰቶታል፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ቤቶችም ሆኑ በፌደሬሽን ምክር ቤት ሥራ ያለው አጣሪ ጉባዔ ሊተረጉሙ የሚችሉት በሰነዱ ውስጥ የተካተቱተን መርሆች ነው፡፡ እንግዲህ ምርጫንና የመንግስትን የሥራ ዘመን ማራዘምን በሚመለከት እየተነሳ እንዳለው ዓይነት በሕገ መንግስቱ ውስጥ ያልተካተተ ጉዳይ ሲያጋጥም ምን ሊደረግ ይችላል?

መፍትሄው በሰነዱ ዝግጅት ወቅት ወደተደረገው አሰራር መመለስ ነው፤ ማለትም ስለሚያከራክሩ ጉዳዮች ተወያይቶ ስምምነት ላይ መድረስ፡፡ ይህን ለማድረግ በቅድሚያ ሕገ መንግስቱን ያረቀቁትንና በድርደሩ ውስጥ የተሳተፉትን በሕገ መንግስቱ ውስጥ የምርጫ መራዘምን እና/ወይም የሥራ ዘመን መራዘምን የሚመለከቱ መርሆች/ድንጋጌዎች ለምን እንዳላካተቱ ልንጠይቃቸው ይገባል፡፡

በኔ አስተያየት ሁለት ዓይነት መልሶችን ልናገኝ እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከሰት ወረርሺኝ የምርጫዎችን መራዘም ሊያስገድድ ይችላል ብለው አላሰቡም፡፡ አገራት በእርስ በርስ ጦርነት መሃል፣ የውጭ ወረራ መቶባቸው ወይም የተፈጥሮ አደጋ አጋጥሟቸው እያለ ምርጫ ስለሚያካሂዱ ምርጫን የማይታሰብነገር ሊያደርግ የሚችል ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ብለው የሕገ መንግስት አርቃቂዎቹ አለማሰባቸውን መረዳት አያስቸግርም፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አብላጫ መቀመጫ ያላቸው አምባገነን የመሆን ፍላጎት የሚታይባቸው አካላት ክፍተቶችን ተጠቅመው ምርጫዎችን በማራዘም የሥልጣን ዘመናቸውን እንዳያራዝሙ አርቃቂዎቹ ሆን ብለው የተውት ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡ በርካታ አምባገነኖች የሥራ ዘመኖችን በማራዘም፣ ምርጫዎችን በማራዘም ወይም በመሰረዝ ሥልጣናቸውን ይዘው ለመቀጠል ስለሚሞክሩ አርቃቂዎቹ ለዚህ ዓይነት ተገቢ ያለሆነ ፖለቲካዊ ዘዴ ክፍተት ላለመተው አስበው ይሆናል፡፡ ይህን የሚደግፍ ማሳያም አለ፡፡ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 9(3) ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው ‹‹በዚህ ሕገ መንግስት ከተደነገገው ውጪ በማናቸውም አኳኋን የመንግስት ሥልጣን መያዝ የተከለከለ ነው››፡፡ ስለዚህ በየጊዜው ሊካሄድ የሚገባው ምርጫና የሥራ ዘመን መራዘም የሚችሉበት ሥነ-ሥርዓት አለመካተቱ የዚህን መርህ ዓለማ ማለትም በየጊዜው ከሚካሄድ ምርጫ ውጪ ሥልጣን መያዝ አይቻለም የሚለውን መርህ የሚያጠናክር ነው፡፡

አሁን ግን በኮቪድ-19 ወረርሺኝ ምክንያት ምርጫ ማካሄድ የማይቻል በመሆኑ ምርጫውን ሕጋዊ በሆነ መንገድ ለማስተላለፍና ምርጫው እስኪካሄድ የሥልጣን ክፍተት እንዳይፈጠር ምን ሊደረግ ይቻላል? በኔ አመለካከት በአርቃቂዎቹ ያልታሰበውን ይህን አዲስ ሕገ መንግስታዊ ችግር ለመፍታት አዲስ ፖለቲካዊ ስምምነት ላይ መድረስ መፍትሄ ይሆናል፡፡ ይህ ፖለቲካዊ ስምምነት ቀጣዩ ምርጫ መቼ መካሄድ እንዳለበት (በሕብረተሰብ ጤና ላይ የተጋረጠውን አደጋ ሁኔታ መገመት አደጋች በመሆኑ ግዴታ አንድ ቀን መወሰን ላያስፈልግ ይችላል) እንዲሁም አሁን ያለው መንግስት የሥልጣን ዘመን ካለቀ በኋላ ምርጫው እስኪካሄድ ድረስ የሚያስተዳድረው ጊዜያዊ መንግስት ባህሪ ምን መምስል አለበት የሚሉትን ጉዳዮች ሊያካትት ይገባል፡፡

