አስተያየት፡ የኢትዮጵያ የሕገ መንግስት ጊዜ ፋይዳ/ ለኢትዮጵያ የሕገ መንግስት ጊዜ ትርጉም መስጠት/

ዮናታን ፍስሃ @YonatanFessha
ዘመልዓክ አየለ @zemelak_a
ሰለሞን ደርሶ @SolomonADersso&
አደም አበበ @AdamAbebe

አዲስ አበባ ግንቦት 6, 2012፡ የኢትዮጵያን ሕገ መንግስት ለሚያጠኑ ምሁራን እንዳለፉት ሳምንታት ዓይነት ትኩረት ሳቢ ጊዜን ማስታወስ ያዳግታል፡፡ በሕገ መንግሰቱ ዙሪያ የተደረገው ውይይት ሕገ መንግስቱ ላይ አመኔታ የሌላቸውን አካላት ትኩረት ሳይቀር መሳብ ችሏል፡፡ በሌላ በኩል ባለሙያዎቹ ያቀረቧቸው ተፃራሪ ሃሳቦች አንዳንዶችን ግራ ያጋቡ ሲሆን አንድ የትዊተር ተጠቃሚ ‹‹ሕገ መንግስቱ የተፃፈው በቻይንኛ ነው እንዴ?›› እስከማለት ደርሷል፡፡

የተቃራኒ ሃሳቦች መንፀባረቅ የማንኛውም ሕግ ነክ ውይይት ባህሪ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በአብዛኛው ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ሳያተኩር ጠቅለል ያለ ይዘተ እንዲኖረው ተደርጎ የሚዘጋጅ ሕገ መንግስት ላይ በሚደረግ ክርክር ውስጥ ጎልቶ ሊታይ ይችላል፡፡ በዚህ ሃሳብ መንፈስና በተፈጠረው ተነሳሽነት ምክንያት ይህንን ጽሁፍ በጋራ ለማዘጋጀት ወስነናል፡፡ ጽሁፉን ያዘጋጀነው የሕገ መንግስት ትርጓሜ ለማሰጠት መንግስት ስለመረጠው መንገድ እንዲሁም የፌድሬሽን ምክር ቤት እና የሕገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ በቀጣይ ስለሚገጥሟቸው ጉዳዮች ጥቂት ተጨማሪ ሃሳቦችን ለማጋራት ነው፡፡
በቅድሚያ ሁሉም ነገሮች የሚያከራክሩ አለመሆናቸው ሊሰመርበት ይገባል፡፡ በፌደራልና በክልል ደረጃ በነሐሴ እንዲደረግ ታስቦ የነበረው ምርጫ በተያዘለት ጊዜ ሊካሄድ እንደማይችል ከሞላ ጎደል ሁሉም ይስማማል፡፡ በኮቪድ-19 ምክንያት በመንግስት የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በርካቶች ይደግፉታል፡፡ አሁን ያለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመኑ ከመጠናቀቁ በፊት ምርጫ ማካሄድ ካልተቻለ ምን መደረግ እንዳለበት አቅጣጫ የሚሰጥ ግልፅ/ቀጥተኛ የሕገ መንግስት ድንጋጌ አለመኖሩን ሁሉም ይስማማል፡፡ ልዩነት ያለው ይህ የሕገ መንግስት ዝምታ እንዴት ይተረጎማል የሚለው ላይ ነው፡፡

የሕግ መንግስቱ ዝምታ
ለአንዳንዶች የሕገ መንግስቱ ዝምታ ሕገ መንግስታዊ መፍትሄ አለመኖሩን የሚያመላክት ነው፡፡ በመሆኑም ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲሰጥ ጥሪ ያቀርባሉ፡፡ ነገር ግን አንዳንዶቻችን እንደተከራከርነው ይህ ጥሪ ሕገ መንግስቱን ወደ ጎን ለመተው የጋራ ስምምነት ላይ ለመድረስ የተደረገ ጥሪ ይሆናል፡፡ ሌሎች ደግሞ ለዚህ ፖለቲካዊ አማራጭ ሕገ መንግስታዊ መሰረት ለመስጠት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክር ቤቱን ከበተነ በኋላ ባላደራ መንግስት እንዲቋቋም የሚፈቅዱት የሕገ መንግስቱ ድንጋጌዎች ተግባራዊ እንዲደረጉ ጥሪ ያደርጋሉ፡፡

