ትንታኔ፡ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ደርሶብናል ያሉት የአስተዳደር በደል እስከ መስከረም ድረስ ካልተቀረፈ እርምጃ እንደሚወስዱ አስጠነቀቁፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ የትምህርት ሚኒስቴር ምኒስትር ምስል- የትምህርት ሚኒስቴር

በብሩክ አለሙ @Birukalemu21

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6/2014 ዓ.ም፡-የዩኒቨርሲቲ መምህራን የደመወዝ ጭማሪ፣ የደረጃ ዕድገት፣ የቤት አበል ፣ የመኖሪያ ቤት፣ በተጨማሪ ስራዎች የሚገኝ ገቢ ላይ የግብር ሁኔታ፣ ለመምህራን እና ለቤተሰቦቻቸው የህይወት ኢንሹራንስ መኖር ፣ የብድር አገልግሎት፣ እንዲሁም የመምህራን የዝውውር መብት የማይሻሻልና የማይጠበቅልን ከሆነ ለምንወስደው እርምጃና በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ ለሚፈጠረው መጉላላት መምህራኑ ሃላፊነት እንደማይወስዱና ተጠያቂ የሚሆነው የትምህርት ሚኒስቴር መሆኑን አስጠነቀቁ፡፡

በስሩ 40ሺ መምህራንን ያቀፈው የዩኒቨርሲቲ መምህራን ማህበር ሐምሌ 27 ቀን 2014 ዓ.ም.  ለትምህርት ሚኒስቴርና ለሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ተቋማት በፃፈው ደብዳቤ ከደሞዝና ከሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች አንጻር እየደረሰባቸው ያለውን አስተዳደራዊ በደሎች ይቀረፉላቸው ዘንድ የመብትና የፍትህ ጥያቄዎችን በቀጥታ ለሚመለከታቸው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና የመንግስት ተቋማት በተደጋጋሚ ማቅረቡን ገልፆ የሚመለከተው አካል እስከ መስከረም 1/ 2015 ዓ.ም ለጥያቄዎቹ መልስ የማይሰጥ ከሆነ መምህራኖቹ የራሳቸውን እርምጃ እንደሚወስዱ አስጠንቅቋል፡፡

ማህበሩ የፃፈው ደብዳቤ በአጭር ጊዜ እንዲመለሱ ከተያዙት ጥያቄዎች መካከል አንዱ የነበረውን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመምህራንን የደረጃ እድገት ተጨባጭ በሆነ መልኩ ለማሻሻል ጥቅምት 8/2014 ዓ.ም የሚመለከተው አካላት ሁሉ የተሳተፉብት ባለሶስት አማራጭ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መምህራን የስራ ደረጃ ማሻሻያ  /JEG/ ምክረ-ሀሳብ ለትምህርት ሚኒስቴር  የገባ መሆኑና ይሄንኑ መሰረት ተደርጎ የደረጃ ማስተካከያ ይደረጋል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም የጥናቱ አካል ያልነበረና በመምህራን የኑሮ ሁኔታ እና የስራ ተነሳሽነት ላይ ምንም አይነት መሠረታዊ ለውጥ የማያመጣ ውሳኔ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ለዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ እና ቴክኒካል ረዳቶች ተብሎ የተሰራ የስራ ደረጃ ማሻሻያ /JEG/ ተገቢ አለመሆኑን ያስረዳል፡፡

