አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18/ 2015 ዓ.ም – ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 የጉራጌ ዞን ዋና ከተማ ወልቂጤ ከጠዋት ጀምሮ ለተወሰኑ ሰአታት ጭር ብላ አሳልፋለች። ይህም የሆነው የጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ከተማዋ በመምጣታቸው ምክንያት መልዕክት ለማስተላለፍ ያለመ ነው ሲል የወልቂጤ ነዋሪው አቡበከር ከማል ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጿል። በወልቂጤ ከተማ ከቤት ያለመውጣት አድማ መደረጉን የጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ (ጎጎት) ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ጀሚል ሰኒ ለአዲስ ስታንዳርድ አረጋግጠዋል። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ጠ/ሚኒስትሩ ወደ ከተማዋ መምጣታቸውን ተከትሎ ህዝቡ ወደ መሰብሰቢያ አዳራሹ ገብቶ ጥያቄዎች እንዳይጠይቅ በመከልከሉ እና በመታፈኑ እንደዚህ ከሆነማ እኔም ጥያቄየን የማቀርብበት መንገድ አለኝ ብሎ እቤት በመቀመጥ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማቅረብ ነው ሲሉ የጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ (ጎጎት) ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ጀሚል ሰኒ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል። ይህም ጥያቄው የግለሰቦች ወይንም የቡድኖች ሳይሆን ህዝባዊ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
ጠ/ሚኒስትሩ በወልቂጤ ተገኝተው የነገሩን አዲስ ነገር የለም ያሉት አቶ ጀሚል በተለያዩ መድረኮች የክልል እና የዞን አመራሮች ክልልነቱን የከለከሉት ጠ/ሚኒስትሩ ናቸው እኛ አይደለንም ይሉን የነበረውን አረጋግጠውልናል ብለዋል። የጠ/ሚኒስትሩ አጠቃላይ መልዕክት ጭብጥ ህገመንግስቱን ለመተግበር ዝግጁ አይደለንም የሚል ነው ሲሉ ያብራሩት ጀሚል ሳኒ በመድረኩ ላይ ስለ ትግስት እና ሰላማዊነት ሲሰብኩት ነበር፤ ነገር ግን የጉራጌን ማህበረሰብ ስለትግስት እና ስለሰላማዊ ትግል የምትነግረው ህዝብ አይደለም ሲሉ ተችተዋል። ይህንንም ሲያብራሩ የጉራጌ ማህበረሰብ የክልልነት አደረጃጀት ህዳረ 17 ቀን 2011 ዓ.ም ህገመንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት ነበር የጠየቀው፤ በአመት ውስጥ የክልል ምክር ቤት ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት፣ ፌደሬሽን ምክር ቤት ወደ ምርጫ ቦርድ መምራት ነበረበት። ነገር ግን ከ2011 ጅመሮ ሀገር በተለያዩ ጉዳዮች ስትወጠር ታግሶ አሳልፏል። ለአራት አመታት መጠበቁን አስታውቀዋል።
ላለፉት ሁለት አመታት ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መልኩማህበረሰቡ ተቃውሞ ሲያሰማ ነበር ሲል ለአዲስ ስታንዳርድ አስተያየቱን የሰጠ የወልቂጤ ነዋሪው አቡበከር ከማል አጠቃላይ ሁኔታውን ሲያብራራ የዞኑ ምክር ቤት በ2011 ዓ.ም ጉራጌ ክልል እንዲሆን በሙሉ ድምጽ ወስኗል፤ በውል የጸደቀው የምክር ቤቱ አቋም ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት ተልኳል፤ ስለሆነም መንግስት ያንን አቋም እውቅና ሰጥቶ ወደ አፈጻጸም እና ወደ አተገባበር ከመግባት ይልቅ የዝሆን ጆሮ ስጠኝ ብሎ ዝም ነው ያለው፤ መንግስት ክላስተር የሚል ማህበረሰቡ ያልተቀበለው፣ ያላመነበትን አዲስ አከላለል ይዞ መጣ። እንደገና ምክር ቤቱ ይህንን አከላለል በአብላጫ ድምጽ ውድቅ ነው ያደረገው፤ ለምን ክላስተሩን ተቃወማችሁ በሚል በማህበረሰቡ ላይ የሚደርሰው ጫናና ግፍ ተዘርዝሮ አያውቀም ብሏል።