ይህ የመፍትሄ ሃሳብ ሁለት ዋና ዋና ችግሮች አሉበት፡፡ የመጀመሪያው በሕገ መንግስቱ ንባባችን መሰረት ምክር ቤቱን የመበተን ዓላማ የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን ከማለቁ በፊት አዲስ ምርጫ ለማካሄድ ነው፡፡ ይህ ዓይነት ምርጫ በተለምዶ ድንገተኛ ምርጫ (snap elections) ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን የፓርላሜንታሪ ዴሞክራሲ ሥርዓት በሚከተሉ አገሮች የተለመደ አሰራር ነው፡፡[1]አሁን የገጠመን ተግዳሮት ግን ይህ ነው ብለን አናምንም፡፡ ቀጣዩ ምርጫ የምክር ቤቱ የአምስት ዓመት የሥራ ዘመን ከመጠናቀቁ በፊት ይካሄዳል የሚል እሳቤ የምክር ቤቱን መበተን ከሚመለከተው ድንጋጌ ጀርባ አለ፡፡ ይህን ድንጋጌ በዚህ መልክ መረዳት ካልተቻለ በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት የሥልጣን ጊዜው ሊያበቃ ሲል ምክር ቤቱን ሆን ብሎ በማፍረስ የስልጣኑን ጊዜ ቢያንስ ለስድስት ወራት ማራዘም ይችላል ማለት ነው፡፡ ሁለተኛ ይህ የመፍትሔ ሃሳብ የሕገ መንግስቱ አንቀፅ 60 ተግባራዊ ተደርጎ ምክር ቤቱ ከተበተነ በኋላ በሥልጣን ላይ ያለውን መንግስት የሚተካ አሳታፊ የሆነ ባላደራ መንግስት መቋቋም አለበት የሚል አቋም ይዟል፡፡ ነገር ግን ሕገ መንግስቱ ይህን አይደነግግም፡፡ ምክር ቤቱ ከተበተነ በኋላ በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት የተገደቡ ኃላፊነቶችን ይዞ ሃገሪቱን ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ማስተዳደር እንደሚቀጥል ሕገ መንግስቱ ይገልፃል፡፡

ይህ የመፍትሔ ሃሳብ ሌሎች ችግሮችም አሉበት፡፡ ምክር ቤቱ ከተበተነ በርካታ ባለድርሻ አካላትን የሚያሳትፍ ሁሉን አቀፍ የሆነ ጊዜያዊ ባላደራ መንግስት ለማቋቋም ረዥም ጊዜ ሊወስድ ይችላል፡፡ በተጨማሪም በቀጣይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማራዘም ቢያስፈልግ ወይም ሌላ አዲስ አዋጅ ማውጣት ቢያስፈልግ በሕገ መንግስቱ መሰረት የአስቸኳይ ጊዜውን ማራዘም የሚችል ወይም ሕጉን የሚያፀድቅ ምክር ቤት አይኖርም፡፡ በመጨረሻም ባላደራ መንግስትን የማቋቋም ፅንሰ ሃሳብ ከአስቸኳይ ጊዜ ፅንሰ ሃሳብ ጋር የሚጣጣም አይደለም፡፡ ይህን በመሰለ ጊዜ ውስጥ መንግስት የተገደበ ሥልጣን ኖሮት የሚንቀሳቀስ ሳይሆን የተሟላና ሲያሻም ልዩ ሥልጣኖችን ይዞ ማስተዳደር ያለበት ወቅት ነው፡፡ ለምሳሌ መንግስት የንግድ ቦታዎችን ሊዘጋ፣ ሰዎች በየቤታቸው ብቻ ፀሎት እንዲያደርጉ ሊያዝና ሌሎች መሰል ተግባራትን በአስቸኳይ ጊዜ ወቅት እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ ሊያከናውን ይችላል፡፡

