አዲስ አበባ: ግንቦት 16፣ 2015 ዓ.ም – ሁዋዌ ከግንቦት 16 እስከ ግንቦት 20 ቀን 2015 ዓ.ም በቻይና ሼንዘን ከተማ በሚያካሂደው የሁዋዌ አይሲቲ ዓለም አቅፍ ውድድር የሚሳተፉት ተማሪዎች በትናንትናው እለት ቻይና የገቡ ሲሆን አሸኛኘትም ተደርጎላቸዋል።
ተማሪዎቹ (Huawei ICT Competition 2022-2023 Global Final) ዓለም አቅፍ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ያቀኑት የተለያዩ ሀገር አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ውድድሮች ላይ ተሳትፈው በየደረጃው በአሸናፊነት በማጠናቀቃቸው ነው። ከጉዟቸው በፊት የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ እና የምናብ አይሲቲ ሶሉሽንስ እና ሃሁ ጆብስ ዋና ስራ አስፈፃሚ እና መስራች ቃለአብ መዝገቡ በተገኙበት የማበረታቻ የሽኝት ስነ ስርዓት ተካሂዷል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ ዶ/ር ሳሙኤል ለወጣት ተማሪዎች ዓለም አቀፍ ልምድ ማግኘት አነቃቂና አበረታች መሆኑን ገልጸዋል። “ይህ እድል ያላችሁን ክህሎትና ተሰጥኦ የምታሳዩበትና ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተማሪዎች ጋር የምትገናኙበት ልዩ እድል ነው፡፡ እዚህ ደረጃ ለመድረስ ብዙ እንደጣራችሁና ከዚህም የተሻለ እንደምትሰሩ እምነቴ ነው፡፡” ብለዋል። አክለውም ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረክ ስለወከላችሁ ልትኮሩና በማሸነፍም የዚህ ታላቅ ህዝብ ኩራት እንደምትሆኑ አምናለሁ ብለዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዓለም በፍጥነት እያደጉ ካሉ ኢንዱስትሪዎች አንዱ እንደመሆኑ በዘርፉ የሰለጠኑ ብቂና በቁ ባለሙያዎች እንደሚሻ ገልጽው “ይህም ውድድር አቅማችሁን፣ ክህሎታችሁንና እውቀታችሁን የምታሳዩበት በመሆኑ በመተጋገዝና መደማምጥ በአሸናፊነት ልትወጡት ይገባል ብለዋል። በመጨረሻም ሁዋዌ ለተማሪዎቹ ለፈጠረው ዓለም አቅፍ እድልም በትምህርት ሚኒስቴር ስም አመስግነው ተማሪዎቹም በድል ሲመለሱ በጽ/ቤታቸው አቀባበል እንደሚያደርጉላቸው ቃል ገብተዋል።
አቶ ቃለአብ በበኩላቸው እድሉን በመፍጠሩ ሁዋዌን አመስግነው “ለትጋታቸው ፣ ጊዜያቸውና ሀብታቸውን ለውድድሩ ስላዋሉ እንዲሁም አለም አቀፋዊ ልምድ ተማሪዎቻችን እንዲያገኙ ስላደረጉልን አስተዋጽኦ አመሰግናለሁ።” ብለዋል፡፡ አክለውም “ በውድድሩ አለም አቀፉን የአይሲቲ ስነምህዳር ለመገንዘብና ለተተኪዎቻችሁ ምሳሌ ለመሆን ያግዛል።” ብለዋል፡፡ ወጣቱ ሥራ ፈጣሪ “በብዙ አገሮች እና ተማሪዎች መካከል የምታደርጉትን ውድድር እርስ በርሳችሁ በመረዳዳት ከአሸናፊዎች መካከል እንድትሆኑ እመኛለሁ ፣ እንደምታሽንፉም እምነት አለኝ ሲሉ ተማሪዎቹን አበረታትተዋል፡፡
እንደ ሚስተር ሊሚንግ ዬ የሁዋዌ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ፣ ሁዋዌ ይህንን የአይሲቲ ውድድር የጀመረው እንደነዚሀ ያሉ ጎበዝ ተማሪዎች ልምድ የሚቅስሙበት፣ ችሎታቸውን የሚያወጡበት፣ የሚያሳዩበትና የሚያዳበሩበት ለማድረግና ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እድል ለመክፈት ሲል ነው። ሊሚንግ ተማሪዎቹን የአይሲቲ ውድድሩን ካጠናቅቁ እና ከዩኒቨርሲቲ ከተመረቁ በኋላ “ከእኛ ጋር በመሆን ለዚህ ታላቅ ህዝብ የበለጠ አስተዋፅዖ እንደምታበረክቱ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።
ድርጅቱ በቀጣይም በኢትዮጵያ ትምህርት ላይ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ዘርግቶ የሚያደርገውን እገዛና ቁርጠኝነት እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል።
ዘጠኙ ተማሪዎች የተገኙት ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ ዋቸሞ፣ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች ነው። በውድድሩ ተማሪዎቹ እያንዳንዳቸው ሶስት አባላት ያላቸው ሶስት ቡድን ያላቸው ሲሆን በፕራክቲካል ትራክ (ዳታኮም፣ ሴኪዩሪቲ፣ WLAN፣ ቢግ ዳታ፣ ስቶሬጅ፣ AI፣ OpenEuler እና OpenGaussን ያካትታል) ሁለት ቡድን እና አንድ ቡድን በኢኖቬሽን ትራክ ይሳተፋሉ። በኢኖቬሽን ትራክ የሚወዳደሩት ተማሪዎች የራሳቸውን የፈጠራ ሃሳብ ይዘው የሚቀርቡ ሲሆን ተማሪዎቹ “የግእዝ ፊደላት ክላሲፋየር” የተሰኘ ውድድር ይዘው ቀርበዋል፡፡
የሁዋዌ አይሲቲ ወድድር ጥራት ያለው የአይሲቲ ታለንት እድገትን ለማፋጠን፣ ለኢንዱስትሪው ብቁ ተሰጥኦዎችን ለማዘጋጅትና መምረጥ፣ የመስኩ ባለተሰጥኦዎችን ወደፊት ለማቅረብና ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ንቁ ተሳታፊዎችን ለማበርከት፣ የመስኩ ፍላጎትና አቅርቦት በቂ እንዲሆን ለማበረታታትና በዘላቂነት አስተዋፅኦ ለማድረግ ይሰራል፡፡