የዩኒቨርሲቲ መምህራን ማህበር ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በፃፉት ደብዳቤ የአስተዳደር በደሎች ያሏቸውን ቅሬታዎች በዝርዝር አስፍረዋል፡፡ የመጀመሪያው ለዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ እና ቴክኒካል ረዳቶች የተሰራውን አዲሱን የስራ ደረጃ ማሻሻያ /JEG/ በተመለከተ ከአጠቃላይ ትምህርት መምህራን አንጻር እንኳን ሲታይ ተገቢ ነው ተብሎ ሊታመን የማይችል መሆኑ እና ለፕሮፌሰር ማዕረግ ላላቸው መምራን ምንም አለመሻሻሉ እንዲሁም በሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም. ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የፌዴራል መንግስት ሰራተኞች የስራ መደቦች ምዘና የደረጃዎች ምደባና የወጣው የደመወዝ ስኬል ደንብ በዩኒቨርሲቲ መምህራን ላይ ተፈፃሚ ባለመደረጉ ቅሬታ ተሰምቶናል ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ መምህራኑ የመምህራን የቤት አበል በፍጥነት እሁን ያለውን የቤት ኪራይ ዋጋ ከግምት አስገብቶ ተሻሽሎ ተግባራዊ እንዲደረግልን፣ የተደረገው  የደረጃ ማሻሻያ ረጅም ጊዜ በዩንቨርሲቲ ያስተማሩ መምራንን ልምድ ያላገናዘበ መሆኑና በመምህራን መካከል በቀጣይ ፍትሀዊ የደመወዝ ልዩነት እንዲኖር ስለማያስችል የደረጃ ማሻሻየው የመምህራንን ልምድ እና ማዕረግ ያገናዘበ አንዲሆን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የረዳት ፕሮፌስር የአዳሚክ ማዕረግ ዝቅተኛ ተፊላጊ ችሎታ የሶስተኛ ዲግሪ መደረጉን በተመለከተም ተቋሞ አለን የሚሉት መምህራኑ ከዚህ በፊት በነበረው የአካዳሚክ ደረጃ እድገት መሰረት አንድ MA/MSc/M.Phil ያላቸው መምህራን ተገቢውን መስፈርት ካሟሉ  ወደ ረዳት ፕሮፌስርነት ደረጃ ያድጉ የነበር መሆኑን ጠቅሰው ይህ አሰራር መሰረዙ ዉሳኔውን ኢሳይንሳዊ (unscientific) ኢ-አመኗዊ (illogical) እና ምክንያት አልባ (unreasonable) ሆኖ አግኝተነዋል ብለዋል፡፡ ሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ ያሉ መምህራን በራሳቸው ጥረት ምርምር ሰርተው የኢኮኖሚ ጫናዉን ተቋቁመው ሊያውም በውጭ ምንዛሬ በመክፊል ምርምራቸውን በታዋቂ  ጁርናሎች አሳትመው የደረጃ እድግት እየጠቱ ባለበት እንዲሁም አንዳንዶች በተመሳሳይ ሂደት አልፈው የአልግሎት ጊዜያቸው እስኪሞላ እየጠበቁ ሳለ ይህንን ሳኔ መወሰን ተገቢ አለመሆኑንም አስረድተዋል፡፡

አክለውም የእድገት መስፈርቶቹ ያነሱ መስለው ከታዩ እነሱን ማሻሻል ተገቢ ሆኖ ሳለ ነገር ግን ሙሉ ለመሱ መሰረዝ የመምሀራንን መብት የሚፃረር በመሆኑ፣ አንዳንድ የትምህርት መስኮች በአገር ዉስጥ የሶስተኛ ዲግሪ ፕሮግራም እምብዛም የሌላቸው ሲሆን ወሳኔውም በነዚህ የትምህርት ዘርፎች ያሉ  መምህራን የወደፊት የአካዳሚክ ጉዞ የሚያመክን ስሰሆነ ይታሰብበት ሲል አስጠንቅቀዋል፡፡

የአካዳሚክ ቴክኒክ ረዳቶች ዝቅተኛው ተፈላጊ የትምህርት ደረጃ የመጀመሪያ ዲግሪ መሆኑ፣ ከዚህ በፊት በዲፕሎማ ደረጃ የነበሩ ቴክኒክ ረዳቶች የወደፊት እጣ ፋንታ በዝርዝር እንዲቀመጥልን እንፈልጋለን ያሉው የመምህራን ማህበሩ ተፈላጊው ደረጃ የመጀመሪያ ዲግሪ ከሆነ አሁን በዲፕሎማ ደረጃ ያሉትን ዩኒቨርሲቲዎች ሙሉ ደመወዝና ጥቅማቸውን በመክፈል የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲማሩም ጠይቀዋል፡፡

በመጨረሻም በአመዛኙ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ሁሉተኛ ዲግሪ ያላቸው መሆኑ እየታውቀ የተሻሻለው የቺፍ ቴክኒካል ረዳት II የትምህርት ደረጃ ሦስተኛ ዲግሪ (ፒ. ኤችዲ) የሚጠይቅ መሆኑ ነባራዊ ሁኔታን ያላገናዘበ እና ከእውነት የተፋታ ነው ብለዋል፡፡