እኛ በዚህ ጉዳይ የሕገ መንግስት ዝምታ እንዳለ እናምናለን፡፡ ነገር ግን የሕገ መንግስት ዝምታ አለ ማለት ሕገ መንግስታዊ መፍትሄ የለም ማለት እንዳለሆነም እናምናለን፡፡ የሕገ መንግስት ትርጉም የሚያስፈለግው ግልፅ ያልሆነ ድንጋጌ ሲኖር ብቻ ሳይሆን ክፍተት ሲኖርና ያልታሰበ ሁኔታም ሲፈጠር ነው፡፡ ፍርድ ቤቶችና የሕገ መንግስት ትርጉም የመስጠት ሥልጣን ያላቸው አካላት የሕገ መንግስቱን መሰረታዊ መርሆችና አጠቃላይ አወቃቀር መሰረት በማድረግ ሕገ መንግስታዊ ትርጉም እየሰጡ ለክፍተቶችና ላልታሰቡ ሁኔታዎች መፍትሄ ያቀርባሉ፡፡ አሁን ያሉት ውይይቶች የሕገ መንግስት ትርጉም የማይቅር መሆኑን ያሳያሉ፡፡

የፌደሬሽን ምክር ቤት የማማከር ሥልጣን
አንዳንዶች ምክር ቤቱ ምክረ ሃሳብ የመስጠት ሥልጣን እንደሌለው ይከራከራሉ፡፡ ነገር ግን የፌደሬሽን ምክር ቤትን ለማጠናከርና ሥልጣንና ተግባሩን ለመዘርዘር የወጣው አዋጅ በሕገ መንግስት ትርጉም ዙሪያ ‹‹የምክር አገልግሎት›› መስጠት ያለመስጠት ውሳኔው የምክር ቤቱ እንደሆነ ይደነግጋል፡፡[2]ሌሎች ደግሞ የዚህን አዋጅ ሕገ መንግስታዊነት ራሱ ይጠራጠራሉ፡፡ ልንደገፍ የሚገባን በሕገ መንግስቱ ድንጋጌዎች ላይ ብቻ ነው ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ ይህ ግን ችግር የሚፈጥር አቋም ነው፡፡ ምክንያቱም ማንኛውም ሥልጣን ተቀባይነት የሚኖረው በግልፅ ሕገ መንግስቱ ላይ ከተደነገገ ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ ነገሩ ግን እንደዚህ አይደለም፡፡ አዋጆችና ደንቦች ዝርዝር ድንጋጌዎችን በማውጣት በሕገ መንግስት ውስጥ የተቀመጡ ጠቅላላ ጉዳዮችን ያስፈፅማሉ፡፡ በተጨማሪም በሕገ መንግስቱ በግልፅ ካልተደነገገ በስተቀር ፓርላማው አንድን አዋጅ ማፅደቅ አይችልም የሚለው ክርክር ሕገ መንግስታዊ ሕግ የማውጣት ግዴታን መንግስት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሕጎችን ለማውጣት ካለው መብት ጋር የሚያምታታ ነው፡፡ ምክር ቤቱ ከሕገ መንግስቱ ጋር ይጣረሳሉ ብሎ አዋጆቹንና ደንቦቹን ካልሻራቸው በስተቀር ለተለያዩ አካላት የሚሰጡት ሥልጣን ቀጣይ እንደሚሆንና የአገሪቱ ሕግ ሆነው እንደሚቀጥሉ በዚህ ክርክር የተረሳ እውነታ ነው፡፡

በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ የፌደሬሽን ምክር ቤትና የሕገ መንግስት አጣሪ ጉባኤው የማማከር ሚና ሕገ መንግስታዊ መሰረት ያለው ነው፡፡ ሕገ መንግሰቱ ሰፊ የሆነውን ሕገ መንግስቱን የመተርጎም ሥልጣን ለምክር ቤቱ ይሰጣል፡፡ ከሕገ መንግስቱ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ክርክሮች ሲነሱ የሕገ መንግስት ትርጉም የሚሰጥ ቢሆንም አንድ አካል ሕገ መንግስቱን በሚመለከት ምክር ሲፈልግም የሕገ መንግስት ትርጉም ሊሰጥ ይችላል፡፡ የሕገ መንግስቱ አርቃቂዎችም ሃሳብ ይህ ነበር፡፡ ‹‹የሕገ መንግስት አጣሪ ጉባኤው ከሕገ መንግስት ጋር የተያያዙ ክርክሮችንና የሕግ መንግስት ትርጉምን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በማጣራት ለፍርድ ቤት ወይም ለሚመለከተው አካል ሃሳቡን ሊያቀርብ ይችላል›› በማለት ገልጸዋል፡፡[3]የአጣሪ ጉባኤውን ተግባራትና ሥልጣን የሚዘረዝረው አዋጅ አንድ ሦስተኛው ወይም ከዚያ በላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሕገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ ሊያቀርቡ እንደሚችሉ በመደንገግ ጉዳዮችን የማጣራት መብት ለጉባኤው የሰጠው በዚህ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡[4]በዚሁ ተመሳሳይ ምክንያት የፌደሬሽን ምክር ቤትን ሥልጣንና ተግባራትን የሚዘረዝረው አዋጅ ለምክር ቤቱ የማማከር አገልግሎቶችን የመስጠት መብት ይሰጠዋል፡፡ በዚያ ላይ በኢትዮጵያ ሕገ መንግስቱን የመተርጎም ሥልጣን ለፍርድ ቤቶች ሳይሆን ለፖለቲካ አካል የተሰጠ በመሆኑ የማማከር ሥልጣን ችግር የሚፈጥር ጉዳይ አይሆንም፡፡ ምናልባት የትርጉም ጥያቄው በቀጥታ ለፌደሬሽን ምክር ቤት እንዲቀርብ ተደርጎ ምክር ቤቱ በሥሩ ላለው የባለሙያዎች አካል ማለተም ለአጣሪ ጉባኤው እንዲመራው ማድረግ ይቻል ነበር፡፡

በማንኛውም ሁኔታ ግን ምክር ቤቱ ምክረ ሃሳቡን ሲያቀርብ ይህ የመጀመሪያ ጊዜው አይደለም፡፡በ1992 ዓ.ም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት የፌደራል መንግስት የቤተሰብ ሕግ ማውጣት ይችላል ወይስ አይችልም በሚለው ጉዳይ ላይ ምክር ቤቱ አስተያየት እንዲሰጥ ተደርጓል፤ ይህ ሥልጣን በግልፅ የፌደራል መንግስት ሥልጣን ነው በሚል በሕገ መንግስቱ ውስጥ አልተደነገገም፡፡ ምክር ቤቱ የፌደራል መንግስት የቤተሰብ ሕግ ሊያወጣ እንደሚችል ነገር ግን ሕጉ በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ የሚደረግ ሳይሆን የተፈፃሚነት ወሰኑ በሁለቱ ከተሞች ብቻ (አዲስ አበባና ድሬዳዋ) የተገደበ መሆን አለበት የሚል ውሳኔ ሰቷል፡፡ በቅርብ ጊዜ በታህሳስ 2007 ዓ.ም ደግሞ የኢ.ፌዲ.ሪ ሕገ መንግስት የመሬት አስተዳደር ሥልጣን የክልሎች እንደሆነ በግልፅ ስለሚደነግግ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት የከተማ መሬት ምዝገባን በሚመለከት እርምጃ ለመውስድ ሥልጣን እንዳላቸውና እንደሌላቸው እርገጠኛ መሆን አልቻሉም ነበር፡፡

