ዜና፡ ምክር ቤቱ መንግስት በሸገር ከተማ እየተከናወነ ያለውን የመስጂድ ፈረሳ ተግባር በአስቸኳይ አቁሞ ያለውን ችግር በመክክር እንዲፈታና የፈረሱ መስጅዶች በአስቸኳይ እንዲተካ ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16/2015 ዓ.ም፡- በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደር እየተከናወን ያለውን የመስጂድ ፈረሳ በተመለከተ የኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ መንግስት የመስጂድ ፈረሳ ተግባር በአስቸኳይ አቁሞ ያለውን ችግር በመክክር እንዲፈታና የፈረሱ መስጅዶች በአስቸኳይ እንዲተካ ጠየቀ፡፡

የኦሮሚያ መጅሊስ ትላንት ግንቦት 14 2015 ባወጣው መግለጫ በየደረጃው ያሉ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ሃላፊዎችን በአካልና በደብዳቤ ማናገሩን ገልፆ ነገር ግን ለህዝበ ሙሲሊሙ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኞ ሆኖ አልተገኙም ሲል ገልጧል፡፡

የሸገር ከተማ የምስራቅ አፍሪካ ትልቋ ከተማ ሆና እንድትገኝ ለእኛ ትልቅ ደስታ ነው ያለው የመጅሊሱ መግለጫ በርካታ መስጂዶች አየፈረሱ በመሆኑ በበርካታ ሙስሊሞች መካከል ያለው አንድነት በመጥፋት፣ ህዝቡ በመንግስት ላይ ቅሬታ ከማቅረብ አልፎ በሃይማኖት እርስ በእርስ መጠራጠር ጀምሯል ሲል ገልጧል፡፡

“እንደሚታወቀው በአገሪቱ ምስጂድ በልመና እና ከህዝበ ሙስሊሙ ገንዘብ ይሰራል እንጂ በማስተር ፕላን የተገነባ በጣም ጠቂት ናቸው፡፡ በአገሪቱ ማስተር ፕላን ውስጥ ታቅፈው የተቀረፁ የሉም ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ህዝበ ሙስሊሙ ያለ መስጂድ አንድ ቀን ማደር አይችልም፤ በቀን ውስጥ አምስት ግዜ ወደ መስጂድ ይሄዳል፡፡ ስለዚህ ገንዘቡን አውጥቶ ገዝቶ በመገንባት የሚሰግድበትን መስጂድ መንግስት ህገ-ወጥ ነው በማለት ማፍረሱ ተቀባይነት የለውም” ሲል መግለጫው አትቷል፡፡

አክሎም “ይህ ተግባር፣ ህዝበ ሙስሊሙን እጅጉን አስቆጥጦታል፣ መንግስትና ህዝብን ወደ ማጋጨቱ እያመራ ነው፣ የአገሪቷን መልካም ስምም ያጠፋል፤ በአለም ደረጃም የመንግስትን ምስል ያጠለሻል” ሲል መግለጫው ገልጧል፡፡

በየትኛው የአገሪቱ ልማት ላይ በቻልነው አቅም ለመሳተፍ ዝግጁ ነን ያለው መጅሊሱ በሸገር ከተማ እየተከናወና ያለው ግንባታ ላይ መንግስት የኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤትንም ሆነ ህዝበ ሙስሊሙን ሳያማክር ወደ መስጂድ ፈረሳ መግባቱን ጠቁሞ ይህ በጭራሽ መሆን አልነበረበትም ብሏል፡፡

ተግባሩ ለሃይማኖት ያለውን ንቀት ያሳያል ያለው መግለጫው የሰላም ስጋት ስለሚያመጣ የመስጅድ ፈረሳን በማቆም ያለው ችግር በውይይት እንዲፈታ ጠይቋል፡፡ የፈረሱ መስጂዶችም በአስቸኳይ እንዲተኩ በህዝበ ሙስሊሙ ስም አጥብቀን እንጠይቃለን ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ግንቦት 10 2015 ለጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ በፃፈው ደብዳቤ ህገ-ወጥ በሚል መስጂዶች እየፈረሱ መሆናቸውን በመግለፅ መፍትሄ እንዲሰጡ ጠይቋል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሀጅ ኢብሪሒም በደብዳቤያቸው የመስጂድ ፈረሳ ጉዳይ በከተማ አስተዳደሩ «ሕገ ወጥ» ስለተባለ ብቻ በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ ሳይሆን የሕዝበ ሙስሊሙ የሃይማኖቱ ዋንኛ ሕልዉናዉ በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲቆም ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የጻፍነው ደብዳቤም እስካሁን ድረስ ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ገልፀዋል።

መስጂዶች እየፈረሱ በመሆኑ የጠቅላይ ምክር ቤቱ አመራርና ህዝበ ሙስሊሙን በእጅጉ ማሳዘኑን የገለፀው የምክር ቤቱ  ድብዳቤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመስጂዶች ፈረሳ ጉዳይ የማያዳግም መፍትሔ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.