ጠ/ሚኒስትር አብይ በወልቂጤ በነበረው ስብሰባ ከዞኑ የተወከሉ ማህበረሰብ ክፍሎች ለተነሱላቸው ጥያቄ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በደቡብ ክልል መገናኛ ብዙሃን በተላለፈው የጠ/ሚኒስትሩ ምላሽ ክልል የመሆኑን ጉዳይ እኔ የምመልሰደው አይደለም፤ ነገር ግን እንደግለሰብ አሁን የተካተታችሁበት ክላስተር ይጠቅማችኋል የሚል እምነት አለኝ፤ ሰከን ብለን ተወያይተን ሁላችንን የሚያስማማ ነገር ለማምጣት መጣር ይሻላል፤ አሁን ብዙም የሚያስቸኩል አይመስለኝም ሲሉ ተደምጠዋል። ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በማህበራዊ ሚዲያ የፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት የጉራጌ ሕዝብ የሚነሡ ችግሮችን ገንቢ በሆነ ተሳትፎና ውይይት የሚፈታ ሰላም ወዳድ ሕዝብ ነው ሲሉ ገልጸው ዛሬ ባደረግናቸው ውይይቶች ያነሧቸውን ሥጋቶች እና ተስፋዎች በመስማቴ ደስተኛ ነኝ፤ በየደረጃው ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮችን ለመፍታት እንሠራለን ብለዋል።
አብዘሃኛው ማህበረሰብ ያመመው እንደ ህዳር አህያ ማንም አይጫናችሁ ማለታቸው ነው ያሉን በቅርቡ የተቋቋመው ጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ (ጎጎት) ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ጀሚል ሰኒ ማህበረሰቡ የራሱ ጥያቄ እንደሌለው፣ የራሱ ፍላጎት እንደሌለው የተገለጸበት መንገድ ማህበረሰቡንም መናቅ ነው፤ የክልል አደረጃጀቱ ጥያቄ ማህበረሰቡ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ሲጠይቀው የነበረ ጥያቄው ህዝባዊ ነው ብለዋል።
በጠ/ሚኒስትሩ ጽ/ቤት የክልልነት አደረጃጀት ጋር በተያያዘ በነበረው የሐሙሱ ስብሰባ ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ እኔ ባምንበት በአምስ ደቂቃ የሚያልቅ ጉዳይ ነው፤ ነገር ግን ለጉራጌ ማህበረሰብ የሚበጅ/የሚጠቅም አይደለም ብለው ነበር ሲሉ ያወሱት ጀሚል ሳኒ በወልቂጤው ስብሰባ ላይ ግን ይህንን አርመው የክልልነት ጥያቄው በህግ እና በህግነት አግባብ ነው የሚመለሰው ሲሉ መደመጣቸውን አስታውቀዋል።
የወልቂጤ ነዋሪዎች ብዙ ቅሬታ ያሉባቸው በመሆናቸው ጠ/ሚኒስትሩን በሚገባ አቀባበል አላደረጉላቸውም ያሉን የወልቅጤ ነዋሪ የሆነው አቡበከር ከማል ባለፉት ሁለት አመታት ይህ ሁሉ በደል ሲደርስብን ጠ/ሚኒስትሩ የት ነበሩ ሲሉ ቅሬታውን ገልጾ ጠ/ሚኒስትሩ በሄዱበት ሁሉ ስብሰባ አድርገው ሲመለሱ ተግባር ላይ የዋለ ያየነው ነገር ባለመኖሩ የኛ እምነት የማህበረሰቡ ጥያቄ መፈጸም ያለበት በአሰራር እና በህገመንግስቱ መሰረት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው በሚል ነው ጠ/ሚኒስትሩን በሚገባ አቀባበል ያላደረግንላቸው ብሎናል።
በማህበራዊ ሚዲያው ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ፣ ጉራጌ ህዝብ ማህበረሰብ አንቂዎች በተለይም መንግስት የሚተቹ፣ ሙሁራን እንዳይሳተፉ በማድረግ የመንግስት ደጋፊ የሆኑትን በመመረጥ እንዲሳተፉ ተደርጓል ያሉን ነዋሪው ጠ/ሚኒስትሩ ክላስተር ነው የሚያዋጣችሁ የሚሉት ለምንድን ነው ማህበረሰቡ ነው የሚያዋጣው የሚፈልገውን የሚያውቀው፤ ለምን በሃይል ሊጭኑበት ይፈልጋሉ ሲል ተችቷል።
በቅርቡ የክልልነት ጉዳዩን ሲያቀነቅኑ የነበሩ ግለሰቦች እና አመራሮች ለእስረ መደረጋቸው ተዘግቧል። ለእስር ከተዳረጉት መካከል የክላስተር አደረጃጀትን ውድቅ በማድረጋቸው ከሃፊነት እንዲነሱ የተደረጉት የጉራጌ ዞን የምክር ቤት ቋሚ ሰብሳቢ የነበሩት ወ/ሮ ጠጄ ደመቀ እንደሚገኙበት በአዲስ ስታንዳርድ በወቅቱ ተዘግቧል። የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ የውሃ አገልግሎቶች ለረዥም ጊዜ መቋረጡን ተከትሎ በተነሣ ተቃውሞ የመንግሥት የጸጥታ ኃይል በወሰደው እርምጃ የዜጎችን ሕይወት መንጠቁ፣ የአካል ጉዳትም ማድረሱ ይታወሳል።