በመሆኑም ለፌደሬሽም ምክር ቤት ጥያቄ አቅርበው ምላሽ አግኝተዋል፡፡ ይህ ማለት ግን የፌደሬሽን ምክር ቤቱ ምክረ ሃሳብ አለመስጠት አይችልም ወይም ምክረ ሃሳብ አልሰጥም ብሎ አያውቅም ማለት አይደለም፡፡ አዋጁ በገልፅ እንዳስቀመጠው ምክር ቤቱ ምክር የመስጠት መበት አለው እንጂ ምክር የመስጠት ግዴታ የለበትም፡፡ እንደዚህ መደረጉ ምክር ቤቱን የሚያጨናንቁ በርካታ ጥያቄዎችን ከመገደብ አንፃር መልካም ውሳኔ ቢሆንም እንደዚህ አይነት ሰፊ መብት ግን ለፖለቲካ አላማ ሊውል ይችላል፡፡
እኛ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የተከተለቸው የሕገ መንግስት አተረጓጎም ሥርዓት ላይ ጥርጣሬ አለን፡፡ ተቋማዊ ሥርዓቱ አመቺ/ተስማሚ አይደለም፡፡ ገለልተኛ መሆኑ አጠያያቂ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ፖለቲካዊ ችግር ይፈጥራል፡፡ ነገር ግን ሕገ መንግስታዊ አመራጭ ነው፡፡ ምናልባት ተስፋ ማድረግ ያለብንናማተኮር ያለብን አጣሪ ጉባኤውና የፌደሬሽን ምክር ቤቱ በሚከተሉት ሂደት እንዲሁም በመጨረሻ በሚሰጡት ምክረ ሃሳብ መሰረት ተግባራዊ የሚደረገው የመፍትሄ ሃሳብ ሊያመጣ የሚችለውን አሉታዊ ተፅዖኖ መቀነስ መቻላቸው ላይ ነው፡፡

ሂደቱ
በፌደሬሽን ምክር ቤትና በአጣሪ ጉባኤው ላይ መደገፍን አሳሳቢ ካደረጉት ጉዳዮች መካከል ዋንኛው እነዚህ ተቋማት በግልፅነታቸውና በአሳታፊነታቸው የሚታወቁ ተቋማት አለመሆናቸው ነው፡፡ ምንም እንኳን ባለሙያዎችን የመስማት መብት ተሰቷቸው ሕዝባዊ ስብሰባዎችን እንዳያደርጉ የሚከለክል ድንጋጌ ባይኖርም የአጣሪ ጉባኤው ውይይቶች እስከዛሬ ይፋ ተደረገው አያውቁም፤ ውሳኔዎቻቸውም አይታተሙም፡፡ ይህ በተቋማቱ ላይ ያለውን አመኔታ ከመሸርሸሩ ባለፈ ከፖለቲካ አካላት ተፅዕኖ ነፃ አይደሉም የሚል አስተሳሰብ እንዲኖር አድርጓል፡፡
የሕገ መንግስቱ አንቀፅ 12 የመንግሰት አሰራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ ይህ ሕገ መንግስታዊ የግልፅነት መርህ በሁሉም የመንግሰት ተቋማት ላይ ተፈፃሚነት አይኖረውም የሚያስብል ምንም ነገር የለም፡፡ እንዳውም እንደፌደሬሽን ምክር ቤቱና እንደአጣሪ ጉባኤው ላሉ የፍርድ ሥልጣን ያላቸው ተቋማት የፍርድ ሂደት ዋና መርህ የሆነው ለሕዝብ ግልፅ/ክፍት የሆኑ ስብሰባዎችን/ችሎቶችን ማድረግ ዋና መገለጫቸው ሊሆን ይገባል፡፡ ጉዳዩ ከሕዝብ ጥቅም ጋር በቅርበት የተያያዘ በሆነ ቁጥር ስብሰባዎቹ ለሕዝብ ግልጽ እንዲሆኑ የማድረግ ሕገ መንግስታዊው ግዴታ ይበልጥ ይጎላል፡፡ በመሆኑም በቅርብ ጊዜ ውይይቶቹ በመገናኛ ብዙሃን እንዲተላፈፉ ተደርጎል፡፡

ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልክ አጣሪ ጉባኤው በሕገ መንግስት ትርጓሜ ላይ አስተያየታቸውን በጽሁፍ እንዲያቀርቡ ለሕግ ባለሙያዎች ጥሪ አድርጎ ነበር፡፡ የተመረጡ ባለሙያዎችንም ሃሳብ ለሕዝብ ግለፅ በሆነ መድረክ ላይ ይሰማል፡፡ እነዚህም ውይይቶች በቀጥታ ሥርጭት እንዲተላለፉ ይደረጋል፡፡ ሂደቱን ለሕዝብ በዚህ መልክ ክፍት ማድረግ ከሕብረተሰቡ ጋር ለመቀራረብና ተቋማቱ ነጻነት እንዲሁም ብቃት የላቸውም የሚለውን አስተሳብ ለማስወገድ ይጠቅማል፡፡ ነገር ግን ባሉት ተቋማዊ ውስንነቶች ምክንያት ለሚነሱት በርካታ የተቀባይነት/ሕጋዊነት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የተሻለ ተሳትፎን የሚያረጋግጡ ተጨማሪ አዳዲስ አሰራሮች ተግባራዊ መደረግ እንዳለባቸው እናምናለን፡፡ በመሆኑም የሂደቱን ተቀባይነት/ሕጋዊነት በተሟላ ደረጃ ለማረጋገጥ ተሳትፎው የሕግ ባለሞያዎችን ብቻ የሚያካትት ሳይሆን ሌሎች የሚመለከታቸው የሕብረተሰቡ አካላትም ሃሳባቸውን እንዲያቀርቡ የሚፈቅድ ነፃ አሰራር ሊኖር ይገባል፡፡

ምክረ ሃሳቡ፡ ከሚጠበቀው በላይ መሄድ
ከፌደሬሽን ምክር ቤቱና ከአጣሪ ጉባኤው ሁለት ዓይነት አስተያየቶችን መጠበቅ እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው ሕገ መንግስቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን የሥራ ዘመን በሚመለከት ያስቀመጠው ድንጋጌ ግልፅ እንደሆነና የሥራ ዘመኑ የሚራዘምበት ሕገ መንግስታዊ መሰረት የለም የሚል ምክር ሃሳብ ለመንግስት ሊያቀርብ ይችላል፡፡ በተቃራኒው የሚቀጥለው ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት ማስተዳደር እንዲቀጥል ሃሳብ ሊያቀርብ ይችላል፡፡ የመጀመሪያው አማራጭ ሕገ መንግስታዊ ቀውስ ውስጥ እንደሚከተን አያጠራጥርም፡፡ ምክንያቱም በሥራ ላይ ያለው ፓርላማ የሥራ ዘመን መስከረም 30 ላይ ከማለቁ በፊት ምርጫ ማካሄድ እንደማይቻል ግልጽ ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁለተኛው አማራጭ መንግስት አጋጣሚውን በመጠቀም ምርጫውን ላልተወሰነ ጊዜ ሊያራዝም ይችላል የሚለው ሃሳብ በርካቶችን ስጋት ውስጥ ከቷል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የፌደሬሽን ምክር ቤት ፓርላማው የሥራ ዘመኑን ማራዘም ይችላል ወይስ አይችልም በሚለው ጉዳይ ላይ ምክረ ሃሳብ ከመስጠት ባለፈ ምርጫው በአጭር ጊዜ ውስጥ መካሄዱን የሚያረጋግጥ ወይም በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት ከሥራ ዘመኑ በኋላ መቀጠል የማይችል ከሆነ ሕገ መንግስታዊ ቀውስን ማስቀረት የሚችል ሃሳብ ማቅረብ ይችላል ወይስ አይችልም የሚለው ጥያቄ ይነሳል፡፡

