ዜና: የአማራ ድምፅ ሚዲያ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌትነት አሻግሬ መታሰሩ ተገለጸ

photo from social media

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18/ 2015 ዓ.ም – የአማራ ድምፅ ሚዲያ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌትነት አሻግሬ ትላንት መጋቢት 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ከቤቱ በጸጥታ ሀይሎች ተይዞ መወሰዱን ቤተሰቦቹና የስራ ባልደረቦቹ ገለጹ፡፡

የጌትነት አሻግሬ እህት እመቤት ታደሰ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩ ትላንት አመሻሽላይ ወደ ቤቱ በመመለስ ላይ እንዳለ  የጸጥታ ሀይሎች ለምርመራ ትፈለጋለህ በሚል እንደወሰዱት ገልጸዋል፡፡

እመቤት አያይዛም በቤት ውስጥ የነበሩ የስራ ቁሳቁሶችንም ጭነው እንደወሰዱበት ገልጻለች።

በዛሬው እለት ወደ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ በመሄድ ከወንድሟ ጋር በአካል መገናኘቷን ያስታወቀችው እመቤት ምርመራ እያደረጉበት መሆኑን እንደነገራት ተናግራለች።

በተመሳሳይ መልኩ የስራ ባለደረባው የሆነው ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይም  ጋዜጠኛው በጸጥታ ሀይሎች ተይዞ መታሰሩንና በርካታ የሚዲያው መገልገያ መሳሪያዎችም  ለምርመራ በሚል እንደተወሰዱ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጿል።

 ከቅርብ ግዜያት ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ የኦንላይን ሚዲያ ተቋማት መገልገያዎች በተለይም ካሜራ እና ላፕቶፖች ለስርቆት እየተዳረጉ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ወደ ቤቱ እንዲወስዳቸው እና በስራ ቀናት ይዟቸው እንዲመጣ ይደረግ ስለነበር በትላንትናው እለትም በቤቱ የነበሩ እቃዎች ለምርመራ በሚል እንደተወሰዱ ጋዜጠኛ ጎበዜ ተናሯል።

በወለጋ በሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች መፈናቀል እና በአዲስ አበባ ዙሪያ እየተፈጸመ ያለው ቤቶችን የማፍረስ እንቅስቃሴ ዘገባዎችን ይሰራ እንደነበር የገለጸው ባልደረባው ጎበዜ ሲሳይ እስካሁን ድረስ ለእስር የዳረገው ምን እንደሆነ እንዳልተነገረው እና ለምርመራ ትፈለጋለህ በሚል ምክንያት ብቻ እንደተወሰደ አስታውቋል፡፡

ጎበዜ አያይዞም ግትነት ለእስር ሊዳርገው የሚችል ምንም ዓይነት ነገር እንደሌለ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግሯል።

የአማራ ድምፅ ሚዲያ በብሮድካስት ፍቃድ ሲሰጠው ዋና አዘጋጅ ተብሎ የተመዘገበው ጋዜጠኛ ጌትነት አሻግሬ መሆኑን የገለጸልን ባልደረባው ጎበዜ የኛ የተሰኛ ሳትላይ ቴሌቮዥን ላይ መስራቱንም ጠቁሟል።

ቀደም ሲልም የኢትዮ ሰላም የዩቱዩብ ቻናል መስራች ጋዜጠኛ እና የፖለቲካ ተንታኝ ቴዎድሮስ አስፋው እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የመገናኛ ብዙኃን ሥርጭት አገልግሎት ጋዜጠኛ ዲያቆን ዮሴፍ ከተማ የካቲት 7 ቀን 2015 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሲኖዶስ መከፋፈል ጋር ተያይዞ ታስረው እንደነበር በዋሰው መለቀቃቸው  ይታወቃል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ኮሚቴ (CPJ) የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የጉራጌ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋዜጠኛ በየነ ወልዴን በአስቸኳይ እንዲፈታ እና የፕሬስ አባላት በስራቸው ምክንያት እንዳይታሰሩ ማድረግ እንዳለባቸው አስታወቆ ነበር።

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.