ዜና፦ህወሓትን አሸባሪ ብሎ የፈረጀው ህግ ድርድርን አይከለክልም፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በዛሬው እለት በፓርላማ አባላት ንግግር አድርገዋል። የምስል ክሬዲት፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት

አዲስ አበባ፡ህዳር 06/2015 ዓ/ም፦ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ  በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ በሰጡበት ወቅት ህወሓትን “አሸባሪ ድርጅት”  ብሎ የፈረጀው ህግ “ከአሸባሪ ድርጅት” ጋር መደራደርን የሚከለክል አይደለም ሲሉ ለፓርላማ አባላት ገልፀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የፌዴራል መንግስት የትግራይ ክልልን ከሚያስተዳድረው ህወሓት ጋር የሰላም ድርድር እንደሚጀምር ካወጀ በኋላ ከነበሩ ውዝግቦች አንዱን ለፓርላማ አባላት ሲያብራሩ “ያፀደቃችሁት ህግ ከአሸባሪዎች ጋር አትደራደሩ አይልም” ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

የሚኒስትሮች ም/ቤት “ህወሓት እና ኦነግ ሸኔን በአሸባሪነት የተፈረጁ ድርጅቶች” በማለት ውሳኔ ያሳለፈው ሚያዚያ 23፣ 2013 ዓ.ም ነበር፡፡

“እነዚህ አካላት የፈፀሙት ወንጀል የሽብር ተግባር ነው፡፡ የተፈፀሙት ተግባራት የሽብር ተግባራትን መከላከል እና መቆጣጠር አዋጅ ቁጥር 1176/2012 ዓ.ም አንቀፅ 3 የሽብርተኝነትን ትርጉም ሙሉ በሙሉ የሚያሟሉ መሆናቸውን በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ የእነዚህ ድርጅቶች አባላት እና ደጋፊዎችን በሽብር ተግባር በተናጠል ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ ድርጅቶቹን በህጉ መሰረት በአሸባሪት በመፈረጅ የሽብር ድርጊቶችን በተሸለ ሁኔታ ለመቆጣጠርና ለመከላከል የበለጠ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል” ሲል የሚኒስትሮች ም/ቤት አሳውቆ ነበር፡፡

በመቀጠልም ግንቦት 06 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት  በ6ኛ ዓመት 13ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ በሙሉ ድምፅ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያሳለፈውን የውሳኔ ሃሳብ በማጽደቅ “ህወሓት እና ሸኔን በአሸባሪነት ፈርጀውታል”። ህጉ  በ”አንድ ድምጽ” ተአቅቦ እና በአብላጫ  ድምፅ  ጸድቋል ሲል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገልጿል።

ይሁን እንጂ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያን የሁለት ዓመታት የእርስ በርስ ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የኢትዮጵያ መንግስት እነዚህን ስያሜዎች እንዲያነሳ ሲጠይቅ ቆይቷል። ባለፈው አመት ነሀሴ 26 በተደረገው የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በይፋ በሰጠው መግለጫ የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሀገራት በተለምዶ A-3+1 በመባል የሚታወቁት፤ መንግስትን ከሚቃወሙ ታጣቂ አካላት ጋር በቀጥታ ግንኙነት እና ድርድር ለማድረግ የኢትዮጵያ ፓርላማ የሽብርተኝነት ፍረጃዉን ማንሳት እንዳለበት ገልጧል፡፡

በሳለፍነው አመት የካቲት ወር ላይ ገዥው የብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያ ልታካሄድ ያቀደችው ብሄራዊ ውይይት “በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጁ” ቡድኖችን  እንደማይጨምር ገልጧል

ጠ/ሚ አብይ ዛሬ በሰጡት ምላሽ ህወሓትን “አሸባሪ ድርጅት” ብሎ የፈረጀው ህግ ከፓርቲው ጋር ትብብር ማድረግን የሚከለክል ሲሆን ይህም መሳሪያ ማስታጠቅ እና ድጋፍ መስጠትን የሚከለክል መሆኑን እና የፌደራል መንግስት በሁለቱም ጉዳዮች ላይ ያልተሳተፈ መሆኑን አስረድተው፤ ለዘላቂ ሰላም የሚደረገው ድርድር መጥፎ ባለመሆኑ ሊበረታታ ይገባል ሲሉ አክለዋል።

የግንቦት 1 የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ “ህወሓት እና ሸኔን በአሸባሪነት የተፈረጁበትን የሽብር ተግባራትን መከላከል እና መቆጣጠር አዋጅ ቁጥር 1176/2020 አንቀጽ 3ን መሰረት በማድረግ ህግ አውጪዎች ህጉን ተግባር ላይ ለማዋል መንገድ የከፈተላቸው ሲሆን ውሳኔው በአሸባሪነት ከተፈረጁት ድርጅቶች ሃሳብና ተግባር ጋር ለሚተባበሩ፣ ግንኙነት ላላቸው ወይም ተመሳሳይ ተግባር በሚፈጽሙ ሌሎች ድርጅቶችና ግለሰቦች ላይ ተፈጻሚ ይሆናል።

በአፍሪካ ህብረት መሪነት በፕሪቶሪያ በተካሄደው የሰላም ድርድር እና ቀጥሎም በፌዴራል መንግስት እና በትግራይ ክልል ተወካዮች መካከል የተፈረመው ዘላቂ ግጭት የማቆም ስምምነት መሰረት የፌደራል መንግስት “በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀውን የህወሓትን  ስያሜ እንዲነሳ ሁኔታዎችን ያመቻችታል” ይላል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.