አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 15/2014 – በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚመራው የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ከፍተኛ የመከላከያ ሰራዊት፣ የፖሊስ እና የመረጃ ባለስልጣናት እንዲሁም የክልል ፕሬዝዳንቶች እና ሌሎችንም ጨምሮ በሀገሪቱ ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ ላይ ተወያይቷል። ምክር ቤቱ፣ በህገ ወጥ መንገድ ታጥቀው የሀገሪቱን ሰላምና ፀጥታ በማደፍረስ ላይ በተሰማሩ እና የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችን እርስበርስ በማጋጨት ላይ በሚገኙ “ቡድኖች እና ግለሰቦች” እንዲሁም የሀሰት መረጃዎችን በማሰራጨት የሀገሪቱን ሰላም በሚያሳጡ አካላት ላይ እርምጃ መውሰድ እንደሚጀምር አስታውቋል።
ምክር ቤቱ ለታሪካዊ ጠላቶቻችን በተላላኪነት የሚያገለግሉ ቡድኖችን፣ የትራንስፖርትና የህዝብን የመዘዋወር ነፃነት እና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በማወክ፣ በመሬት ወረራ፣ በስርቆት፣ በማጭበርበርና በህገ ወጥ ንግድ ላይ በተሰማሩ አካላት እንዲሁም የምግብና ልዩ ልዩ ሸቀጦች ዋጋ እንዲንር የሸቀጦችን ዋጋ ለመጨመር ሸቀጦችን የማከማቸት ድርጊት ላይ የተሰማሩ፣ ነዳጅና ሌሎች ምርቶችን ከአገር ወደ ጎረቤት አገሮች የሚያሾልኩ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድም ምክር ቤቱ አስታውቋል።
የደህንነት ምክር ቤቱ መግለጫ የወጣው በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይም በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ወታደራዊ ግጭት እየተባባሰ በመጣበት፣ በሁለቱ ክልሎች ላይ እየደረሰ ላለው የጸጥታ ችግርን ተከትሎ በሁለቱ ክልሎች መንግስታት መካከል የቃላት ጦርነት እየጨመረ በመጣበት ወቅት ነው።
ምክር ቤቱ የኢትዮጵያን “ጠላቶች” በሦስት ከፍሎአቸዋል። በዚህም መሰረት የመጀመሪያዎቹ “ምንጊዜም የማይተኙት ታሪካዊ ጠላቶቻችን ናቸው። እነዚህ ጠላቶቻችን ጠላትነታቸውን የሚያቆሙት ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር ከምድር ገጽ ስትጠፋ ብቻ ነው። ይኼ ምኞታቸው እንዲሳካ ብቻቸውን አይሠሩም ይልቁንም “መልእክተኞች” አላቸው የሚለው ምክር ቤቱ እነዚህ መልእክተኞች “ሁለተኛ ጠላቶች ናቸው” ብሏል፡፡ ለገንዘብና ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ወገናቸውን እንደ ይሁዳ የሚሸጡ፣ ሀገር የጣለባቸውን እምነት በሽርፍራፊ ሳንቲም የሚለውጡ ሀገር አልባ ባይተዋሮች ናቸው” ይላል መግለጫው ።
ምክር ቤቱ ማንንም የቡድን ወይም ግለሰቦችን በስም ባይጠቅስም “የተናገሩትን ሆነው የማይገኙ፣ ቀን ቀን በአደባባይ ስለ ሕዝብ ፍቅር እና ስለ ሀገር አንድነት የሚደሰኩሩ፤ ማታ ማታ ከጠላት ጋር እያሴሩ ወገንን የሚክዱና ሀገር ለማፍረስ ጉድጓድ የሚቆፍሩ ናቸው” ብሏል።
