ዜና ትንታኔ፡- የደራሼ ልዩ ወረዳ አስተዳዳሪን በታጣቂዎች መገደላቸው፣ ስምንት ህንዳውያን መታገታቸው ተሰማ

በብሩክ አለሙ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 26/2014-  በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የደራሼ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጆበርና አሰፋ በታጣቂዎች ተገደሉ። ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የዓይን እማኝ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት ቅዳሜ ሚያዚያ 22 ቀን ጠዋት ነው አስተዳዳሪው የተገደሉት። በአካባቢው የመንግስት ከፍተኛ አመራር ላይ ግድያ ሲፈጸም ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። በመጋቢት ወር በኮንሶ ዞን  በሰገን ወረዳ ዙሪያ የገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ገረሙ ገለቦ ከጓደኞቻቸው ጋር በአንድ ሆቴል ውስጥ ሲመገቡ በጥይት ተገድለዋል። የወረዳው ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጋዲሳ ካሮ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት ከአካባቢው ባለስልጣን ግድያ ጋር በተያያዘ አራት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

የደቡብ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ እና የመልካም አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ ግድያው መፈጸሙን ገልጸው ሚያዝያ 17 ቀን ስምንት ህንዳውያንን አፍነው የወሰዱት እነዚሁ “የጥፋት ሃይሎች” ጥቃት በመሰንዘር በጸጥታ አካላት  እና በሰላማዊ ሰዎች ላይ  ጉዳት አድርሰዋል ብለዋል። የክልሉን ሰላም ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት አንዳንድ የክልሉ ልዩ ሃይል አባላትም ተገድለዋል። ከሲቪሎችም ሆነ ከክልሉ ልዩ ሃይል የማቾቹን ቁጥር አለማየሁ ባይጠቅስም ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። በተጨማሪም ታፍነው ተወስደዋል የተባሉትን ስምንቱ የህንድ ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ ሳይገልጹ አልፈዋል፡፡ አዲስ አበባ የሚገኘው የህንድ ኤምባሲም ያወጥው ይፋዊ መግለጫ የለም።

አዲስ ስታንዳርድ በስልክ ያነጋገራቸው የዓይን እማኙ “በደራሼ ልዩ ወረዳ የሚገኘው የጊዶሌ ከተማ ከሚያዝያ 17 እስከ ሚያዚያ 22 ቀን ለአንድ ሳምንት ያህል በተኩስ ሲናወጥ ቆይቷል ብሏል። የዞን አስተዳደር የመመስረት ጥያቄ ከሚነሳባቸው ወረዳዎች አንዱ ደራሼ  ወረዳ ነው።

ስማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ ሁለተኛ የአይን እማኝ እንዳሉት በአካባቢው ሰላም እጦት የተለመደ ከሆነ ሰነባብቷል። ከሰሞኑ በጊዶሌ ከተማ ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ መሰማቱንና ነዋሪዎቹ በፍርሃት ውስጥ መሆናቸውንም አስረድተዋል። አክለውም “ወጣቶቹ የቀድሞ አመራሮችን ቤትም አቃጥለዋል። በአካባቢው የጸጥታ ሃይሎች አለመኖራቸውን ተከትሎ ህይወታችን አደጋ ላይ ወድቋል“ ብለዋል።

ሦስተኛው የአይን እማኝም በኮንሶ እና ደራሼ ልዩ ወረዳ ታጣቂዎች እና በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ልዩ  ሃይሎች መካከል የተኩስ ልውውጥ መደረጉን ገልጿል። ቅዳሜ የአካባቢው ሀገር ሽማግሌዎች እና ሀይማኖት አባቶች ጣልቃ በመግባት ሁከትና ብጥብጥ እንዲቆም መደረጉን ገልፆ  መደበኛው ፖሊስ አካልትም በፍርሀት ውስጥ መቆየታቸውን ተናግሯል።

እማኙ ለረዥም ጊዜ ቸልተኛ በመሆን የከተማውን ነዋሪዎች  ከስጋት ለመታደግ  የጸጥታ ሃይሎችን  ባለማሰማራቱ የክልሉ መንግስትን ወቅሰዋል፡፡

ሚያዚያ 23 ቀን የደቡብ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ወደ አካባቢው መሰማራታቸውን ገልጿል። የክልሉ መንግስት ወንጀለኞችን ለህግ እንደሚያቀርብ ገልጾ የአካባቢው ማህበረሰብ ወንጀለኞችን የማጋለጥ ስራውን እንዲያጠናክር ጠይቋል።

ይህ ግጭት የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ለመፍታትና የጋራ እቅድ ለማውጣት ሚያዚያ 15 ቀን ከኮንሶ ዞን እና ከሰገን ወረዳ የተውጣጡ የጸጥታ ሃይሎች እና አስተዳደሪዎች ውይይት ካደረጉ ከአንድ ሳምንት በኋላ  ነው።

አዲስ ስታንዳርድ ላለፉት በርካታ ሳምንታት በኮንሶ እና አካባቢው ስላለው የጸጥታ ችግር ሲዘግብ ቆይቷል። በሚያዝያ ወር አጋማሽ በዞኑ የተቀሰቀሰው የእርስ በርስ ግጭት ለአዲስ መፈናቀል ምክንያት ሆኗል። ከ10 ቀበሌዎች ወደ 19,000 የሚጠጉ ሴቶችና ልጃ ገረዶችን ጨምሮ 37,000 የሚደርሱ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል።

በሚያዝያ ወር መጀመሪያ ላይ በኮንሶ እና ደራሼ ማህበረሰቦች መካከል በተፈጠረ ግጭት በሰገን ዙሪያ ወረዳ ከ32,000 በላይ እና በካራት ዙሪያ ወረዳ ፉቹቻ ቀበሌ ከ3 ሺ ሰዎች በላይ ተፈናቅለዋል። በቦርቃራ፣ መታራጊዛባ ቀበሌዎች በተፈጠረው ሁከት ባለፉት ሳምንታት ብቻ ከ1,000 በላይ ሰዎችም ተፈናቅለዋል።

ባለፉት ሁለት አመታት በኮንሶ ዞን የዜጎችን ህይወት የቀጠፉ ግጭቶች ሲስተዋሉ ቆይተዋል። በአጎራባች ኮልሜ ክላስተር ቀበሌዎች የሰላም ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ጉዳታ ኩታኖ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት እነዚህ ግጭቶች የብዙ ንፁሃን ዜጎችን ሞትና መፈናቀልን አስከትሏል። አስ

የአርታዒ ማስታወሻ፡ ይህ ዜና የደራሼ ልዩ ወረዳ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት ስር እንጂ በኮንሶ ዞን ስር አለመሆኑን ለማሳየት ተስተካክሏል። ስለ ስህተቱ ይቅርታ ።

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.