በብዙ አገሮች ውስጥ ፍርድ ሰጪ አካላት የአንድን ውሳኔ ወይም ሕግ ሕገ መንግስታዊነት ከመወሰን ባለፈ ተጨማሪ ትዕዛዝ የመስጠት በግልፅ ወይም በተዘዋዋሪ የተደነገገ ሕገ መንግስታዊ ሥልጣን አላቸው፡፡ ያስተላለፉትን ትዕዛዝ በማስፈፀም ሥራ ውስጥም ቀጥተኛ ተሳትፎ ያደርጋሉ፡፡ ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጄከብ ዙማ መኖሪያ ቤታቸውን ለማሳደስ ያለአግባብ ከሕዝብ ሃብት ላይ 25 ሚሊየን ዶላር ወሰደው ነበር፡፡ የአገሪቱ እምባ ጠባቂ ይህ ድርጊት ተገቢ ባለመሆኑ ገንዘቡን እንደመልሱ ጠይቀዋቸዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ግን ትዕዛዙን ለመፈፀም አልተስማሙም፡፡ ጉዳዩ የሕገ መንግስት ፍርድ ቤት ደረሰ፡፡ ፍርድ ቤቱም የፕሬዝዳንቱ ድርጊት ‹ኢሕገ መንግስታዊ› ነው ሲል ፍርድ ሰጠ፡፡ ፍርድ ቤቱ ከውሳኔው ባለፈ ፕሬዝዳንቱ ገንዘቡን የሚመልሱበትንም አግባብ አስቀምጧል፡፡ በመቀጠል ከወጣው ወጪ ፕሬዝዳንቱ ለመንግስት የሚመልሱት ምን ያህሉን እንደሆነ ወስኖ ለፍርድ ቤቱ ሪፖርት እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ለአገሪቱ ብሄራዊ ትሬዠሪ ተላለፈ፡፡ በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ የብሄራዊ ተሬዠሪ ተቋሙን ሪፖርት ካፀደቀ በኋላ በተቋሙ የተወሰነውን የገንዘብ መጠን ፕሬዝዳንቱ እንዲከፍሉ ትዕዛዝ ሰቷቸዋል፡፡ በደቡብ አፍሪካ የሕገ መንግሰት ፍርድ ቤትና የሌሎች አገራት ፍርድ ቤቶች ያላቸው ቀጥተኛ ተሳትፎ የማድረግ ሥልጣን የፌደሬሽን ምክር ቤት የፓርላማው የሥራ ዘመን ሊራዘም ይችላል ወይስ አይችልም በሚለው ጉዳይ ላይ ምክረ ሃሰብ ከመስጠት ያለፈ ሚና ሊኖር ይችላል ወይስ አይችልም የሚለውን ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ችግሩ አሁን የተፈጠረው ሁኔታ ግጭት ወይም ክርክር አይደለም፡፡ የተጠየቀው ምክር ሃሳብ ነው፡፡ ሆኖም የሁኔታዎቹን መመሳሰል ማነፃፀር ስህተት አይሆንም፡፡

የፌደሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግስቱን የመተርጎም የመጨረሻ ስልጣን ያለው ተቋም እንደመሆኑ የሕገ መንግስቱና የሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱ ጠባቂ ነው፡፡በዚህ ምክንያት አጣሪ ጉባኤውና የፌደሬሽን ምክር ቤቱ የፓርላማው የሥራ ዘመን መራዘምን በሚመለከተ ብቻ ለመንግስት ምክር ሃሳብ ማቅረባቸው በቂ እንደማይሆን እናምናለን፡፡ የፓርላማው የሥራ ዘመን መራዘም አለበት የሚል ምክረ ሃሳብ ከቀረበ ምክር ቤቱና አጣሪ ጉባኤው ቢያንስ ሁለት ነገሮችን የሚያረጋግጥ አሰራር እንዲዘረጋ መጠቆም ይኖርባቸዋል፡፡ የመጀመሪያው ጉዳይ ሁኔታው ሲፈቅድ ምክንያታዊ በሆነ የተወሰነ ጊዜ ውስጥ ምርጫው መካሄዱን የሚያረጋገጥ አሰራር ነው፡፡ በዚህ ረገድ ምክር ቤቱና አጣሪ ጉባኤው መንግስት አዎንታዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ሥልጣን ያለአግባብ ሊያዝ ይችላል የሚል ሥጋት ያለባቸውን አካላት ፍራቻ ማስወገድ እንዳለበት ሃሳብ ሊያቀርቡ ይገባል፡፡ በተጨማሪም አገሪቱ ለምርጫ ዝግጁ መሆኗን በየጊዜው የሚፈትሽ የባለሙያዎች ኮሚቴ እንዲቋቋም ሃሳብ ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ይህ ጉዳይ አሁንም የሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች አመኔታ ለማግኘት እየታገሉ ላሉት የአስፈፃሚ አካላትና ለምርጫ ኮሚሽኑ ሊተው አይገባም፡፡ ዞሮ ዞሮ የአብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስጋት ምርጫው መራዘሙ ሳይሆን ከሚፈለገው በላይ ምርጫው እንዳይራዘም ነው፡፡

