ግንቦት 3፣ 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ፡- የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ወኪል አከፋፋዮችን ከገበያ ሥርዓት ውስጥ አስወጥተው ምርታቸው በቀጥታ እንዲሸጡ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አዘዘ፡፡ ሚኒስቴሩ ለአሥር የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ደብዳቤ የፃፈ ሲሆን ፋብሪካዎቹ ያስወጧቸውን የሲሚንቶ አከፋፋይ ወኪሎች ብዛትና ስም ዝርዝር በደብዳቤ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንዲልኩም አሳስቧል፡፡
ሐሙስ ሚያዝያ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተጻፈው ደብዳቤ፣ የጅምላ ንግድ ፈቃድ የያዙ ነጋዴዎች ሲሚንቶውን ለሌሎች ጅምላ ነጋዴዎች እየሸጡ ስለመሆናቸው መታወቁን ያስረዳል፡፡ ደብደቤው አክሎም ጅምላ ከጅምላ የሚደረግን የጎንዮሽ ንግድ የሚከለክለውን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 980/2008 እንደሚጥስ ገልጿል፡፡ በዚህም ምክኒያት ፋብሪካዎቹ ደብዳቤው ከደረሳቸው ቀን ጀምሮ የሲሚንቶ ወኪል አከፋፋዮችን አስወጥተው ለሚኒስቴሩ እንዲያሳውቁ ታዘዋል፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ደኤታ አቶ ሐሰን ለሪፖርተር እንደገለፁት፣ ሚኒስቴሩ ሲሚንቶ ላይ ያለውን የግብይት ሰንሰለት ለማሳጠር እየሠራ መሆኑን ገልጸው የግብይት ሰንሰለቱን ከሚያራዝሙት አካላት ውስጥ አንደኛው ወኪሎች መሆናቸውንና በሕግም እንደማይደገፉ አስታውቀዋል፡፡ አክለውም ከአሁን በኋላ ሲሚንቶን ለማከፋፈል ወኪሎችን የሚጠቀም የሲሚንቶ ፋብሪካ ከተገኘ ጥብቅ የሆነ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ነው የገለፁት፡፡
ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ፋብሪካዎች ምርቶቻቸውን ወደሚፈልጉት አካባቢ የሚያሠራጩላቸውን ወኪሎች የሚመርጡ ሲሆን ጅምላ ነጋዴች ግን የሲሚንቶ ምርቶችን ቀጥታ ከፋብሪካዎቹ አይገዙም ነበር፡፡ ይሁንና ወኪልቹ ከፋብሪካዎቹ የሚረከቡትን ሲሚንቶ ዋጋ ጨምረው ለጅምላ አከፋፋዮች ስለሚሸጡ ሰንሰለቱን ከማርዘሙ በላይ ከፋብሪካ የሚወጣው ሲሚንቶ ተጠቃሚው ጋር እስኪደርስ በሦስት ደረጃ የዋጋ ጭማሪ እንዲደረግበት ምክንያት ሆኗል፡፡
በዚህም ምክንያት ከአሁን በኋላ የሲሚንቶ ግብይቱ በቀጥታ የጅምላ ነጋዴዎች ከፋብሪካዎች እንደሚረከቡ አቶ ሐሰን የገለፁ ሲሆን የመንግሥት የልማት ድርጅቶችና ሌሎች የመንግሥት ግንባታ ፕሮጀክቶች ደግሞ በተለየ መልኩ እንደሚታዩ ማሳወቃቸውን ሪፖርተር ዘግቧል፡፡ አስ