በነዚህ ውይይቶች ውስጥ ማን ሊሳተፍ ይገባል?
ይህ ጉዳይ የሚመለከታቸው በርካታ ባለድርሻ አካላት ቢኖሩም ምርጫው ባይራዘም ኖሮ ለመወዳደር አስበው የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዋንኛነት የውይይቱ ተሳታፊዎች ሊሆኑ ይገባል፡፡ ስለዚህ በሕጋዊ መንገድ የተመዘገቡና በተራዘመው ምርጫ ለመሳተፍ መስፈርቶችን ያሟሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች በመከራከርና በመደራደር በጊዜያዊነት ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል አሰራር ላይ ሊስማሙ ይችላሉ፡፡ ይህ ጊዜያዊ ስምምነት አገሪቱ ምርጫ ማካሄድ ስትችልና አዲስ መንግስት ሲመሰረት የሚያበቃ ይሆናል፡፡ በአዲስ መልክ የሚመረጡት ሕግ አውጪዎች ካመኑበት ጊዜያዊ ስምምነቱን በማፅደቅ ሕግ አድርገው ሊያወጡት ይችላሉ፡፡ በሌላ በኩል አስፈላጊነቱን ከተቀበሉት ስምምነቱን በመተው የምርጫ መራዘመን በሚመለከት በሕገ መንግስቱ ያለውን ክፍተት የሚሞላ የመፍትሄ ሃሳብ ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡

ውይይቱን ማን ሊያስጀምረውና ሊመራው ይችላል?
እንደዚህ ዓይነት ወይይትን ሊያስተባብር የሚገባው ገለልተኛ የሆነና ከሂደቱ ውጤት የሚጠብቀው ቀጥተኛ በሆነ መንገድ ለአንድ ወገን የሚያደላ ፍላጎት የሌለው አካል ነው፡፡ እስካሁን የተደረጉት ጥቂት ውይይቶች በሰብሳቢነት የመራው ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ነው፡፡ በውይይቱ ውጤት ማለትም በምርጫው መራዘምና ጊዜያዊው መንግስት ምን ዓይነት ባህሪይ ሊኖረው ይገባል በሚለው ጉዳይ ላይ ቀጥተኛ የሆነ ፍላጎትና አቋማ ያለው የገዢው ፓርቲ ፕሬዝዳንት በመሆናቸው ውይይቱን እሳቸው ሊመሩት እንደማይገባ ግልጽ ነው፡፡ እስካሁን የተደረጉት ውይይቶችም ለዚህ ጥሩ ማሳያ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ተቃዋሚዎችም ይህን መድረክ ሊያዘጋጁ አይችሉም፡፡ ስለዚህ ያለው አማራጭ ሁሉም ሊቀበሉት የሚችሉ ሦስተኛ ወገን የሆነ ሰው ወይም ተቋም ነው፡፡ ይህን ማድረግ ካልተቻለና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ውይይቱ አሁን ባለው መንግስታዊ መዋቅር ሥር መካሄድ እንዳለበት ከተስማሙ ጉዳዩ በቀጥታ የማይነካውን ተቋምና አመራር ተስመምተው ሊመርጡ ይችላሉ፡፡