ማህበሩ የትምህርት ሚኒስቴር ጥያቄዎቹን ተቀብሎ አግባብነት ያለው ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ በቀጣይ መብቶቹን ለማስከበር ስራ ማቆምን ጨምሮ  አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃዎችን እንደምንወስድ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። አክሎም ለሚፈጠረው የትኛውም የአሰራር መቃወስ፣ የትምህርት መርሀ-ግብር  መስተጓጎል፣ የተማሪዎች መንገላታት እና ቤተሰቦቻቸው ላይ ለሚደርስ ተጨማሪ ጫና ሀላፊነቱን በቃላቸው ያልተገኙትና የመምህሩን ህመምና ሸክም መረዳት የተሳናቸው የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንና የትምህርት ሚኒስቴር የሚወስዱ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ማህበር ማስጠንቀቂያ

መተመሳሳይ መልኩ የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ማህበር ሐምሌ 11 ቀን 2014 ዓ.ም ለ.ፌ.ዲ.ሪ. ጠ/ሚ/ር፣ ትምህርት ሚ/ር እና ሌሎቸች ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ተቋማት በላከው ደብዳቤ፤ የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር የተሻሻለ ጂኤጂ በሚል ለዩኒቨርሲቲ መምህራን ተደረገ የተባለው የደረጃ ማሻሻያ በሂደቱ በባለድርሻ አካላት መካከል የነበረውን መናበብ፣ መተባበርና የጋራ መግባባት የናደ እና መንግስት የምሁራን ችግር በአግባቡ ያልተረዳበት፣ መምህራን ላይ የሞራል የጉዳት ያስከተለ መሆኑን በመግለፅ የአሶሳ ዩንቨርሲቲ ምህራን ማህበር አባላት በፍፁም እንደማይቀበሉትና በአስቸኳይ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድበት አሳስቧል።

የማህበሩ ፕሬዘዳንት ለማረጋገጫ ደብዳቤውን ለአዲስ ስታንዳርድ የላኩ ሲሆን፤ ደብዳቤው የዩኒቨርሲቲ መምህራን አሁን ላይ የሚከፈላቸው ደምወዝ  እንኳን አሁንና ከ5 አመት በፊትም የነበረውን ኑሮ በአግባቡ ለምራት የሚያስችል አለመሆኑንና መምህሩ ሀገሪቱ ያሳለፈችውን አስከፊ ጊዜና መንግስትም የነበረበትን የሽግግር ወቅት ታሳቢ በማድረግ ከቀን ቀን እየከፋ የመጣውን የኑሮ ጫና በትዕግስት ተሸክሞ መቆየቱን ያስረዳል፡፡  ጨምሮም በተጠናቀቀው የ2014 በጀት አመት በባለድርሻ አካላት መካከል በነበሩ ተከታታይ ውይይቶችና በተደረገው የጂኤጅ ጥናት መሰረት አግባብነት ያለው የደምወዝ ማሻሻያ ይደረጋል የሚል የጋራ መግባባት ላይ ተደርሶ ነበር ቢሆንም ነገር ግን ትምህርት ሚኒስቴር ቃሉን ሳያከበር ያስተላለፈው ውሳኔ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምህራንን እጅጉን አስከፍቷል ሲል ደብዳቤው ያትታል፡፡

መምህሩ ኑሮውን ሊያሸንፍበት የሚችል የደረጃ  መሻሻያ ለማድረግ የሚያስችል በጀት ለመመደብ ዳተኝነትን ያሳየ መንግስት በተዘዋዋሪ በመምህሩ የአዕምሮ ነፃነትና ተነሳሽነት ማጣት፤ የተሻለ ክፍያ ፍለጋ ልምድ ያላቸው መምህራን ከስራ መልቀቅና በተያያዥ ምክንያቶች ሊፈጠር በሚችለው የትምህርት ጥራት መዳከምና ብቁ ያልሆኑ ተመራቂዎች ምክንያት በብዙ እጥፍ የገንዘብ ኪሳራና የምርታማነት ቀነስ መጋፈጡ እንደማይቀር ሊሰመርበት ይገባል ያለው ደብዳቤው መንግስት ለመምህራን ያለውን የተንሸዋረረ አመለካከት የማያስተካክል ከሆነና የተቋማቱ መምህራንን ለ5 እና 10 አመት በተመሳሳይ ደመወዝ ለማሰራት የታሰብ ከሆነ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከዩንቨርሲቲዎቻችን ሲንየር/ልምድ ያላቸው/ ምህራን የተሻለ ስራ ፍለጋ ወጥተው አልቀው ዩንቨርሲቲዎቻችን ለአዳዲስ ተመራቂዎች ልምድ ማግኚያ እና ወደ ሌላ ስራ መሸጋገሪያ ድልድይ ሆነው የሚያገለግሉ ደካማ ተቋማት መሆናቸው አይቀርም ሲል አሳስቧል።

የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ማህበሩ ትምህርት ሚኒስትርም ሆነ የሚመለከተው የመንግስት አካላት ጥያቂያችንን ተቀብለው አግባብነት ያለው ምላሽ ጊዜ ሳይወስድ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነ ለየትኛውም የአስራር መቃወስ፣ የትምህርት መርሀ-ግብር መስተጓጎል፣ የተማሪዎች መንገላታት እና ቤተሰቦቸው ላይ ለሚደርስ ተጨማሪ ጫና የዩኒቨርሲቲው መምህራን ሃላፊነቱን የማይወስድ መሆኑንም ገልጿል፡፡

የዩኒቨርሲቲ መምህራን ሃሳብ

የመጀመሪያ ዲግሪ በ”ሲቪል ኢንጂነሪንግ” እና ሁለተኛ ዲግሪ በ”ኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ እና ማኔጅመንት” ያላቸው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህር “የእኔ የተጣራ ደመወዝ የቤት አበል ጨምሮ 8576.90 ነው” ይላሉ፡፡ ይህም አነስተኛ የደመወዝ መጠን መሆኑን ገልፀው እንደማንኛውም የመንግስት ሰራተኛ ጥናት ከተደረገ በኋላ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ሊተገበር የነበረ ነገር ግን የዩኒቨርስቲ መምህራንና የአካደሚክ ሰራቸኞች ለብቻ ጥናት ይደረግበታል ተብሎ እስካሁን  ምንም ነገር ሳይደረግ መቅረቱን ለአዲስ ስታንዳርድ አስረድተዋል፡፡

አንድ መምህር የፈለገውንም ያህል የአገልግሎት ጊዜ ቢኖረው የስራ ልምድን መሠረት ያደረገ የደሞዝ ማሻሻያ የሚባል ነገር የለም ለምሳሌ እኔ ስቀጠር ደሞዜ 11,305.00 ነበር ከእኔ በፊት የተቀጠሩትም ከእኔ በኃላ አመታት ቆይተው የተቀጠሩትም ተመሳሳይ ነው የሚከፈላቸው፡፡ ይህ ማለት 2 አመትም ይሁን 10 አመት የፈለገውን ያህል ዓመት ያገለገለ መምህር ደመወዙ እንደ አዲስ ከሚቀጠር መምህር ደመወዝ ጋር እኩል ነው ሲሉ አክለው ገልፀዋል፡፡

ሌላኛው የዩኒቨርሲቲ መምህርም እንደ እንደገለፁት በንጉሱ ዘመን የነበረ 800 ብር የቤት አበለ (house allowance) ታክስ ተደርጎ 520.00 ብር የነበር ሲሆን እስከ ዛሬ ማስተካከያ አልተደረገበትም፡፡ መምህሩ በየ አመቱ እንኳን ምን ያህል የቤት ኪራይ ዋጋ እንደሚጨምር ልብ ማለት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ አዲስ አበባም፣ ጎንደርም፣ ጅማም፣ ሀዋሳም፣ መቀሌም ይሁን የትኛውም በፌዴራልም፣ በክልልም፣ በዞንም ያሉ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የቤት አበሉ (house allowance) ተመሳሳይ (እኩል) ነው፡፡ የከተሞችን የኑሮ ዉድነት ከግምት ውስጥ ያላስገባ አዲስ አበባም ጎንደርም ደባርቅም እንጅባራም የቤት አበሉ  800.00 ብር መሆኑ ትክክል አይደለም ብለዋል፡፡

