አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2014 ጥር 30 ለየካቲት 1 አጥቢያ ሌሊት ከ7 ሰዓት ጀምሮ በላይ ጋይንት ወረዳ ነፋስ መውጫ ከተማ በሚገኙ የወረዳ ማረሚያ ቤት፣ ፖሊስ ጣቢያ እና ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ላይ ጥቃት መድረሱን የአማራ ክልላዊ መንግሥት አስታውቋል።
ጉዳዩን አስመልክቶ የክልሉ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን እና ፖሊስ ኮሚሽን በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫውም በፋኖ ስም የሚነግድ የተደራጀ ቡድን ድንገተኛ ተኩስ ከፍቶ የሕግ ታራሚዎችን ማስመለጡን እና ከፍተኛ ዝርፊያ መፈጸሙ ተመላክቷል። የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን መረጃው እንደደረሰው ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር የጸጥታ ኀይሎች ስምሪት በመስጠት ጉዳዩን እየተከታተለ መሆኑን የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ውቤ ወንዴ ተናግረዋል። የችግሩን መንስኤ እና ውጤት በማጣራት በአጥፊዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ፥ “ድርጊቱን የፈጸሙት ፋኖ ያልሆኑ ነገር ግን ፋኖ ነን የሚሉና በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ አካላት ናቸው” ብለዋል። እነዚህ አካላት ታራሚዎች እንዲያመልጡ ማድረጋቸውን እንዲሁም በፖሊስ ጣቢያ እና በሚሊሻ ጽሕፈት ቤት የነበረን ትጥቅ ዘርፈው መውሰዳቸውን አመላክተዋል። ኮሚሽኑ መረጃ እንደደረሰው ከዞኑ የጸጥታ አካላትና እና የፖለቲካ መሪዎች ጋር በመተባበር የኦፕሬሽን እና የወንጀል ምርመራ ቡድን በማሰማራት የተፈጸመውን ወንጀል የማጣራትና አጥፊዎችን የመቆጣጠር ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።
በዚህም ያመለጡ ታራሚዎችን መልሶ በሕግ ቁጥጥር ስር የማዋልና አጥፊዎችን ለሕግ የማቅረብ ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ ነው የተናገሩት። ከተዘረፈው የጦር መሳሪያ መካከል የተወሰነውን ማስመለስ እንደተቻለም አመላክተዋል። የኦፕሬሽን እና የወንጀል ምርመራ ቡድኖቹ ቀሪ ሥራዎችን በትኩረት እየሠሩ ነውም ብለዋል። በሂደቱ የዞኑ ሕዝብና የጸጥታ ኀይሉ ተቀናጅቶ አጥፊዎችን ለመቆጣጠር ርብርብ ማድረጉን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
በጥር ወር ውስጥ የብሄራዊ ደህንነት መረጃ አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ተመስገን ጥሩነህ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት (ብመደአ) የተሰሩ ጥናቶች መሰረት መደበኛ ባልሆኑ ኃይሎች ላይ አስፈላጊ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ተናግረዋል። የቀድሞው የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ፋኖ ብለው በቀጥታ ባይጠቅሱም፣ የሰጡት አስተያየት ከፋኖ መዋቅር ደጋፊዎች ተቃውሞ አሰምተው ነበር።
በእስክንድር ነጋ የሚመራው ባልደራስ የእውነተኛ ና ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ፋኖ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት አይደለም፣ ሕዝብን ያላማከለ ድርድርም አገርን አይጠቅምም ሲሉ ፋኖ በጭንቅ ጊዜ አገርን ከወረራ እና ከብተና የሚታደግ፣ በሠላም ጊዜ በየሙያ ዘርፉ ተሰማርቶ ሠላማዊ ኑሮውን የሚኖር ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ በዚህም መሠረት፣ ፋኖ፣ በጊዜያዊነት ተሰባስቦ በአገር ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ሙሉ በሙሉ እስከሚወገድ በዱር በገደሉ እየተሰማራ፣ አካባቢውንና አገሩን ከጥቃት የሚከላከል ህዝባዊ ኃይል እንጂ፣ቋሚ የሆነ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት አይደለም፡፡ ሲል በማህበራዊ ትስስር ገፁ ጥር 27 2014 መግለጫ ማውጣቱ የሚታወስ ነው:: አስ