ሁለተኛው በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት ምርጫው እስኪካሄድ ድረስ ያላግባብ መንግስታዊ ተቋማትን በመጠቀም ተቃዋሚዎችን ለመርታትና ለምርጫው የሚያግዙትን ሁኔታዎች እንዳያመቻች የጥንቃቄ እርምጃ እንዲወሰድ ምክር ቤቱ ሃሳብ ማቅረብ አለበት፡፡ ይህ መንግስትና ሌሎች አካላት የተወሰኑ ውሳኔዎችን እንዳያስተላልፉ ወይም በተወሰኑ እንቅስቃሴዎች ውስጥ እንዳይሳተፉ ምክር መስጠትን ያካትታል፡፡ ከዚያም አልፎ ተቀባይነት የሌላቸው ተግባራት ወይም እንቅስቃሴዎች ምን እንደሆኑ ሊጠቁም ይችላል፡፡ ሆኖም ምክር ቤቱ የፓርላማው የሥራ ዘመን እንደማይራዘምና አሁን ያለው መንግስት ሥልጣን መስከረም ላይ ያበቃል የሚል ምክረ ሃሳብ ካቀረበ በቀጣይ አገሪቱን እንዴት ማስተዳደር እንደሚቻልና በሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱ ላይ እያንዣበበ ያለውን አደጋ ማስቀረት የሚያስችል ሃሳብ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡

የሕገ መንግስት ጊዜያችን
በሕገ መንግሰቱ ዙሪያ የተነሳው ክርክርና ተከትሎ የመጣው የሕገ መንግስቱ አተረጓጎም ሂደት የሳበው ሕብረተሳባዊ ትኩረትና የተፈጠረው ተነሳሽነት አግባብነት የሌለው አይደለም፡፡ እንዳውም ኢትዮጵያ ታሪካዊ በሆነ የሕገ መንግስት ጊዜ ላይ መሆኗን ሕብረተሰቡ እንደተገነዘበ የሚያሳይ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ወቅቱ የሚፈልገውን ልዩ ኃላፊነት የመሸከም ግዴታ የተጣለባቸው አካላት የክስተቱ ግዙፍነት ሊጠፋቸው አይገባም፡፡ የሚጠበቅባቸውን ሳያሳኩ እንደማይቀሩ ተሰፋ እናደርጋለን፡፡

የግርጌ ማስታወሻ
[1]የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚበተንበት ሌላው አጋጣሚው የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረቶች ሲፈርሱ ነው፡፡ ይህ ግን አሁን ላለው ጉዳይ ጠቃሚ አይደለም፡
[2]የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ለማጠናከርና ሥልጣንና ተግባሩን ለመዘርዘር የወጣ አዋጅ ቁጥር 251/1993
[3]የሕገ መንግስት ጉባኤ ቃለ ጉባኤ ቁ. 28 ሕዳር 21 1987 ዓ.ም
[4]አንቀፅ 3(2)(ሐ) አዋጅ 798/2005

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.