ሶስተኛው ምድብ የኢትዮጵያ ጠላትን ሳያውቁት ከላይ ከተጠቀሱት ሁለቱ ምድቦች ጋር ተባባሪ የሚሆኑ ናቸው ያለው ምክር ቤቱ ግድየለሾች ስለሆኑ የሚያደርጉት ነገር የሚያስከትለውን ውጤት ሳይገነዘቡ በዘፈቀደ የጠላትን ተልዕኮ የሚፈጽሙ ውል አልባ ኢትዮጵያውያን ናቸው ብሏል። ይህ ቡድን አንድን ነገር ተቀብለው ማውራታቸውን፤ ወይም አድርጉ የተባሉትን ነገር ማድረጋቸውን፤ ወይም ሳይመረምሩ የሰጧቸውን መረጃ ሁሉ ማስተላለፋቸውን እንጂ በሀገራቸውና በሕዝባቸው ላይ የሚያስከትለውን መዘዝ አይመረምሩትም። ከመረመሩም ጉዳቱ ከደረሰ በኋላ ብቻ የሚፀፀቱ ናቸው ሲል ገልጧቸዋል።
“ኢትዮጵያ የበለጠ የተፈተነችው በእነዚህ በሁለቱ ነው። ታሪካዊ ጠላቶቻችን የታወቁ ጠላቶቻችን ናቸው። የማናውቀው እና መርህ አልባ ኢትዮጵያውያን ግን ለእነሱ ትኩረት ሳንሰጥ ብዙ ጊዜ ዋጋ ያስከፍለናል። እስከመቼ እንደዚህ ይሆናል? ሁላችንም ቆም ብለን ይህንን ጥያቄ መመለስ አለብን”ሲል መግለጫው ያትታል።
ምክር ቤቱ እነዚህን አካላት “ለውጡን ለመከልከል እና ኢትዮጵያ ጠንካራ አፍሪካዊ ሃይል እንዳትሆን የሚችላቸውን ሁሉ አድርገዋል” ብሎ ኢትዮጵያውያንን በጎሳ ለመከፋፈልና ለመግዛት፣ ኢኮኖሚውን ለማዳከምና ተቋማቱን ለማፍረስና ሀገር ተሸክመው የኖሩ ተቋሞቻችን እንዲፈራርሱ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል” ሲል ወቅሷል።
“መገናኛ ብዙኃን እና የታጠቁ ሃይሎችን በመጠቀም ማህበራዊ ህብረታችንን ለማጠፋት፣ የእምነት እና የማህበራዊ ተቋማትን ለማቃጠል፣ ህብረተሰቡን በማሸበር ሁሉንም አይነት እኩይ ተግባራት ፈጽመዋል። ምንም እንኳን የእነርሱ ግፍ አሰቃቂ እና ዜጎቻችንን የጎዳ ቢሆንም በኢትዮጵያውያን ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ለሀገራቸው ባላቸው የጸና ፍቅር ምክንያት ጠላቶቻችን የሚፈልጉትን ግብ ሊያሳኩ አልቻሉም ሲል ምክር ቤቱ ተናግሯል።
የህግ አስከባሪ ተቋማት እና የፍትህ አካላት ከለውጡ በፊት ስብራት ያጋጠማቸው ሁለቱ ዘርፎች መሆናቸውን የገለጸው ምክር ቤቱ ይህም የሆነው የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ነው ብሏል። አክሎም “በአገሪቱ ላይ ስልጣንና ሃብት የያዙት የታሪክ ጠላቶቻችን ተላላኪዎች የህግ አስከባሪውን እና የጸጥታ ተቋሙን በሞትና በሕይወት መካከል እንዲኖሩ አድርገዋቸው ነበር። ከለውጡ በኋላ በእነዚህ ተቋማት ላይ በተሰሩት ስራዎች የኢትዮጵያን ህልውና ለመታደግ ወደሚችሉበት ደረጃ ለማድረስ ተችሏል ብሏል።
ለተሻለ ነገ ለመዘጋጀት አስተዳደሩ “ብዙ ፈተናዎችን ተቋቁሟል” ሲል ምክር ቤቱ ተናግሮ አሁን ትዕግስቱ ማለቁን ተናግሯል። “አሁን የደህንነት እና መረጃ ተቋማቱ የተሻለ ደረጃ ላይ በመሆናቸው ወቅታዊ እና ተመጣጣኝ ምላሽ ከመስጠት ወደ ኋላ አንልም” ሲል አሳስቧል።
ሆኖም ምክር ቤቱ የሀገሪቱን የጸጥታ ችግሮች ለመፍታት የሚያደርገው ጥረት “የብዙ አካላት የተቀናጀ ጥረት እንደሚጠይቅ” በመግለጽ “ሁሉም ዜጋ፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ መገናኛ ብዙሃንና ሌሎች የህዝብ አይንና ጆሮ ሆነው የሚሰሩ ከደህንነት ኤጀንሲዎች ጋር በቅንጅት ለመስራት በሙሉ ልብ ቁርጠኞች መሆን አለባችሁ ሲል ጥሪ አቅርቧል።
“ህዝቡ ለሚያሸብሩንና ለሚያስጨንቁን ጠላቶቻች ምሽግ ከሆነ የጸጥታ ሃይሉ ጥረት ብቻውን ፍትሄ አይሆንም ” ሲል ምክር ቤቱ አስጠንቅቋል።አስ