ዜና፡ በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ በፀጥታ ሃይሎች ለተገደሉ እና ለተጎዱት ዜጎች መንግሥት ካሣ እንዲሰጥ ኢዜማ ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13/ 2015 ዓ›ም፡- በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ከወጀባር፣ቃጤሳ እና ሬቦ የሚቀርቡ የውሃ አገልግሎቶች ለረዥም ጊዜ መቋረጡን ተከትሎ በተነሣ ተቃውሞ የመንግሥት የጸጥታ ኃይል በወሰደው እርምጃ ለተገደሉ እና ለተጎዱት ዜጎች መንግሥት ካሣ እንዲሰጥ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ጠየቀ፡፡

የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ የውሃ አገልግሎቶች ለረዥም ጊዜ መቋረጡን ተከትሎ በተነሣ ተቃውሞ የመንግሥት የጸጥታ ኃይል በወሰደው እርምጃ የዜጎችን ሕይወት ነጥቋል፤ የአካል ጉዳትም አድርሷል።

ይህን ተከትሎ በትላንትናው ዕለት መግለጫ ያወጣው ኢዜማ ለተገደሉ እና ለተጎዱት ዜጎች መንግሥት ካሣ እንዲሰጥ እንዲሁም የፀጥታ ኃይሎች ሕዝብን መጠበቅ እንጂ ሰላማዊ ሰልፈኞችን በአደባባይ መግደል በአፋጣኝ እንዲያቆሙ እና የዜጎችን ሕይወት የነጠቁ የፀጥታ ኃይሎች በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ጠይቋል፡፡

በተጨማሪም የማኅበረሰቡን የውሃ አቅርቦት ጥያቄ ጊዜያዊ አማራጮችን እና ለዘለቄታው መፍትሔ የሚሆኑ መንገዶችን ምክንያታዊ በሆነ ጊዜ ውስጥ ምላሽ እንዲሰጥ ሲል አክሏል፡፡

“የዜጎች የመሠረተ ልማት ጥያቄያቸው አለመመለሱ ሳያንስ ቅሬታቸውን ሲገልጹ የጥይት እራት መኾናቸው የመንግሥት የአመራር ውድቀት ማሳያ እና የአምባገነንነት መገለጫ መኾኑን መንግስት ሊያውቀው ይገባል” ያለው ድርጅቱ መንግስት በሰላማዊ መንገድ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በአግባቡ በመመለስ ተጨማሪ የጸጥታ ስጋቶችን ሊያስወግድ ይገባል ሲል አሳስቧል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሁለት ቀናት በፊት የፋ ባደረገው መግለጫው መሠረት 3 ሰዎች ጭንቅላታቸውና ደረታቸው ላይ በጥይት ተመተው የተገደሉ መሆኑን ገልጦ ቢያንስ በ30 ሰዎች ላይ የተለያየ መጠን ያለው የአካል ጉዳት መድረሱን ገልጧል፡፡

የኢሰመኮ የዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “የክልሉ መንግሥት አስቸኳይ ማጣራት አድርጎ በአጥፊዎች ላይ ተጠያቂነት ሊረጋገጥ እና የተጎዱ ሰዎችም ተገቢውን ካሳ ሊያገኙ ይገባል” ብለዋል፡፡

አክለውም የተወሰደው የኃይል እርምጃ ከነገሩ ሁኔታ አንጻር ሲታይ ተመጣጣኝ ያልሆነ መሆኑን የገለፁት ዋና ኮሚሽነሩ ለወደፊቱም ተመሳሳይ ዓይነት የመብት ጥሰቶች እንዳይፈጸሙ ለጸጥታ ኃይሎች ግልጽ አመራር እንዲተላለፍ ያስፈልጋል በማለት አሳስበዋል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.