በዩኒቨርስቲ ዉስጥ ያሉትን የኮንደሚኒየም ቤቶች የዩኒቨርሲቲዎቹ ፕረዘዳንት፣ ምክትል ፕረዘዳንት እና የኮሌጅ ዳይሬክተሮች ብቻ የሚኖሩባቸዉ ናቸው የሚሉት መምህሩ ከብዙ የመምህራኑ አቤቱታ በኋላ ማስተካከያ ተደርጓል ለማለት ያህል በሰኔ 23/2014 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ ከ11,305.00 ወደ 12579.00 ጭማሪ ተደርጓል ተባልን ይህ ማለት የቤት አበል (house allowance) ሳይጨምር  የተጣራ ክፍያ ከ8056.90 ወደ 8795.82 ብር ብቻ ነው ተጨምሯል ተባልን የ738.92 ብር ብቻ ጭማሪ ከሐምሌ 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለነበረን ቅሬታ ማለት ነው፡፡ የቤት አበል ግን ምንም ማስተካከያ ሳይደረግበት ቀርቷል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

አዲስ ስታንዳር ያነጋገራቸው መምህራን ቅሬታዎቻችን ተሠሚነትና መፍትሔ ስላላገኙ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ከመስከረም 01/2015 ጀምሮ መምህራን እና የቴክኒካል ረዳቶች በማንኛውም የዩኒቨርስቲ እንቅስቃሴዎች ይሁን የመማር ማስተማር ሂደት ላይ የማንሳተፍ መሆኑን በደብዳቤዎችን አሳዉቀናል ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ አክለው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዘዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) የዩኒቨርሲቲ መምህራን ያቀረቡትን ጥያቄዎችን ለትምህርት ሚኒስቴርና ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት አቅርበን አንዳንድ ለውጦች ተደርገዋል ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልፀዋል፡፡ የማኅበሩ ፕሬዘዳንት ከክፍያ ተመን ጥያቄ ጋር መስተካከያ ተደርጎ በሁሉም ዩኒቨርሲቲ ከሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በገንዘብ ሚንስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ተፈርሞ ተግባሪዊ መደረጉን አስረድተዋል፡፡ መምህራኑ አንድ ሰራተኛ የሚሰራቸውን ስራዎች (Job Description) ስራ እድገት ደረጃ ምደባ ላይ ቅሬታ እንደነበራቸው ጠቅሰው የደረጃ ምደባው ማሻሻያ ተደርጎበት ከረዳት ምሩቅና ከፕሮፌሰር በስተቀር ሁሉም ከነበሩበት አንደ ደረጃ ከፍ እንዲሉ ተደርጓል ብለዋል፡፡ ጨምረውም መምህራኑ ግን የደረጃ እድገቱ አሁንም በቂ አይደለም ማለታቸውን ገልፀው በፊት ከነበረው የተሻለ ነው ብለዋል፡፡

የደረጃ እድገቱ የረዳት ምሩቃንና ፕሮፌሰሮችን ባለማካተቱ እንደገና እንዲታይ ጥያቄ አቅርናል ያሉት ፕሬዘዳንቱ ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) የቤት አበልንም በተመለከተ እየተሰራበት መሆኑን ገልፀው በቅርቡ ይጠናቀቃል ብለን እናስባለን ብለዋል፡፡ ሎሎች ጥያቄዎችንም በተመለከተ ደረጃ በደረጃ እንደሚታዩና በቅርበት እንደሚከታተሉም አስረድተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲ መምህራኑ ጥያቄዎቻቸው ከልተመለሰ ከመስከረም 1 ቀን ጀምሮ ስራ የማቆም አድማ እንደሚያደረጉ በመግለፃቸው የትምህርት ሂደቱን እንዳይስተጓጓል ምን ታስቧል ብለን ለቀረብንላቸውም ጥያቄ መንግስት ህጉ በሚፈቅደው ልክ እየተሰራ ባለበት ወቅት መምህራኑ የራሳችንን እርምጃ እንወስዳለን ማለታቸው ተገቢ አለመሆኑን ጠቅሰው ጥያቄዎቹ ውውይትና ድርድር የሚስፈልገው በመሆኑ ለሁሉም ጥያቄ እስከ መስከረም ምላሽ መስጠት አስቸጋሪ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊን ለተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ደጋግመን ያደረግነው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.