ትኩስ ዜና፦ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን ከአምስት ወራት እስር በኋላ በ30 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር ተፈታ

ጋዜጠኛ ደሳለኝ ከፌደራል ማረሚያ ቤት ሲወጣ። ፎቶ፡ ታሪኩ ደሳለኝ

አዲስ አበባ ፤ ህዳር 7፤ 2015– ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከአምስት ወራት እስር በኋላ ዛሬ ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ተፈታ፡፡ ጋዜጠኛ ተመስገን በ30 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈታ የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረሽብርና ህገመንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ብይን የሰጠ ቢሆንም የቂሊጦ እስር ቤት ትእዛዙን በመተላለፍ ሊለቀው ፍቃደኛ አለመሆኑን ቤተሰቦቹ ተናገረው ነበር፡፡

ወንድሙ ታሪኩ ደሳለኝ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገረው ፍርድ ቤቱ ትላንት በዋለው ችሎት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከዚህ በፊት ቀርበውበት ከነበሩት ሶስት ተደራራቢ ክሶች ሁለቱ በመነሳታቸው የቀረውን አንድ ክስ ከእስር በዋስትና ተፈቶ እንዲከታተል ፍርድ ቤቱ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

ይህንኑ ተከትሎ አስፈላጊ የዋስትና ሂደቶች ቢከናወኑም የቂሊጦ እስር ቤት ከትላንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ከሰአት ድረስ እንዳለቀቀው ታሪኩ ተናግሯል፡፡

የጋዜጤኛው ጠበቃ አቶ ሄኖክ አክሊሉ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት ተመስገን ደሳለኝ ከዚህ በፊት ተፈቅዶለት በነበረው ዋስትና 100ሺ ብር አስይዞ የነበረ ሲሆን በትላንቱ ችሎት ደግሞ በ30ሺ ብር ተያዥ እንዲፈታ ተወስኖለታል፡፡

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ  “ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት፣ ህዝቡ በመከላከያ ሰራዊት ላይ እንዲሁም በመንግስት ላይ እምነት እንዲያጣ እና እንዲያምፅ በመቀስቀስ” ተጠርጥሯል በሚል በፖሊስ ግንቦት 18 ቀን 2014 ዓም በቁጥጥር ስር መዋሉ ይታወቃል።

ፌዴራል ዐቃቤ ህግ  በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ ሰኔ 22 ቀን 2014 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የህግ መንግስት እና የሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ሶስት ተደራራቢ የወንጀል ክሶች መመስረቱ ይታወቃል።

ጋዜጠኛው የአገር መከላከያ ሚስጥር በማውጣት፣ በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የሀሰት ወይንም የሚያደናግር መረጃ በማውጣት እና ወንጀል በማነሳሳትና በመገፋፋት ተሳትፎ አድርጓል የሚሉ ነበሩ።

ጥቅምት 11 ቀን 2015 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዓቃቢ ህግ በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ ካቀረበው ሶስት ተደራራቢ ክሶች ውስጥ ለሁለቱን ክሶች ያቀረበው ማስረጃ ወንጀሉን የሚያስረዳ ሆኖ ስላላገኘው ክሱ ውድቅ እንደረገውና 3ኛውን ክስ ብቻ እንዲከላከል ብይን መስጠቱ ይታወቃል፡፡ አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.