በምርጫው በቀጥታና በቅርበት የማይመለከታቸው የፕሬዝዳንት ጽ/ቤትና ጠቅላይ ፍርድ ቤት ናቸው (የምርጫውም ሆነ የሥራ ዘመኑ መራዘም በቀጥታ አይመለከታቸውም)፡፡ የሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንትና ጠቅላይ ፍርድ ቤት ገለልተኛና ከፓርቲ ፖለቲካ ነፃ ሊሆኑ ይገባል፡፡ በተለይ ደግሞ ፕሬዝዳንት በማንኛውም ፖለቲካዊ ጉዳይ ውስጥ ተሳትፎ ማድረግ ስለማይችል የምክር ቤት አባል ከነበረ እንኳ የተወከለበትን ወንበር መልቀቅ የሚጠበቅበት የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ነው፡፡ የፕሬዝዳንት የሥራ ዘመን ከሕግ ውጪውና ከሕግ አስፈፃሚው በላይ እንዲረዝም የተደረገውም በምርጫ ወቅት የመንግስትን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ነው፡፡ ለምሳሌ በአዲስ መንግስትና በምርጫ በተሸነፈ መንግስት መካከል የሚደረገውን የሥልጣን ርክክብ የሚቆጣጠረው ፕሬዝዳንቱ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት አሁን ያሉት ፕሬዝዳንት የውይይት መድረኩን ከማዘጋጀትና ከማስተባበር አልፈው ስምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮች መፈፀማቸውን መከታተልና ሁሉም አካላት ግዴታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይችላሉ፡፡ በዚህ ሥራ ውስጥ ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የተለያዩ ባለሙያዎች ለፕሬዝዳንቷ ድጋፍ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡
የምርጫን ሆነ የሥራ ዘመን መራዘምን በሚመለከት ሕገ መንግስታዊ አቅጣጫ በሌለበት እንዲህ ዓይነት ልዩ ሁኔታ ውስጥ ገለልተኛ አካል በሚመራው ውይይት የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ስምምነት ላይ ቢደርሱ ምርጫውን ለማራዘም የሚደረገው ሂድት በሕዝቡ ዓይንና በተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ያደርገዋል፡፡

በመጨረሻ ጥቂት የማጠቃለያ ነጥቦችን ላንሳ፡፡ የመጀመሪያው እኔ እስከማውቀው ድረስ የምርጫውን መራዘም የሚቃወም አንድም ፓርቲ የለም፡፡ ምክንያቱም የኮቪድ-19 ወረርሺኝ በሕብረተሰቡ ጤና ላይ የተጋረጠ ሥጋት መሆኑና በቀላሉ ሊታይ እንደማይገባ አጠቃላይ ግንዛቤ አለ፡፡ ክርክር ያለው ምርጫው የሚራዘምበት መንገድ ላይና በቀጣይ ሊፈጠር የሚችለውን የሥልጣን ክፍተት እንዴት መሙላት ይችላል በሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ሁለተኛ ከሕገ መንግስቱ ቀውስ በተጨማሪ ላለፉት 29 አመታት በጥብቅ ቁጥጥር ሲያስተዳደር የነበረው ገዢ ፓርቲ በተጭበረበረ ምርጫ አባላቱ የተቆጣጠሯቸውን ሕግ አውጪ አካላት በመጠቀም ሕገ መንግስቱን በማሻሻል ወይም በመተርጎም የሥልጣን ዘመኑን ለማራዘም መሞከሩ በፍጹም ተቀባይነት የለውም፡፡

ገዢው ፓርቲ ከተቃዋሚ ፓርቲዎችና ከባለደርሻ አካላት ጋር ለመደራደር ፍቃደኛ ሳይሆን የሥራ ዘመኑን ካራዘመ የሕገ መንግስቱን አንቀጽ 9(3) በመጣስ በሕገወጥ መንገድ ሥልጣን እንደያዘ ይቆጠራል፡፡ ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግስት ተቋም ወይም የውጭ ኃይል እንደዚህ ዓይነትን መንግስት ሕጋዊ ነው ብሎ እንዲቀበለው አይጠበቅም፡፡ ይህ ደግሞ ለአገሪቱ መረጋጋትና አንድነት ከፍተኛ አደጋ የሚፈጥር ሲሆን የኮቪድ-19ን መስፋፋት መቆጣጠርና ከሚያደርሰው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ በፍጥነት ለማገገም መንቀሳቀስ ባለብን ወቅት መከሰት የሌለበት ነው፡፡

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.